ዘሌዋውያን 26:1-46

  • ከጣዖት አምልኮ ራቁ (1, 2)

  • መታዘዝ የሚያስገኘው በረከት (3-13)

  • አለመታዘዝ የሚያስከትለው ቅጣት (14-46)

26  “‘ትሰግዱላቸው ዘንድ+ ለራሳችሁ ከንቱ አማልክትን አትሥሩ፤+ እንዲሁም ለራሳችሁ የተቀረጸ ምስል+ ወይም የማምለኪያ ዓምድ አታቁሙ፤ በምድራችሁም ከድንጋይ የተቀረጸ ምስል አታኑሩ፤+ ምክንያቱም እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። 2  ሰንበቶቼን ጠብቁ፤ ለመቅደሴም አክብሮት* ይኑራችሁ። እኔ ይሖዋ ነኝ። 3  “‘ባወጣኋቸው ደንቦች መሠረት ብትሄዱና ትእዛዛቴን ብትጠብቁ እንዲሁም ብትፈጽሙ+ 4  ዝናብን በወቅቱ አዘንብላችኋለሁ፤+ ምድሪቱም ምርቷን ትሰጣለች፤+ የሜዳ ዛፎችም ፍሬያቸውን ይሰጣሉ። 5  ገና እህላችሁን ወቅታችሁ ሳትጨርሱ ወይናችሁን የምትሰበስቡበት ጊዜ ይደርሳል፤ ገና ወይኑን ሰብስባችሁ ሳትጨርሱ ደግሞ ዘር የምትዘሩበት ጊዜ ይመጣል፤ ምግባችሁን እስክትጠግቡ ድረስ ትበላላችሁ፤ በምድራችሁም ያለስጋት ትቀመጣላችሁ።+ 6  በምድሪቱ ሰላም አሰፍናለሁ፤+ እናንተም ማንም ሳያስፈራችሁ ትተኛላችሁ፤+ እኔም አደገኛ አውሬዎች በምድሪቱ እንዳይኖሩ አደርጋለሁ፤ በምድራችሁም የጦርነት ሰይፍ አያልፍም። 7  እናንተም በእርግጥ ጠላቶቻችሁን ታሳድዳላችሁ፤ እነሱም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ። 8  አምስታችሁ 100 ሰዎችን ታሳድዳላችሁ፤ መቶዎቻችሁ ደግሞ 10,000 ሰዎችን ታሳድዳላችሁ፤ ጠላቶቻችሁም በፊታችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።+ 9  “‘እኔም ሞገስ አሳያችኋለሁ፤* ፍሬያማ እንድትሆኑና እንድትበዙ አደርጋችኋለሁ፤+ ከእናንተ ጋር የገባሁትንም ቃል ኪዳኔን እጠብቃለሁ።+ 10  እናንተም ያለፈውን ዓመት እህል ገና በልታችሁ ሳትጨርሱ ለዘንድሮው እህል ቦታ ለማግኘት ያለፈውን ዓመት እህል ታስለቅቃላችሁ። 11  የማደሪያ ድንኳኔን በመካከላችሁ እተክላለሁ፤+ እኔም አልተዋችሁም።* 12  በመካከላችሁ እሄዳለሁ፤ አምላካችሁም እሆናለሁ፤+ እናንተ ደግሞ ሕዝቦቼ ትሆናላችሁ።+ 13  የግብፃውያን ባሪያዎች ሆናችሁ እንዳትቀሩ ከዚያ ምድር ያወጣኋችሁና ቀንበራችሁን ሰብሬ ራሳችሁን ቀና አድርጋችሁ* እንድትሄዱ ያደረግኳችሁ እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ። 14  “‘ይሁን እንጂ የማትሰሙኝ ወይም እነዚህን ትእዛዛት በሙሉ የማትፈጽሙ ከሆነ+ 15  እንዲሁም ደንቦቼን ችላ የምትሉና+ ትእዛዛቴን በሙሉ ላለመፈጸም ድንጋጌዎቼን የምትጸየፉ፣* ቃል ኪዳኔንም የምታፈርሱ ከሆነ+ 16  እኔ ደግሞ እንዲህ አደርግባችኋለሁ፦ ዓይናችሁ እንዲጠፋና ሕይወታችሁ* እንዲመነምን የሚያደርግ የሳንባ ነቀርሳና ኃይለኛ ትኩሳት በእናንተ ላይ በማምጣት በጭንቀት እቀጣችኋለሁ። ዘራችሁን የምትዘሩት እንዲሁ በከንቱ ይሆናል፤ ምክንያቱም የሚበሉት ጠላቶቻችሁ ናቸው።+ 17  እኔም በእርግጥ ፊቴን አጠቁርባችኋለሁ፤ ጠላቶቻችሁም ድል ያደርጓችኋል፤+ የሚጠሏችሁም ሰዎች ይረግጧችኋል፤+ እንዲሁም ማንም ሳያሳድዳችሁ ትሸሻላችሁ።+ 18  “‘እነዚህ ሁሉ ነገሮች ደርሰውባችሁም የማትሰሙኝ ከሆነ ለሠራችሁት ኃጢአት ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። 19  ኃይለኛ የሆነውን ትዕቢታችሁን እሰብረዋለሁ፤ ሰማያችሁን እንደ ብረት፣+ ምድራችሁን ደግሞ እንደ መዳብ አደርገዋለሁ። 20  ምድራችሁ ምርቷን ስለማትሰጥና የምድርም ዛፍ ፍሬ ስለማያፈራ ኃይላችሁን እንዲሁ በከንቱ ታባክናላችሁ።+ 21  “‘ሆኖም እኔን መቃወማችሁን ከቀጠላችሁና እኔን ለመስማት ፈቃደኞች ሳትሆኑ ከቀራችሁ እንደ ኃጢአታችሁ መጠን ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። 22  የዱር አራዊትን እሰድባችኋለሁ፤+ እነሱም ልጆቻችሁን ይነጥቋችኋል፤+ የቤት እንስሶቻችሁንም ይበሉባችኋል፤ ቁጥራችሁም እንዲመናመን ያደርጋሉ፤ መንገዶቻችሁም ጭር ይላሉ።+ 23  “‘እነዚህ ሁሉ ነገሮች ደርሰውባችሁም እርማቴን ባትቀበሉና+ እኔን መቃወማችሁን ብትገፉበት 24  እኔም እናንተን በመቃወም እመጣባችኋለሁ፤ ለኃጢአታችሁም ሰባት እጥፍ እመታችኋለሁ። 25  ከእኔ ጋር የገባችሁትን ቃል ኪዳን ስላፈረሳችሁ+ በላያችሁ ላይ የበቀል ሰይፍ አመጣባችኋለሁ። በከተሞቻችሁ ውስጥ ከተሰበሰባችሁ በመካከላችሁ በሽታ እልክባችኋለሁ፤+ እናንተም ለጠላት እጅ ትሰጣላችሁ።+ 26  የዳቦ እጥረት እንዲከሰትባችሁ+ በማደርግበት ጊዜ* አሥር ሴቶች በአንድ ምድጃ ብቻ ዳቦ ይጋግሩላችኋል፤ ዳቦውንም እየመዘኑ ያከፋፍሏችኋል፤+ እናንተም ትበላላችሁ፤ ነገር ግን አትጠግቡም።+ 27  “‘ይሁን እንጂ በዚህም እኔን ለመስማት ፈቃደኛ ካልሆናችሁና እኔን መቃወማችሁን ከገፋችሁበት 28  በኃይል እቃወማችኋለሁ፤+ እኔ ራሴም ለኃጢአታችሁ ሰባት እጥፍ እቀጣችኋለሁ። 29  በመሆኑም የወንድ ልጆቻችሁን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የሴት ልጆቻችሁንም ሥጋ ትበላላችሁ።+ 30  በከፍታ ቦታዎች ላይ ያሉትን ቅዱስ ስፍራዎቻችሁን+ አጠፋለሁ፤ የዕጣን ማጨሻዎቻችሁንም አስወግዳለሁ፤ በድናችሁንም አስጸያፊ በሆኑት ጣዖቶቻችሁ* በድን ላይ እከምረዋለሁ፤+ እኔም ተጸይፌያችሁ ከእናንተ ዞር እላለሁ።*+ 31  ከተሞቻችሁን ለሰይፍ አሳልፌ እሰጣለሁ፤+ መቅደሶቻችሁንም ባዶ አደርጋቸዋለሁ፤ የመሥዋዕቶቻችሁን ደስ የሚያሰኝ* መዓዛ አላሸትም። 32  እኔ ራሴ ምድሪቱን ባድማ አደርጋታለሁ፤+ በዚያ የሚኖሩ ጠላቶቻችሁም በመደነቅ ይመለከቷታል።+ 33  እናንተንም በብሔራት መካከል እበትናችኋለሁ፤+ ሰይፍም መዝዤ አሳድዳችኋለሁ፤+ ምድራችሁ ባድማ ትሆናለች፤+ ከተሞቻችሁም ይፈራርሳሉ። 34  “‘በጠላቶቻችሁ ምድር ሆናችሁ ምድሪቱ ባድማ ሆና በምትቆይባቸው ጊዜያት ሁሉ የሰንበት ዕዳዋን ትከፍላለች። በዚያን ጊዜ ምድሪቱ የሰንበት ዕዳዋን መክፈል ስላለባት ታርፋለች።*+ 35  ምድሪቱ ትኖሩባት በነበረው ጊዜ በሰንበታችሁ ወቅት ስላላረፈች ባድማ ሆና በምትቆይባቸው ጊዜያት ሁሉ ታርፋለች። 36  “‘ከእናንተ መካከል በሕይወት የሚተርፉትም+ በጠላቶቻቸው ምድር ልባቸው ተስፋ እንዲቆርጥ አደርጋለሁ፤ የቅጠል ኮሽታ እንኳ ያስበረግጋቸዋል፤ ከሰይፍ እንደሚሸሽ ሰው ይፈረጥጣሉ፤ ማንም ሳያሳድዳቸው ይወድቃሉ።+ 37  ከሰይፍ እንደሚሸሹ ሰዎች እነሱም ማንም ሳያሳድዳቸው እርስ በርሳቸው እየተደነቃቀፉ ይወድቃሉ። እናንተም ጠላቶቻችሁን መቋቋም ይሳናችኋል።+ 38  በብሔራት መካከል ትጠፋላችሁ፤+ የጠላቶቻችሁም ምድር ትበላችኋለች። 39  ከእናንተ መካከል የሚተርፉትም በሠሩት ስህተት የተነሳ በጠላቶቻችሁ ምድር ይበሰብሳሉ።+ አዎ፣ በአባቶቻቸው ስህተት የተነሳ ይበሰብሳሉ።+ 40  ከዚያም የገዛ ራሳቸውን ስህተት እንዲሁም አባቶቻቸው የፈጸሙትን ስህተትና ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ይናዘዛሉ፤+ እንዲሁም እኔን በመቃወም ታማኝ ሳይሆኑ መቅረታቸውን አምነው ይቀበላሉ።+ 41  እኔም እነሱን ወደ ጠላቶቻቸው ምድር በማምጣት+ እቃወማቸዋለሁ።+ “‘ምናልባትም ያልተገረዘው* ልባቸው በዚያ ጊዜ ትሑት ይሆናል፤+ የስህተታቸውንም ዋጋ ይከፍላሉ። 42  እኔም ከያዕቆብ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳንና ከይስሐቅ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስባለሁ፤+ እንዲሁም ከአብርሃም ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ፤+ ምድሪቱንም አስባለሁ። 43  እነሱም ምድሪቱን ትተዋት በሄዱበት ጊዜ ምድሪቱ የሰንበት ዕዳዋን ትከፍላለች፤+ ያለእነሱም ባድማ ሆና ትቆያለች፤ እነሱም ድንጋጌዎቼን ችላ ስላሉና ደንቦቼን ስለተጸየፉ*+ የስህተታቸውን ዋጋ ይከፍላሉ። 44  ይህ ሁሉ ቢሆንም ግን በጠላቶቻቸው ምድር በሚቆዩበት ጊዜ ሁሉ እርግፍ አድርጌ አልተዋቸውም፤+ ፈጽሜ እስካጠፋቸውም ድረስ አልጥላቸውም፤ እንዲህ ባደርግ ከእነሱ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ማፍረስ ይሆንብኛል፤+ ምክንያቱም እኔ አምላካቸው ይሖዋ ነኝ። 45  አምላካቸው መሆኔን አስመሠክር ዘንድ ብሔራት በዓይናቸው እያዩ ከግብፅ ምድር ካወጣኋቸው አባቶቻቸው+ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን ስለ እነሱ ስል አስባለሁ።+ እኔ ይሖዋ ነኝ።’” 46  ይሖዋ በሲና ተራራ ላይ በሙሴ አማካኝነት በራሱና በእስራኤላውያን መካከል ያስቀመጣቸው ሥርዓቶች፣ ድንጋጌዎችና ሕጎች እነዚህ ናቸው።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

ወይም “አድናቆት።” ቃል በቃል “ፍርሃት።”
ቃል በቃል “ወደ እናንተ ዞር እላለሁ።”
ወይም “ነፍሴም አትተዋችሁም።”
ቃል በቃል “ቀጥ ብላችሁ።”
ወይም “ነፍሳችሁ ትእዛዛቴን በሙሉ ላለመፈጸም ድንጋጌዎቼን የምትጸየፍ።”
ወይም “ነፍሳችሁ።”
ቃል በቃል “የዳቦ በትሮቻችሁን በምሰብርበት ጊዜ።” ዳቦ ለማስቀመጥ የሚያገለግሉ በትሮችን የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም።
እዚህ ላይ የገባው የዕብራይስጥ ቃል “ፋንድያ” ከሚለው ቃል ጋር ዝምድና ሊኖረው የሚችል ሲሆን ንቀትን ለማመልከት ተሠርቶበታል።
ወይም “ነፍሴ ተጸይፋችሁ ከእናንተ ዞር ትላለች።”
ወይም “የሚያረጋጋ፤ የሚያበርድ።” ቃል በቃል “እረፍት የሚሰጥ።”
ወይም “ሰንበትን ታከብራለች።”
ወይም “ግትር የሆነው።”
ወይም “ነፍሳቸው ደንቦቼን ስለተጸየፈች።”