ትምህርት 41
ዳዊት እና ሳኦል
ዳዊት ጎልያድን ከገደለ በኋላ ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን የሠራዊቱ መሪ አደረገው። ዳዊት ብዙ ጦርነቶችን አሸነፈ፤ እስራኤላውያንም በጣም ወደዱት። ዳዊት ከጦርነት በሚመለስበት ወቅት፣ ሴቶች ‘ሳኦል ሺዎችን ገደለ፤ ዳዊት ደግሞ አሥር ሺዎችን ገደለ’ ብለው እየዘፈኑና እየጨፈሩ ይቀበሉት ነበር። ስለዚህ ሳኦል በዳዊት ይቀና ጀመር፤ በዚህም የተነሳ ሊገድለው ፈለገ።
ዳዊት በገና ሲጫወት ጎበዝ ነበር። አንድ ቀን ዳዊት ለሳኦል በገና እየተጫወተለት ሳለ ንጉሡ በዳዊት ላይ ጦሩን ወረወረበት። ሆኖም ዳዊት ጎንበስ ሲል ጦሩ ግድግዳው ላይ ተሰካ። ከዚያ በኋላም ሳኦል በተደጋጋሚ ዳዊትን ለመግደል ሞክሯል። በመጨረሻም ዳዊት ሸሽቶ በረሃ ውስጥ ተደበቀ።
ሳኦል 3,000 ወታደሮችን ይዞ ዳዊትን ፍለጋ ሄደ። ከዚያም አንድ ዋሻ ውስጥ ገባ፤ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች የተደበቁት እዚሁ ዋሻ ውስጥ ነበር። ከዳዊት ጋር
የነበሩት ሰዎችም ‘ሳኦልን ለመግደል ከዚህ የተሻለ አጋጣሚ አታገኝም’ በማለት ዳዊትን አደፋፈሩት። በዚህ ጊዜ ዳዊት ቀስ ብሎ ወደ ንጉሥ ሳኦል ተጠጋና የልብሱን ጫፍ ቆረጠ። ሳኦል፣ ዳዊት ምን እንዳደረገ አላወቀም ነበር። በኋላ ግን ዳዊት፣ ይሖዋ ለቀባው ንጉሥ አክብሮት ባለማሳየቱ በጣም አዘነ። አብረውት የነበሩት ሰዎችም በሳኦል ላይ ጉዳት እንዲያደርሱበት አልፈቀደላቸውም። ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ ሳኦልን በመጥራት ሊገድለው ይችል እንደነበረ ነገረው። ታዲያ ሳኦል ከዚህ በኋላ ዳዊትን ማሳደዱን ይተው ይሆን?በፍጹም፤ ሳኦል ዳዊትን ማሳደዱን አልተወም። አንድ ቀን ዳዊትና የእህቱ ልጅ አቢሳ ተደብቀው ወደ ሳኦል ድንኳን ገቡ። የሳኦል ጠባቂ የነበረው አበኔርም ተኝቶ ነበር። በዚህ ጊዜ አቢሳ ‘ይህ ጥሩ አጋጣሚ ነው! ሳኦልን ልግደለው’ አለ። ዳዊት ግን እንዲህ ብሎ መለሰ፦ ‘ይሖዋ ራሱ በሳኦል ላይ እርምጃ ይወስድበታል። አሁን ጦሩንና የውኃ መያዣውን ይዘን እንሂድ።’
ከዚያም ዳዊት፣ ሳኦል በሰፈረበት አካባቢ የሚገኝ ተራራ ላይ ወጣ። ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ አለ፦ ‘አበኔር፣ ንጉሡን የማትጠብቀው ለምንድን ነው? የሳኦል የውኃ መያዣና ጦር የት አለ?’ ሳኦልም እየተናገረ ያለው ዳዊት መሆኑን ሲያውቅ ‘ልትገድለኝ ትችል ነበር፤ ግን አልገደልከኝም። ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ አንተ እንደምትሆን አውቃለሁ’ አለ። ከዚያም ሳኦል ወደ ቤተ መንግሥቱ ተመለሰ። ሳኦል ዳዊትን ይጠላው የነበረ ቢሆንም ከቤተሰቡ አባላት መካከል ዳዊትን የሚወድ ሰው ነበር።
“ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር በእናንተ በኩል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ። የተወደዳችሁ ወንድሞች፣ ራሳችሁ አትበቀሉ።”—ሮም 12:18, 19