ዘፍጥረት 6:1-22

  • የአምላክ ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች አገቡ (1-3)

  • ኔፍሊሞች ተወለዱ (4)

  • ይሖዋ በሰው ልጆች ክፋት አዘነ (5-8)

  • ኖኅ መርከብ እንዲሠራ ተልእኮ ተሰጠው (9-16)

  • አምላክ የጥፋት ውኃ እንደሚመጣ ተናገረ (17-22)

6  ሰዎች በምድር ላይ ቁጥራቸው እየጨመረ ሲሄድ ሴቶች ልጆችን ወለዱ፤ 2  የእውነተኛው አምላክ ልጆችም*+ የሰዎች ሴቶች ልጆች ውብ እንደሆኑ አስተዋሉ። በመሆኑም የመረጧቸውን ሁሉ ለራሳቸው ሚስቶች አድርገው ወሰዱ። 3  ከዚያም ይሖዋ “ሰው ሥጋ ስለሆነ* መንፈሴ ሰውን ለዘላለም አይታገሥም።+ በመሆኑም ዘመኑ 120 ዓመት ይሆናል”+ አለ። 4  በዚያ ዘመንም ሆነ ከዚያ በኋላ ኔፍሊም* በምድር ላይ ነበሩ። በዚያ ጊዜም የእውነተኛው አምላክ ልጆች ከሰዎች ሴቶች ልጆች ጋር ግንኙነት ፈጸሙ፤ ሴቶቹም ወንዶች ልጆችን ወለዱላቸው። እነሱም በጥንት ዘመን በኃያልነታቸው ዝና ያተረፉ ሰዎች ነበሩ። 5  በዚህም የተነሳ ይሖዋ የሰው ልጅ ክፋት በምድር ላይ እንደበዛና የልቡም ሐሳብ ሁሉ ምንጊዜም ወደ መጥፎ ብቻ ያዘነበለ+ እንደሆነ ተመለከተ። 6  ይሖዋም ሰዎችን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤* ልቡም አዘነ።+ 7  በመሆኑም ይሖዋ እንዲህ አለ፦ “የፈጠርኳቸውን ሰዎች ከምድር ገጽ ጠራርጌ አጠፋለሁ፤ ሰውን ጨምሮ የቤት እንስሳትን እንዲሁም መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳትንና በሰማያት ላይ የሚበርሩ ፍጥረታትን አጠፋለሁ፤ ምክንያቱም እነሱን በመፍጠሬ ተጸጽቻለሁ።” 8  ኖኅ ግን በይሖዋ ፊት ሞገስ አገኘ። 9  የኖኅ ታሪክ ይህ ነው። ኖኅ ጻድቅ ሰው ነበር።+ በዘመኑ* ከነበሩት ሰዎች መካከል እሱ እንከን* የሌለበት ሰው ነበር። ኖኅ ከእውነተኛው አምላክ ጋር ይሄድ ነበር።+ 10  ኖኅ ከጊዜ በኋላ ሴም፣ ካምና ያፌት+ የተባሉ ሦስት ወንዶች ልጆች ወለደ። 11  ይሁንና ምድር በእውነተኛው አምላክ ፊት ተበላሽታ ነበር፤ እንዲሁም በዓመፅ ተሞልታ ነበር። 12  አዎ፣ አምላክ ምድርን ተመለከተ፤ ምድርም ተበላሽታ ነበር፤+ ሰው* ሁሉ በምድር ላይ መንገዱን አበላሽቶ ነበር።+ 13  ከዚህ በኋላ አምላክ ኖኅን እንዲህ አለው፦ “በእነሱ የተነሳ ምድር በዓመፅ ስለተሞላች ሥጋን ሁሉ ለማጥፋት ወስኛለሁ፤ ስለሆነም እነሱን ከምድር ጋር አጠፋቸዋለሁ።+ 14  አንተ ከጎፈር እንጨት ለራስህ መርከብ* ሥራ።+ በመርከቡም ውስጥ የተለያዩ ክፍሎችን ሥራ፤ እንዲሁም መርከቡን ከውስጥም ሆነ ከውጭ ቅጥራን*+ ለቅልቀው። 15  መርከቡንም የምትሠራው እንደሚከተለው ነው፦ የመርከቡ ርዝመት 300 ክንድ፣* ወርዱ 50 ክንድ እንዲሁም ከፍታው 30 ክንድ ይሁን። 16  በመርከቡም ላይ ከጣሪያው ሥር አንድ ክንድ ቁመት ያለው ብርሃን ማስገቢያ የሚሆን መስኮት* ሥራ፤ የመርከቡንም በር በጎኑ በኩል አድርግ፤+ መርከቡም ምድር ቤት እንዲሁም አንደኛና ሁለተኛ ፎቅ ይኑረው። 17  “እኔ ደግሞ ከሰማያት በታች የሕይወት እስትንፋስ* ያለውን ሥጋ ሁሉ ለማጥፋት በምድር ላይ የጥፋት ውኃ+ አመጣለሁ። በምድር ላይ ያለ ነገር ሁሉ ይጠፋል።+ 18  እኔም ከአንተ ጋር ቃል ኪዳኔን እመሠርታለሁ፤ አንተም ወደ መርከቡ መግባት አለብህ፤ አንተ፣ ከአንተም ጋር ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና የልጆችህ ሚስቶች ወደ መርከቡ መግባት ይኖርባችኋል።+ 19  ከአንተ ጋር በሕይወት እንዲተርፉ ከሁሉም ዓይነት ሕያው ፍጡር+ ተባዕትና እንስት እያደረግክ ሁለት ሁለት ወደ መርከቡ አስገባ፤+ 20  በሕይወት እንዲተርፉ የሚበርሩ ፍጥረታት እንደየወገናቸው፣ የቤት እንስሳት እንደየወገናቸው እንዲሁም በምድር ላይ ያሉ መሬት ለመሬት የሚሄዱ እንስሳት ሁሉ እንደየወገናቸው ሁለት ሁለት እየሆኑ ከአንተ ጋር ይግቡ።+ 21  ለአንተም ሆነ ለእንስሳቱ ምግብ እንዲሆን ማንኛውንም ዓይነት ምግብ+ ሰብስበህ ይዘህ ትገባለህ።” 22  ኖኅም አምላክ ያዘዘውን ሁሉ በተባለው መሠረት አከናወነ። ልክ እንደዚሁ አደረገ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

የአምላክ ልጆች የሆኑትን መላእክት የሚያመለክት የዕብራይስጥ ዘይቤያዊ አነጋገር ነው።
ወይም “የሥጋውን ፈቃድ ስለሚፈጽም።”
“የሚያፈርጡ” ይኸውም ሌሎችን እያነሱ የሚያፈርጡ ማለት ሳይሆን አይቀርም። የቃላት መፍቻውን ተመልከት።
ወይም “ተከፋ።”
ቃል በቃል “በእሱ ትውልድ።”
ወይም “ነቀፋ።”
ቃል በቃል “ሥጋ።”
ቃል በቃል “ትልቅ ሣጥን።” ትልቅ ጀልባ።
ወይም “ሬንጅ።”
አንድ ክንድ 44.5 ሴንቲ ሜትር ነው። ከተጨማሪው መረጃ ላይ ለ14ን ተመልከት።
የዕብራይስጡ ቃል “ጾሃር” ነው። ይህ ቃል ከብርሃን ማስገቢያ ቀዳዳ ወይም መስኮት ይልቅ አንድ ክንድ ተዳፋት የሆነን ጣሪያ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።
ወይም “የሕይወት መንፈስ።”