የማርቆስ ወንጌል 7:1-37
7 ከኢየሩሳሌም የመጡ ፈሪሳውያንና አንዳንድ ጸሐፍት ወደ እሱ ተሰበሰቡ።+
2 ከደቀ መዛሙርቱ አንዳንዶቹ በረከሰ ማለትም ባልታጠበ እጅ* ምግብ ሲበሉ አዩ።
3 (ፈሪሳውያንና አይሁዳውያን ሁሉ የአባቶችን ወግ አጥብቀው ስለሚከተሉ እጃቸውን እስከ ክርናቸው ድረስ ካልታጠቡ አይበሉም ነበር፤
4 ከገበያ ሲመለሱም ካልታጠቡ በስተቀር አይበሉም። ጽዋዎችን፣ ገንቦዎችንና የነሐስ ዕቃዎችን ውኃ ውስጥ እንደመንከር* ያሉ ከአባቶቻቸው የወረሷቸውና አጥብቀው የሚከተሏቸው ሌሎች በርካታ ወጎችም አሉ።)+
5 በመሆኑም እነዚህ ፈሪሳውያንና ጸሐፍት “ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ ከመከተል ይልቅ በረከሰ እጅ የሚበሉት ለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት።+
6 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “ኢሳይያስ፣ ግብዞች ስለሆናችሁት ስለ እናንተ በትክክል ተንብዮአል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው።+
7 የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።’+
8 የአምላክን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ አጥብቃችሁ ትከተላላችሁ።”+
9 ደግሞም እንዲህ አላቸው፦ “የራሳችሁን ወግ ለመጠበቅ ስትሉ የአምላክን ትእዛዝ በዘዴ ገሸሽ ታደርጋላችሁ።+
10 ለምሳሌ ሙሴ ‘አባትህንና እናትህን አክብር’+ እንዲሁም ‘አባቱን ወይም እናቱን የሚሳደብ* ይገደል’+ ብሏል።
11 እናንተ ግን እንዲህ ትላላችሁ፦ ‘አንድ ሰው አባቱን ወይም እናቱን “እናንተን መጦር የምችልበት፣ ያለኝ ነገር ሁሉ ቁርባን (ማለትም ለአምላክ የተወሰነ ስጦታ) ነው” ቢል’
12 ከዚያ በኋላ ለአባቱ ወይም ለእናቱ ምንም ነገር እንዲያደርግ አትፈቅዱለትም።+
13 በመሆኑም ለሌሎች በምታስተላልፉት ወግ የአምላክን ቃል ትሽራላችሁ።+ እንዲህ ያለም ብዙ ነገር ታደርጋላችሁ።”+
14 ከዚያም ሕዝቡን እንደገና ወደ እሱ ጠርቶ እንዲህ አላቸው፦ “ሁላችሁም ስሙኝ፤ የምናገረውንም አስተውሉ።+
15 ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን ሊያረክስ የሚችል ምንም ነገር የለም፤ ከዚህ ይልቅ ሰውን የሚያረክሰው ከውስጡ የሚወጣው ነው።”+
16 *——
17 ከሕዝቡ ተለይቶ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ምሳሌው ይጠይቁት ጀመር።+
18 እሱም እንዲህ አላቸው፦ “እናንተም እንደ እነሱ ማስተዋል ተሳናችሁ? ከውጭ ወደ ውስጥ ገብቶ ሰውን ሊያረክስ የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ አታውቁም?
19 ምክንያቱም የሚገባው ወደ ልቡ ሳይሆን ወደ ሆዱ ነው፤ ከዚያም ወጥቶ ወደ ጉድጓድ ይገባል።” እንዲህ በማለት ምግብ ሁሉ ንጹሕ መሆኑን አመለከተ።
20 አክሎም እንዲህ አለ፦ “ሰውን የሚያረክሰው ከውስጡ የሚወጣው ነው።+
21 ከውስጥ ይኸውም ከሰው ልብ+ ክፉ ሐሳብ ይወጣል፦ የፆታ ብልግና፣* ሌብነት፣ ግድያ፣
22 ምንዝር፣ መጎምጀት፣ ክፋት፣ ማታለል፣ ማንአለብኝነት፣* ምቀኝነት፣* ስድብ፣ ትዕቢትና ሞኝነት።
23 እነዚህ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከሰው ልብ ይወጣሉ፤ ሰውንም ያረክሳሉ።”
24 ከዚያም ተነስቶ ወደ ጢሮስና ሲዶና ክልል ሄደ።+ ወደ አንድ ቤትም ገባ፤ እዚያ መኖሩንም ማንም እንዲያውቅ አልፈለገም፤ ይሁንና ከሰዎች ሊሰወር አልቻለም።
25 ወዲያውም፣ ትንሽ ልጇ በርኩስ መንፈስ የተያዘችባት አንዲት ሴት ስለ እሱ ሰምታ መጣችና እግሩ ላይ ወደቀች።+
26 ሴትየዋ ግሪካዊት፣ በዜግነት* ደግሞ ሲሮፊንቃዊት ነበረች፤ እሷም ጋኔኑን ከልጇ እንዲያስወጣላት ወተወተችው።
27 እሱ ግን “የልጆችን ዳቦ ወስዶ ለቡችሎች መጣል ተገቢ ስላልሆነ መጀመሪያ ልጆቹ ይጥገቡ” አላት።+
28 ሆኖም ሴትየዋ መልሳ “አዎ ጌታዬ፣ ቡችሎችም እኮ ከገበታ በታች ሆነው ከልጆች የሚወድቀውን ፍርፋሪ ይበላሉ” አለችው።
29 በዚህ ጊዜ “ሂጂ፤ እንዲህ ስላልሽ ጋኔኑ ከልጅሽ ወጥቷል” አላት።+
30 እሷም ወደ ቤቷ ስትመለስ ልጇ አልጋ ላይ ተኝታ፣ ጋኔኑም ወጥቶላት አገኘቻት።+
31 ኢየሱስ ከጢሮስ ክልል ሲመለስ በሲዶና በኩል አድርጎ ዲካፖሊስ በተባለው ክልል* በማለፍ ወደ ገሊላ ባሕር ሄደ።+
32 በዚያም* ሰዎች መስማት የተሳነውና የመናገር እክል ያለበት+ አንድ ሰው ወደ እሱ አምጥተው እጁን እንዲጭንበት ተማጸኑት።
33 እሱም ከሕዝቡ ለይቶ ለብቻው ወሰደው። ከዚያም ጣቶቹን በሰውየው ጆሮዎች ውስጥ አስገባ፤ እንትፍ ካለ በኋላም የሰውየውን ምላስ ዳሰሰ።+
34 ወደ ሰማይ እየተመለከተም በረጅሙ ተንፍሶ “ኤፈታ” አለው፤ ይህም “ተከፈት” ማለት ነው።
35 በዚህ ጊዜ ጆሮዎቹ ተከፈቱ፤+ ምላሱም ተፈቶ አጥርቶ መናገር ጀመረ።
36 ይህን ለማንም እንዳይናገሩ አዘዛቸው፤+ እነሱ ግን ይበልጥ ባስጠነቀቃቸው መጠን የዚያኑ ያህል ነገሩን በስፋት ያወሩ ነበር።+
37 እንዲያውም ከመጠን በላይ ከመደነቃቸው የተነሳ+ “ያደረገው ነገር ሁሉ መልካም ነው። ሌላው ቀርቶ መስማት የተሳናቸው ሰዎች እንዲሰሙ፣ ዱዳዎችም እንዲናገሩ ያደርጋል” አሉ።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ሃይማኖታዊ ሥርዓትን በተከተለ መንገድ አለመንጻትን ያመለክታል።
^ ቃል በቃል “እንደማጥመቅ።”
^ ወይም “የሚያንቋሽሽ።”
^ ፖርኒያ የተባለው ግሪክኛ ቃል ብዙ ቁጥር። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ወይም “እፍረተ ቢስነት የሚንጸባረቅበት ምግባር።” ግሪክኛ፣ አሴልጊያ። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
^ ቃል በቃል “ምቀኛ ዓይን።”
^ ወይም “በትውልድ።”
^ ወይም “አሥሩ ከተሞች በሚገኙበት ክልል።”
^ ኢየሱስ በዲካፖሊስ ሳለ ማለት ነው።