ለቆሮንቶስ ሰዎች የተጻፈ የመጀመሪያው ደብዳቤ 12:1-31

  • የመንፈስ ስጦታዎች (1-11)

  • አንድ አካል፣ ብዙ የአካል ክፍሎች (12-31)

12  ወንድሞች፣ አሁን ደግሞ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች+ በሚገባ እንድታውቁ እፈልጋለሁ።  አሕዛብ* በነበራችሁበት ጊዜ ድምፅ የሌላቸው ጣዖቶች+ ካሳደሩባችሁ ተጽዕኖ የተነሳ ወደመሯችሁ ቦታ ሁሉ በመሄድ እነሱን ተከትላችሁ ትባዝኑ ነበር።  ስለዚህ ይህን እንድታውቁ እወዳለሁ፦ በአምላክ መንፈስ ተመርቶ “ኢየሱስ የተረገመ ነው!” የሚል ማንም የለም፤ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ካልሆነ በቀር ማንም “ኢየሱስ ጌታ ነው!” ብሎ ሊናገር አይችልም።+  ልዩ ልዩ ስጦታዎች አሉ፤ ምንጩ ግን ያው መንፈስ ነው፤+  ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፤+ ሁሉም አገልግሎት የሚቀርበው ግን ለአንድ ጌታ ነው፤  በተጨማሪም ልዩ ልዩ ሥራዎች* አሉ፤ ሆኖም ሁሉም ሰዎች እነዚህን ሁሉ ነገሮች እንዲያከናውኑ የሚያስችለው አንድ አምላክ ብቻ ነው።+  ይሁን እንጂ መንፈስ በእያንዳንዱ ሰው አማካኝነት ጠቃሚ ለሆነ ዓላማ ይገለጣል።+  ለአንዱ በመንፈስ አማካኝነት በጥበብ የመናገር ችሎታ* ይሰጠዋልና፤ ለሌላው ደግሞ በዚያው መንፈስ በእውቀት የመናገር ችሎታ ይሰጠዋል፤  ለሌላው በዚያው መንፈስ እምነት ይሰጠዋል፤+ ለሌላው ደግሞ በዚያው መንፈስ፣ የመፈወስ ስጦታ ይሰጠዋል፤+ 10  እንዲሁም ለሌላው ተአምራት የመሥራት፣+ ለሌላው ትንቢት የመናገር፣ ለሌላው በመንፈስ መሪነት የተነገረን ቃል የመረዳት፣+ ለሌላው በተለያዩ ልሳኖች* የመናገር፣+ ለሌላው ደግሞ ልሳኖችን የመተርጎም ችሎታ ይሰጠዋል።+ 11  ሆኖም ለእያንዳንዱ በግለሰብ ደረጃ እነዚህን ስጦታዎች እንደፈቀደ በማከፋፈል እነዚህን ሁሉ ነገሮች የሚያከናውነው ያው አንድ መንፈስ ነው። 12  አካል አንድ ቢሆንም ብዙ የአካል ክፍሎች እንዳሉትና የዚህ አካል ክፍሎች በሙሉ ብዙ ቢሆኑም አንድ አካል+ እንደሆኑ ሁሉ ክርስቶስም እንደዚሁ ነው። 13  አይሁዳውያንም ሆን ግሪካውያን፣ ባሪያዎችም ሆን ነፃ ሰዎች ሁላችንም አንድ አካል ለመሆን በአንድ መንፈስ ተጠምቀናልና፤ እንዲሁም ሁላችንም አንድ መንፈስ እንድንጠጣ ተሰጥቶናል። 14  አካል በአንድ ብቻ ሳይሆን በብዙ የአካል ክፍሎች የተገነባ ነውና።+ 15  እግር “እኔ እጅ ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ አይቀርም። 16  እንዲሁም ጆሮ “እኔ ዓይን ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ አይቀርም። 17  አካል በሙሉ ዓይን ቢሆን ኖሮ እንዴት መስማት ይቻል ነበር? አካል በሙሉ ጆሮ ቢሆን ኖሮስ እንዴት ማሽተት ይቻል ነበር? 18  ሆኖም አምላክ እያንዳንዱን የአካል ክፍል እሱ በፈለገው ቦታ መድቦታል። 19  የአካል ክፍሎች ሁሉ አንድ ዓይነት ቢሆኑ ኖሮ ሙሉ አካል ከየት ይገኝ ነበር? 20  አሁን ግን የአካል ክፍሎች ብዙ ቢሆኑም አካል ግን አንድ ነው። 21  ዓይን እጅን “አንተ አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም፤ ወይም ደግሞ ራስ እግርን “አንተ አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም። 22  እንዲያውም ደካማ የሚመስሉት የአካል ክፍሎች በጣም አስፈላጊ ናቸው፤ 23  እምብዛም ክብር የላቸውም ብለን የምናስባቸውን የአካል ክፍሎች የበለጠ ክብር እንሰጣቸዋለን፤+ በመሆኑም የምናፍርባቸውን የአካል ክፍሎች ይበልጥ በክብር እንይዛቸዋለን፤ 24  በአንጻሩ ደግሞ የሚያምሩት የአካል ክፍሎቻችን ምንም አያስፈልጋቸውም። ይሁንና አምላክ ክብር የሚጎድለውን የአካል ክፍል ታላቅ ክብር በማልበስ አካልን ገንብቷል፤ 25  ይህን ያደረገው በአካል መካከል ክፍፍል እንዳይኖር፣ ከዚህ ይልቅ የአካል ክፍሎች በእኩል ደረጃ አንዳቸው ለሌላው አሳቢነት እንዲያሳዩ ነው።+ 26  አንድ የአካል ክፍል ቢሠቃይ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይሠቃያሉ፤+ ወይም አንድ የአካል ክፍል ክብር ቢያገኝ ሌሎቹ የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረውት ይደሰታሉ።+ 27  እንግዲህ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤+ እያንዳንዳችሁም በግለሰብ ደረጃ የአካሉ ክፍል ናችሁ።+ 28  አምላክ የተለያዩ የአካል ክፍሎችን ይኸውም አንደኛ ሐዋርያትን፣+ ሁለተኛ ነቢያትን፣+ ሦስተኛ አስተማሪዎችን፣+ ከዚያም ተአምር የሚፈጽሙትን፣+ ከዚያም የመፈወስ ስጦታ ያላቸውን፣+ ጠቃሚ አገልግሎት የሚያከናውኑትን፣ የመምራት ችሎታ ያላቸውንና+ በተለያዩ ልሳኖች የሚናገሩትን+ በጉባኤ ውስጥ መድቧል። 29  ሁሉ ሐዋርያት ናቸው? ሁሉስ ነቢያት ናቸው? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸው? ሁሉስ ተአምር ይሠራሉ? 30  ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸው? ሁሉስ በልሳን ይናገራሉ?+ ሁሉስ ተርጓሚዎች ናቸው?+ 31  ይሁንና ብልጫ ያላቸውን ስጦታዎች ለማግኘት ጥረት* ማድረጋችሁን ቀጥሉ።+ ደግሞም ከሁሉ የላቀውን መንገድ አሳያችኋለሁ።+

የግርጌ ማስታወሻዎች

አማኝ እንዳልነበሩ ያመለክታል።
ወይም “አሠራሮች።”
ወይም “ጥበብ የሚንጸባረቅበት መልእክት።”
ወይም “ቋንቋዎች።”
ወይም “ቅንዓት የተሞላበት ጥረት።”