ፈጣሪያችን ያዘጋጃቸውን ዘላለማዊ በረከቶች ማግኘት ትችላለህ
አምላክ ለነቢዩ አብርሃም ከዘሮቹ መካከል አንዱ ‘ለምድር ብሔራት ሁሉ’ በረከት እንደሚያመጣ ቃል ገብቶለት ነበር። (ዘፍጥረት 22:18) ታዲያ ይህ የአብርሃም ዘር ማን ነው?
ወደ 2,000 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት፣ አምላክ የአብርሃም ዘር ለሆነው ለኢየሱስ ታላላቅ ተአምራትን የመፈጸም ኃይል ሰጥቶት ነበር። እነዚህ ተአምራት፣ አምላክ ለአብርሃም ቃል በገባው መሠረት ብሔራት የሚባረኩት በኢየሱስ በኩል እንደሆነ ይጠቁማሉ።—ገላትያ 3:14
ኢየሱስ የፈጸማቸው ተአምራት፣ ለሰው ልጆች በረከት ለማምጣት በአምላክ የተመረጠው እሱ መሆኑን አረጋግጠዋል፤ በተጨማሪም አምላክ በኢየሱስ ተጠቅሞ የሰው ልጆችን ለዘላለም የሚባርከው በምን መንገድ እንደሆነ አሳይተዋል። ኢየሱስ ያከናወናቸው ተአምራት የእሱን ግሩም ባሕርያት የሚያሳዩት እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
አዛኝ—ኢየሱስ የታመሙትን ፈውሷል።
በሥጋ ደዌ የተያዘ አንድ ሰው “ብትፈልግ እኮ ልታነጻኝ ትችላለህ” ብሎ ኢየሱስን ለምኖት ነበር። ኢየሱስም ሰውየውን ዳሰሰውና “እፈልጋለሁ! ንጻ” አለው። ሰውየውም ወዲያውኑ የሥጋ ደዌው ለቀቀው።—ማርቆስ 1:40-42
ለጋስ—ኢየሱስ የተራቡትን መግቧል።
ኢየሱስ ሰዎች እንዲራቡ አይፈልግም ነበር። ጥቂት ዳቦና ዓሣ ተጠቅሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተአምር የመገበባቸው ወቅቶች ነበሩ። (ማቴዎስ 14:17-21፤ 15:32-38) ሁሉም በልተው ጠግበዋል፤ እንዲያውም ብዙ ምግብ ተርፎ ነበር።
ሩኅሩኅ—ኢየሱስ የሞቱትን አስነስቷል።
ጧሪ ቀባሪ የሚሆናትን አንድ ልጇን በሞት ላጣችው መበለት ‘በጣም ስላዘነላት’ ልጇን ከሞት አስነስቶላታል።—ሉቃስ 7:12-15