ትምህርት 7
ብቸኝነትና ፍርሃት ተሰምቶህ ያውቃል?
በሥዕሉ ላይ ያለውን ትንሽ ልጅ አየኸው? ብቻውን ከመሆኑም ሌላ የፈራ ይመስላል አይደል? አንተስ እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል?— ሁሉም ሰው አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ይሰማዋል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አንዳንድ የይሖዋ ወዳጆችም ብቸኝነትና ፍርሃት ተሰምቷቸው እንደሚያውቅ ይናገራል። ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ኤልያስ ነው። እስቲ የኤልያስን ታሪክ እንመልከት።
ኤልያስ፣ ኢየሱስ ከመወለዱ ከረጅም ጊዜ በፊት በእስራኤል ይኖር ነበር። በወቅቱ የእስራኤል ንጉሥ የነበረው አክዓብ፣ እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን የሚያገለግል ሰው አልነበረም። አክዓብና ሚስቱ ኤልዛቤል የሚያመልኩት በኣል የተባለውን የሐሰት አምላክ ነበር። በመሆኑም አብዛኞቹ እስራኤላውያን በኣልን ማምለክ ጀመሩ። በጣም መጥፎ ሴት የነበረችው ንግሥት ኤልዛቤል፣ ኤልያስን ጨምሮ ይሖዋን የሚያገለግሉ ሰዎችን በሙሉ ለመግደል ትፈልግ ነበር። በዚህ ጊዜ ኤልያስ ምን እንዳደረገ ታውቃለህ?—
ኤልያስ መኖሪያውን ትቶ ሸሸ! ረጅም ርቀት ተጉዞ ወደ በረሃ በመሄድ በአንድ ዋሻ ውስጥ ተደበቀ። ይህን ያደረገው ለምን ይመስልሃል?— አዎ፣ በጣም ፈርቶ ስለነበር ነው። ይሁን እንጂ ኤልያስ መፍራት አልነበረበትም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ሊረዳው እንደሚችል ያውቅ ነበር። ይሖዋ ምን ያህል ኃይል እንዳለው ከዚህ ቀደም ለኤልያስ አሳይቶታል። በአንድ ወቅት ይሖዋ፣ ኤልያስ ላቀረበው ጸሎት ምላሽ በመስጠት እሳት ከሰማይ እንዲወርድ አድርጎ ነበር። አሁንም ቢሆን ይሖዋ፣ ኤልያስን ሊረዳው እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም!
ኤልያስ ዋሻው ውስጥ እያለ ይሖዋ ‘እዚህ ምን ታደርጋለህ?’ በማለት ጠየቀው። ኤልያስም ‘አንተን ከሚያመልኩት መካከል የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ። እኔም እንዳልገደል ፈርቻለሁ’ በማለት መለሰ። ኤልያስ ሌሎቹ የይሖዋ አገልጋዮች በሙሉ እንደተገደሉ አስቦ ነበር። ይሖዋ ግን እንዲህ አለው፦ ‘የቀረኸው አንተ ብቻ አይደለህም። አሁንም እኔን የሚያገለግሉ 7,000 ሰዎች አሉኝ። አትፍራ። ብዙ የምትሠራው ሥራ አዘጋጅቼልሃለሁ!’ ኤልያስ ይህንን ሲሰማ የተደሰተ ይመስልሃል?—
ኤልያስ ካጋጠመው ሁኔታ ምን ትምህርት ማግኘት ትችላለህ?— ምንም ነገር ቢያጋጥምህ ብቸኝነትና ፍርሃት ሊሰማህ አይገባም። አንተንም ሆነ ይሖዋን የሚወዱ ወዳጆች አሉህ። በተጨማሪም፣ ይሖዋ ከፍተኛ ኃይል ስላለው ምንጊዜም ይረዳሃል! መቼም ቢሆን ብቻህን እንዳልሆንክ ማወቅህ አያስደስትህም?—