ትምህርት 11
ስለ ኢየሱስ የጻፉ ሰዎች
በሥዕሉ ላይ ያሉትን ሰዎች አየሃቸው?— እነዚህ ሰዎች ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ፣ ዮሐንስ፣ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣ ይሁዳና ጳውሎስ ናቸው። ሁሉም ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የኖሩ ሰዎች ሲሆኑ ስለ ኢየሱስ ጽፈዋል። እስቲ ስለ እነዚህ ሰዎች እንመልከት።
ስለ እነዚህ ሰዎች ምን ያህል ታውቃለህ?
ስለ ኢየሱስ ከጻፉት ሰዎች መካከል ሦስቱ፣ ከእሱ ጋር ይሰብኩ የነበሩ ሐዋርያት ናቸው። እነዚህ ሦስት ሰዎች የትኞቹ እንደሆኑ ታውቃለህ?— ማቴዎስ፣ ዮሐንስና ጴጥሮስ ናቸው። ማቴዎስ እና ዮሐንስ የተባሉት ሐዋርያት ኢየሱስን በደንብ ያውቁት የነበረ ሲሆን
ሁለቱም ስለ ኢየሱስ ሕይወት በዝርዝር ጽፈዋል። በተጨማሪም ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ራእይ የተባለ መጽሐፍ እንዲሁም አንደኛ ዮሐንስ፣ ሁለተኛ ዮሐንስ እና ሦስተኛ ዮሐንስ ተብለው የሚጠሩ ደብዳቤዎችን ጽፏል። ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ደብዳቤዎች ጽፏል። ደብዳቤዎቹ አንደኛ ጴጥሮስ እና ሁለተኛ ጴጥሮስ በመባል ይጠራሉ። ጴጥሮስ በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤው ላይ ይሖዋ ከሰማይ ሆኖ ኢየሱስን በተመለከተ ‘ይህ ልጄ ነው። እወደዋለሁ እንዲሁም እኮራበታለሁ’ ማለቱን ገልጿል።በሥዕሉ ላይ የሚታዩት ሌሎች ሰዎችም በመጽሐፋቸው ላይ ከጻፉት ነገር ስለ ኢየሱስ መማር እንችላለን። ከእነዚህ አንዱ ማርቆስ ነው። ማርቆስ ኢየሱስ በተያዘበት ወቅት በቦታው ተገኝቶ የተከናወነውን ሁሉ ሳይመለከት አልቀረም። ሌላው ደግሞ ሉቃስ ነው። ሉቃስ ሐኪም ሲሆን ክርስቲያን የሆነው ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ሳይሆን አይቀርም።
በሥዕሉ ላይ የምታያቸው ሌሎች ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ደግሞ የኢየሱስ ታናናሽ ወንድሞች ናቸው። ስማቸውን ታውቃለህ?— ያዕቆብ እና ይሁዳ ይባላሉ። እነዚህ ወንድሞቹ መጀመሪያ ላይ በኢየሱስ አያምኑም ነበር። እንዲያውም እብድ እንደሆነ አስበው ነበር። በኋላ ግን በኢየሱስ አምነው ክርስቲያኖች ሆኑ።
በሥዕሉ ላይ የሚታየው ሌላው የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ ጳውሎስ ነው። ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ሳኦል ተብሎ ይጠራ ነበር። ክርስቲያኖችን በጣም ይጠላ የነበረ ከመሆኑም በላይ ብዙ መጥፎ ነገር አድርሶባቸዋል። ጳውሎስ ክርስቲያን ለመሆን የፈለገው ለምን እንደሆነ ታውቃለህ?— አንድ ቀን ጳውሎስ በመንገድ ላይ እያለ አንድ ድምፅ ከሰማይ ሲያነጋግረው ሰማ። ያነጋገረው ኢየሱስ ነበር! ኢየሱስ፣ ‘በእኔ የሚያምኑትን የምታስቸግራቸው ለምንድን ነው?’ ብሎ ጠየቀው። ከዚያ በኋላ ጳውሎስ ተለውጦ ክርስቲያን ሆነ። ጳውሎስ ከሮም እስከ ዕብራውያን ያሉትን 14 የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት ጽፏል።
መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ እናነባለን አይደል?— መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ስለ ኢየሱስ ብዙ መማር እንችላለን። አንተስ ስለ ኢየሱስ ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ?—