አንደኛ ነገሥት 4:1-34
4 ንጉሥ ሰለሞን መላውን እስራኤል ይገዛ ነበር።+
2 ከፍተኛ ባለሥልጣናቱ* እነዚህ ነበሩ፦ የሳዶቅ+ ልጅ አዛርያስ ካህን ነበር፤
3 የሺሻ ልጆች ኤሌሆሬፍና አኪያህ ጸሐፊዎች ነበሩ፤+ የአሂሉድ ልጅ ኢዮሳፍጥ+ ታሪክ ጸሐፊ ነበር፤
4 የዮዳሄ ልጅ በናያህ+ የሠራዊቱ አዛዥ ነበር፤ ሳዶቅና አብያታር+ ካህናት ነበሩ፤
5 የናታን+ ልጅ አዛርያስ የአስተዳዳሪዎቹ ኃላፊ ነበር፤ የናታን ልጅ ዛቡድ ካህንና የንጉሡ ወዳጅ ነበር፤+
6 አሂሻር የቤቱ አዛዥ ነበር፤ የአብዳ ልጅ አዶኒራም+ የግዳጅ ሥራ እንዲሠሩ በተመለመሉት+ ላይ አዛዥ ነበር።
7 ሰለሞን በመላው እስራኤል ላይ የተሾሙ ለንጉሡና ለቤተሰቡ ቀለብ የሚያቀርቡ 12 አስተዳዳሪዎች ነበሩት። እያንዳንዳቸውም በዓመት ውስጥ ለአንድ ወር ቀለብ የማቅረብ ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር።+
8 ስማቸውም የሚከተለው ነው፦ በኤፍሬም ተራራማ አካባቢ የሁር ልጅ፣
9 በማቃጽ፣ በሻአልቢም፣+ በቤትሼሜሽ እና በኤሎንቤትሃናን የዴቀር ልጅ፣
10 በአሩቦት የሄሴድ ልጅ (ሶኮህ እና የሄፌር ምድር በሙሉ በሥሩ ነበሩ)፣
11 በዶር ሸንተረር በሙሉ የአቢናዳብ ልጅ (እሱም የሰለሞንን ልጅ ጣፋትን አግብቶ ነበር)፣
12 በታአናክ እና በመጊዶ+ እንዲሁም ከኢይዝራኤል በታች ከጸረታን አጠገብ በሚገኘው በቤትሼን+ በሙሉና ከቤትሼን አንስቶ በዮቅመአም+ እስከሚገኘው እስከ አቤልምሆላ ድረስ የአሂሉድ ልጅ ባአና፣
13 በራሞትጊልያድ+ የጌቤር ልጅ (በጊልያድ+ የሚገኙት የምናሴ ልጅ የያኢር+ የድንኳን ሰፈሮች በእሱ ሥር ነበሩ፤ እንዲሁም በባሳን+ የሚገኘው የአርጎብ ክልል+ ይኸውም በቅጥር የታጠሩና የመዳብ መቀርቀሪያ ያላቸው 60 ትላልቅ ከተሞች በእሱ ሥር ነበሩ)፣
14 በማሃናይም+ የኢዶ ልጅ አሂናዳብ፣
15 በንፍታሌም አኪማዓስ (እሱም ሌላኛዋን የሰለሞንን ልጅ፣ ባሴማትን አግብቶ ነበር)፣
16 በአሴርና በበዓሎት የኩሲ ልጅ ባአና፣
17 በይሳኮር የፓሩህ ልጅ ኢዮሳፍጥ፣
18 በቢንያም+ የኤላ ልጅ ሺምአይ+
19 እንዲሁም የአሞራውያን ንጉሥ የሲሖን+ እና የባሳን ንጉሥ የኦግ+ ምድር በሆነው በጊልያድ+ ምድር የዖሪ ልጅ ጌቤር። በተጨማሪም በምድሪቱ አስተዳዳሪዎች ሁሉ ላይ የተሾመ አንድ አስተዳዳሪ ነበር።
20 ይሁዳና እስራኤል ከብዛታቸው የተነሳ እንደ ባሕር አሸዋ ነበሩ፤+ እነሱም ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ይደሰቱ ነበር።+
21 ሰለሞን ከወንዙ*+ አንስቶ እስከ ፍልስጤማውያን ምድርና እስከ ግብፅ ወሰን ድረስ ባሉት መንግሥታት ሁሉ ላይ ገዛ። እነሱም በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ግብር ያመጡለት እንዲሁም ያገለግሉት ነበር።+
22 ሰለሞን በየቀኑ የሚገባለት ቀለብ ይህ ነበር፦ 30 የቆሮስ መስፈሪያ* የላመ ዱቄት፣ 60 የቆሮስ መስፈሪያ ዱቄት
23 እንዲሁም 10 ቅልብ ከብቶች፣ ከግጦሽ የመጡ 20 ከብቶች፣ 100 በጎችና የተወሰኑ የርኤም* ዝርያዎች፣ የሜዳ ፍየሎችና የሰቡ ወፎች።
24 እሱም ከወንዙ ወዲህ ያሉትን ነገሥታት ሁሉ ጨምሮ ከቲፍሳ አንስቶ እስከ ጋዛ+ ድረስ የሚገኙትን ከወንዙ+ ወዲህ* ያሉትን አካባቢዎች በሙሉ ተቆጣጥሮ ነበር፤ በዙሪያው ባለው አካባቢ ሁሉ ሰላም ሰፍኖለት ነበር።+
25 በሰለሞን ዘመን ከዳን አንስቶ እስከ ቤርሳቤህ ድረስ በይሁዳና በእስራኤል የሚገኝ እያንዳንዱ ሰው ከገዛ ወይኑና ከበለስ ዛፉ ሥር ያለስጋት ይኖር ነበር።
26 ሰለሞን ሠረገሎቹን ለሚጎትቱት ፈረሶች የሚሆኑ 4,000* ጋጣዎችና 12,000 ፈረሶች* ነበሩት።+
27 እነዚህ አስተዳዳሪዎች ለንጉሥ ሰለሞንና ከንጉሥ ሰለሞን ማዕድ ለሚመገቡት ሁሉ ቀለብ ያቀርቡ ነበር። እያንዳንዳቸውም በተመደበላቸው ወር የሚጠበቅባቸውን ያቀርቡ የነበረ ሲሆን ምንም ነገር እንዳይጓደል ጥንቃቄ ያደርጉ ነበር።+
28 እንዲሁም እያንዳንዳቸው በተመደበላቸው ድርሻ መሠረት ለፈረሶቹና ለሰንጋ ፈረሶቹ የሚሆነውን ገብስና ገለባ ወደተፈለገው ቦታ ያመጡ ነበር።
29 አምላክም ለሰለሞን እጅግ ታላቅ ጥበብና ማስተዋል እንዲሁም በባሕር ዳርቻ ላይ እንዳለ አሸዋ፣ ሰፊ ልብ* ሰጠው።+
30 የሰለሞን ጥበብ ከምሥራቅ ሰዎች ሁሉ ጥበብና ከግብፅ ሁሉ ጥበብ የላቀ ነበር።+
31 እሱም ከማንኛውም ሰው ይልቅ ጥበበኛ ነበር፤ ከዛራዊው ከኤታን+ እንዲሁም የማሆል ልጆች ከሆኑት ከሄማን፣+ ከካልኮል+ እና ከዳርዳ ይልቅ ጥበበኛ ነበር፤ ዝናውም በዙሪያው ባሉት ብሔራት ሁሉ ዘንድ ተሰማ።+
32 እሱም 3,000 ምሳሌዎችን+ አቀናበረ፤* የመዝሙሮቹም+ ብዛት 1,005 ነበር።
33 በሊባኖስ ከሚገኘው አርዘ ሊባኖስ አንስቶ በቅጥር ላይ እስከሚበቅለው ሂሶጵ+ ድረስ ስለ ዛፎች ተናግሯል፤ እንዲሁም ስለ እንስሳት፣+ ስለ አእዋፍ፣*+ መሬት ለመሬት ስለሚሄዱ ፍጥረታትና*+ ስለ ዓሣዎች ተናግሯል።
34 ስለ እሱ ጥበብ ሲወራ የሰሙ በተለያየ የምድር ክፍል የሚገኙ ነገሥታትን ጨምሮ ከልዩ ልዩ ብሔራት፣ ሰዎች የሰለሞንን ጥበብ ለመስማት ይመጡ ነበር።+
የግርጌ ማስታወሻዎች
^ ወይም “መኳንንቱ።”
^ ኤፍራጥስን ያመለክታል።
^ ቅርንጫፍ የሚመስሉ ቀንዶች ያሉት አጥቢ እንስሳ፤ ከአጋዘን ጋር ይመሳሰላል።
^ ከኤፍራጥስ በስተ ምዕራብ ያለውን ያመለክታል።
^ ይህ አኃዝ በእጅ በተጻፉ አንዳንድ ጥንታዊ ቅጂዎችና በሌላ ቦታ ላይ በሚገኘው ተመሳሳይ ዘገባ ላይ ይገኛል። ሌሎች ጥንታዊ ቅጂዎች ደግሞ 40,000 ይላሉ።
^ ወይም “ፈረሰኞች።”
^ ወይም “አስተዋይ ልብ።”
^ ወይም “ተናገረ።”
^ ወይም “በራሪ ፍጥረታት።”
^ በምድር ላይ የሚሳቡ እንስሳትንና ጥቃቅን ነፍሳትን የሚጨምር ሊሆን ይችላል።