ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ 7:1-17
7 ከዚህ በኋላ አራት መላእክት በአራቱ የምድር ማዕዘናት ቆመው አየሁ፤ እነሱም በምድር ወይም በባሕር ወይም በማንኛውም ዛፍ ላይ ምንም ነፋስ እንዳይነፍስ አራቱን የምድር ነፋሳት አጥብቀው ይዘው ነበር።
2 እንዲሁም የሕያው አምላክ ማኅተም ያለው ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ* ወደ ላይ ሲወጣ አየሁ፤ እሱም ምድርንና ባሕርን እንዲጎዱ ሥልጣን የተሰጣቸውን አራቱን መላእክት በታላቅ ድምፅ
3 እንዲህ አላቸው፦ “የአምላካችንን ባሪያዎች ግንባራቸው ላይ ማኅተም እስክናደርግባቸው ድረስ+ ምድርን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጉዱ።”+
4 የታተሙትን ሰዎች ቁጥር ሰማሁ፤ ቁጥራቸው 144,000+ ሲሆን የታተሙትም ከእያንዳንዱ የእስራኤል ልጆች ነገድ ነበር፦+
5 ከይሁዳ ነገድ 12,000 ታተሙ፤ከሮቤል ነገድ 12,000፣ከጋድ ነገድ 12,000፣
6 ከአሴር ነገድ 12,000፣ከንፍታሌም ነገድ 12,000፣ከምናሴ+ ነገድ 12,000፣
7 ከስምዖን ነገድ 12,000፣ከሌዊ ነገድ 12,000፣ከይሳኮር ነገድ 12,000፣
8 ከዛብሎን ነገድ 12,000፣ከዮሴፍ ነገድ 12,000፣ከቢንያም ነገድ 12,000 ታተሙ።
9 ከዚህ በኋላ አየሁ፤ እነሆም፣ ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ+ አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ ነጭ ልብስ ለብሰው+ በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆመው ነበር፤ የዘንባባ ዝንጣፊዎችንም በእጆቻቸው ይዘው ነበር።+
10 በታላቅም ድምፅ እየጮኹ “መዳን ያገኘነው በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው+ ከአምላካችን እንዲሁም ከበጉ+ ነው” ይሉ ነበር።
11 መላእክቱ ሁሉ በዙፋኑ፣ በሽማግሌዎቹና+ በአራቱ ሕያዋን ፍጥረታት ዙሪያ ቆመው ነበር፤ እነሱም በዙፋኑ ፊት በግንባራቸው ተደፍተው ለአምላክ ሰገዱ፤
12 እንዲህም አሉ፦ “አሜን! ውዳሴ፣ ግርማ፣ ጥበብ፣ ምስጋና፣ ክብር፣ ኃይልና ብርታት ለዘላለም ለአምላካችን ይሁን።+ አሜን።”
13 ከሽማግሌዎቹ አንዱ መልሶ “እነዚህ ነጭ ልብስ የለበሱት+ እነማን ናቸው? ከወዴትስ የመጡ ናቸው?” አለኝ።
14 እኔም ወዲያውኑ “ጌታዬ፣ የምታውቀው አንተ ነህ” አልኩት። እሱም እንዲህ አለኝ፦ “እነዚህ ታላቁን መከራ+ አልፈው የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።+
15 በአምላክ ዙፋን ፊት ያሉትም ለዚህ ነው፤ በቤተ መቅደሱም ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት እያቀረቡለት ነው፤ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም+ ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል።+
16 ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም እንዲሁም አይጠሙም፤ ፀሐይ አይመታቸውም፤ ሐሩሩም አያቃጥላቸውም፤+
17 ምክንያቱም በዙፋኑ መካከል ያለው በጉ+ እረኛቸው ይሆናል፤+ ወደ ሕይወት ውኃ ምንጭም ይመራቸዋል።+ አምላክም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።”*+