መዝሙር 18:1-50
ለሙዚቀኞች ቡድን መሪ። የይሖዋ አገልጋይ የሆነው ዳዊት፣ ይሖዋ ከጠላቶቹ ሁሉ እጅና ከሳኦል እጅ ባዳነው ቀን ለይሖዋ የዘመረው መዝሙር፦+
18 ብርታቴ ይሖዋ ሆይ፣+ እወድሃለሁ።
2 ይሖዋ ቋጥኜ፣ ምሽጌና ታዳጊዬ ነው።+
አምላኬ የምሸሸግበት ዓለቴ ነው፤+ጋሻዬ፣ የመዳኔ ቀንድና* አስተማማኝ መጠጊያዬ ነው።+
3 ውዳሴ የሚገባውን ይሖዋን እጠራለሁ፤ከጠላቶቼም እድናለሁ።+
4 የሞት ገመዶች ተተበተቡብኝ፤+የማይረቡ ሰዎች የለቀቁት ድንገተኛ ጎርፍ አሸበረኝ።+
5 የመቃብር* ገመድ ተጠመጠመብኝ፤የሞት ወጥመድ ተጋረጠብኝ።+
6 በጭንቅ ውስጥ ሳለሁ ይሖዋን ጠራሁት፤እርዳታ ለማግኘት አምላኬን አጥብቄ ተማጸንኩት።
በመቅደሱ ሆኖ ድምፄን ሰማ፤+እርዳታ ለማግኘት የማሰማውም ጩኸት ወደ ጆሮው ደረሰ።+
7 ምድርም ትንቀጠቀጥና ትናወጥ ጀመር፤+የተራሮች መሠረቶች ተንቀጠቀጡ፤እሱ ስለተቆጣም ራዱ።+
8 ከአፍንጫው ጭስ ወጣ፤የሚባላም እሳት ከአፉ ወጣ፤+ፍምም ከእሱ ፈለቀ።
9 ወደ ታች ሲወርድ ሰማያት እንዲያጎነብሱ አደረገ፤+ከእግሮቹም በታች ጥቅጥቅ ያለ ደመና ነበር።+
10 በኪሩብ ላይ ተቀምጦ እየበረረ መጣ።+
በመንፈስ* ክንፎች በፍጥነት ወረደ።+
11 ከዚያም በጨለማ ራሱን ሸፈነ፤+ጥቁር ውኃና ጥቅጥቅ ያለ ደመና+እንደ መጠለያ በዙሪያው ነበር።
12 በፊቱ ካለው ብርሃን፣ከደመናቱ መካከል በረዶና ፍም ወጣ።
13 ከዚያም ይሖዋ በሰማያት ያንጎደጉድ ጀመር፤+ልዑሉ አምላክ ድምፁን አሰማ፤+ደግሞም በረዶና ፍም ነበር።
14 ፍላጻዎቹን አስፈንጥሮ በታተናቸው፤+መብረቁን አዥጎድጉዶ ግራ አጋባቸው።+
15 ይሖዋ ሆይ፣ ከተግሣጽህ፣ ከአፍንጫህም ከሚወጣው ኃይለኛ እስትንፋስ የተነሳ+የጅረቶች ወለል ታየ፤*+የምድር መሠረቶችም ተገለጡ።
16 ከላይ ሆኖ እጁን ሰደደ፤ከጥልቅ ውኃ ውስጥም አወጣኝ።+
17 ከብርቱ ጠላቴ አዳነኝ፤+ከእኔ ይበልጥ ብርቱዎች ከሆኑት፣ ከሚጠሉኝ ሰዎች ታደገኝ።+
18 ችግር ላይ በወደቅኩበት ቀን ተነሱብኝ፤+ይሖዋ ግን ድጋፍ ሆነልኝ።
19 ከዚያም ደህንነት ወደማገኝበት ስፍራ* አመጣኝ፤በእኔ ስለተደሰተ ታደገኝ።+
20 ይሖዋ እንደ ጽድቄ ወሮታ ይከፍለኛል፤+እንደ እጄ ንጽሕና ብድራት ይመልስልኛል።+
21 የይሖዋን መንገድ ጠብቄአለሁና፤አምላኬን በመተው ክፉ ድርጊት አልፈጸምኩም።
22 ፍርዱ ሁሉ በፊቴ ነው፤ደንቦቹን ቸል አልልም።
23 በፊቱ እንከን የለሽ ሆኜ እኖራለሁ፤+ራሴንም ከስህተት እጠብቃለሁ።+
24 ይሖዋ እንደ ጽድቄ፣+በፊቱ ንጹሕ እንደሆኑት እጆቼ ብድራት ይመልስልኝ።+
25 ታማኝ ለሆነ ሰው ታማኝ ትሆናለህ፤+እንከን የለሽ ለሆነ ሰው እንከን የለሽ ትሆናለህ፤+
26 ከንጹሕ ሰው ጋር ንጹሕ ሆነህ ትገኛለህ፤+ጠማማ ለሆነ ሰው ግን ብልህ መሆንህን ታሳያለህ።+
27 ችግረኞችን* ታድናለህና፤+ትዕቢተኛውን* ግን ታዋርዳለህ።+
28 ይሖዋ ሆይ፣ መብራቴን የምታበራው አንተ ነህና፤አምላኬ ሆይ፣ ጨለማዬን ብርሃን የምታደርገው አንተ ነህ።+
29 በአንተ እርዳታ ወራሪውን ቡድን መጋፈጥ እችላለሁ፤+በአምላክ ኃይል ቅጥር መውጣት እችላለሁ።+
30 የእውነተኛው አምላክ መንገድ ፍጹም ነው፤+የይሖዋ ቃል የነጠረ ነው።+
እሱ መጠጊያ ለሚያደርጉት ሁሉ ጋሻቸው ነው።+
31 ደግሞስ ከይሖዋ ሌላ አምላክ ማን ነው?+
ከአምላካችንስ ሌላ ዓለት ማን ነው?+
32 ብርታትን የሚያስታጥቀኝ እውነተኛው አምላክ ነው፤+መንገዴንም ፍጹም ያደርግልኛል።+
33 እግሮቼን እንደ ዋልያ እግሮች ያደርጋል፤በከፍታ ቦታዎች ላይ ያቆመኛል።+
34 እጆቼን ለጦርነት ያሠለጥናል፤ክንዶቼ የመዳብ ደጋን ማጠፍ ይችላሉ።
35 የመዳን ጋሻህን ትሰጠኛለህ፤+ቀኝ እጅህ ይደግፈኛል፤ትሕትናህም ታላቅ ያደርገኛል።+
36 ለእርምጃዬ መንገዱን ታሰፋልኛለህ፤እግሮቼ* አያዳልጣቸውም።+
37 ጠላቶቼን አሳድጄ እደርስባቸዋለሁ፤ተጠራርገው እስኪጠፉ ድረስ ወደ ኋላ አልመለስም።
38 እንዳያንሰራሩ አድርጌ አደቃቸዋለሁ፤+እግሬ ሥር ይወድቃሉ።
39 ለውጊያው ብርታት ታስታጥቀኛለህ፤ጠላቶቼ ሥሬ እንዲወድቁ ታደርጋለህ።+
40 ጠላቶቼ ከእኔ እንዲሸሹ ታደርጋለህ፤*እኔም የሚጠሉኝን አጠፋቸዋለሁ።*+
41 እርዳታ ለማግኘት ይጮኻሉ፤ ሆኖም የሚያድናቸው የለም፤ወደ ይሖዋም ይጮኻሉ፤ እሱ ግን አይመልስላቸውም።
42 በነፋስ ፊት እንዳለ አቧራ ፈጽሜ አደቃቸዋለሁ፤በመንገድ ላይ እንዳለ ጭቃ አውጥቼ እጥላቸዋለሁ።
43 ስህተት ከሚለቃቅሙ ሰዎች ታድነኛለህ።+
የብሔራት መሪ አድርገህ ትሾመኛለህ።+
የማላውቀው ሕዝብ ያገለግለኛል።+
44 ስለ እኔ በሰሙት ነገር ብቻ ይታዘዙኛል፤የባዕድ አገር ሰዎችም አንገታቸውን ደፍተው ወደ ፊቴ ይቀርባሉ።+
45 የባዕድ አገር ሰዎች ወኔ ይከዳቸዋል፤*ከምሽጎቻቸው እየተንቀጠቀጡ ይወጣሉ።
46 ይሖዋ ሕያው ነው! ዓለቴ+ ይወደስ!
የመዳኔ አምላክ ከፍ ከፍ ይበል።+
47 እውነተኛው አምላክ ይበቀልልኛል፤+ሕዝቦችንም ከበታቼ ያስገዛልኛል።
48 በቁጣ ከተሞሉ ጠላቶቼ ይታደገኛል፤ከሚያጠቁኝ ሰዎች በላይ ከፍ ከፍ ታደርገኛለህ፤+ከዓመፀኛ ሰው ታድነኛለህ።
49 ይሖዋ ሆይ፣ በብሔራት መካከል የማከብርህ ለዚህ ነው፤+ለስምህም የውዳሴ መዝሙር እዘምራለሁ።+
50 እሱ ለንጉሡ ታላላቅ የማዳን ሥራዎች ያከናውናል፤*+ለቀባውም ታማኝ ፍቅር ያሳያል፤+ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም ይህን ያደርጋል።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “ኃያል አዳኜና።” የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “የሲኦል።” የሰው ልጆችን ሁሉ መቃብር ያመለክታል። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “በነፋስ።”
^ ወይም “የውኃ መውረጃ ቦዮች ታዩ።”
^ ወይም “ሰፊ ወደሆነ ስፍራ።”
^ ወይም “የተጎሳቆሉትን ሰዎች።”
^ ቃል በቃል “ትዕቢተኛውን ዓይን።”
^ ወይም “ቁርጭምጭሚቶቼ።”
^ ወይም “የጠላቶቼን ጀርባ ትሰጠኛለህ።”
^ ቃል በቃል “ጸጥ አሰኛቸዋለሁ።”
^ ወይም “ይጠወልጋሉ።”
^ ወይም “ታላላቅ ድሎችን ያጎናጽፋል።”