አምላክን የሚታዘዙ ሰዎች የሚያገኟቸው በረከቶች
የአምላክን ትእዛዛት የምንፈጽም ከሆነ የእሱን በረከት እንደምናገኝ ነቢዩ ሙሴ ተናግሯል። (ዘዳግም 10:13፤ 11:27) አምላክን የምንታዘዘው እንዳይቀጣን ፈርተን አይደለም። አምላክን የምንታዘዘው ግሩም በሆኑ ባሕርያቱ የተነሳ ስለምንወደውና እሱን የሚያሳዝን ነገር ማድረግ ስለማንፈልግ ነው። “አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነው።”—1 ዮሐንስ 5:3
ይሁንና አምላክን መታዘዝ በረከት የሚያስገኝልን እንዴት ነው? እስቲ ሁለት መንገዶችን እንመልከት።
1. አምላክን መታዘዝ ጥበበኛ ያደርገናል
“የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ፣ ልትሄድበትም በሚገባህ መንገድ የምመራህ እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።”—ኢሳይያስ 48:17
ፈጣሪያችን ይሖዋ አምላክ በሚገባ ያውቀናል፤ የሚያስፈልገንን መመሪያም ይሰጠናል። አምላክ ባስተማረን ነገር ላይ የተመሠረተ ጥሩ ውሳኔ ማድረግ ከፈለግን፣ አምላክ ስለሚጠብቅብን ነገር ከቅዱሳን መጻሕፍት መማርና የተማርነውን ነገር ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል።
2. አምላክን መታዘዝ ደስተኛ ያደርገናል
“ደስተኞችስ የአምላክን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው!”—ሉቃስ 11:28
በዛሬው ጊዜ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክን ቃል በመታዘዛቸው እውነተኛ ደስታ አግኝተዋል። በስፔን የሚኖርን አንድ ሰው እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህ ሰው ግልፍተኛ የነበረ ሲሆን ሚስቱን ጨምሮ ሌሎች ሰዎችን የሚይዘው አክብሮት በጎደለው መንገድ ነበር። አንድ ቀን፣ ነቢዩ ሙሴ በጻፈው መጽሐፍ ላይ የያዕቆብ ልጅ የሆነው ዮሴፍ ስላሳየው ግሩም ባሕርይ አነበበ። ዮሴፍ በባርነት ተሽጦ በግፍ ቢታሰርም ልዝብ፣ ሰላማዊና ይቅር ባይ ሰው ነበር። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 37-45) በስፔን የሚኖረው ሰው እንዲህ ብሏል፦ “ዮሴፍ ስለተወው ምሳሌ ማሰቤ ልዝብና ደግ እንድሆን እንዲሁም ራሴን እንድገዛ አነሳሳኝ። በዚህም የተነሳ አሁን በሕይወቴ ደስተኛ መሆን ችያለሁ።”
ቅዱሳን መጻሕፍት ከሌሎች ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ግንኙነት ተጨማሪ መመሪያዎች ይሰጡናል። በቀጣዩ ርዕስ ላይ ስለዚህ ጉዳይ ይበልጥ እንመለከታለን።