መጽሐፍ ቅዱስና የወደፊት ሕይወትህ
እስቲ የሚከተለውን ሁኔታ አስብ፦ አንድ ምሽት፣ ጨለምለም ባለ መንገድ ላይ በእግርህ እየተጓዝክ ነው። ጀምበሯ ከጠለቀች ትንሽ ቢቆይም እንኳ ኃይለኛ ብርሃን የሚሰጥ የእጅ ባትሪ ስለያዝክ ብዙም አልጨነቀህም። የእጅ ባትሪውን ወደ ታች ስታበራው በቅርብህ ያለው ነገር በግልጽ ይታይሃል። ከፊት ለፊትህ ወዳለው አካባቢ ስታበራው ደግሞ ብርሃኑ ከርቀት ያለውን ቦታ ሁሉ ፍንትው አድርጎ ያሳይሃል።
መጽሐፍ ቅዱስ ከእጅ ባትሪ ጋር የሚመሳሰልባቸው መንገዶች አሉ። ቀደም ባሉት ርዕሶች ላይ እንደተመለከትነው የአምላክ ቃል፣ በምሳሌያዊ አነጋገር በቅርባችን ያሉትን ሁኔታዎች ይኸውም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለማስተዋልና ለመፍታት ይረዳናል። ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናገኘው ጥቅም ግን ይህ ብቻ አይደለም። የወደፊቱ ጊዜ ፍንትው ብሎ እንዲታየን ስለሚያደርግ፣ ዘላቂ ደስታና እርካታ የሚያስገኝልንን ጎዳና ከርቀት ለማየትና በዚያ መንገድ ላይ ለመጓዝ ያስችለናል። (መዝሙር 119:105) እንዴት?
መጽሐፍ ቅዱስ ለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ ይሰጠናል፤ ይህን የሚያደርግባቸውን ሁለት መንገዶች እስቲ እንመልከት፦ 1 ሕይወታችን ዓላማ ያለው እንዲሆን ይረዳናል፤ እንዲሁም 2 ከፈጣሪያችን ጋር ዘላለማዊ ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያስተምረናል።
1 ዓላማ ያለው ሕይወት
መጽሐፍ ቅዱስ ችግሮቻችንን ለመቋቋም የሚረዳ አስተማማኝ ምክር ይለግሳል፤ ያም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ማንኛውም ራስ አገዝ መጽሐፍ ልንመለከተው አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ በግል በሚያስጨንቁን ጉዳዮች ላይ ብቻ ከማተኮር ይልቅ ለሌሎችም እንድናስብ ያበረታታናል። ዓላማ ያለው ሕይወት መምራት የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።
“ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። (የሐዋርያት ሥራ 20:35) የተቸገረን ሰው የረዳህበት ጊዜ ትዝ ይልሃል? አሊያም ደግሞ አንድ ወዳጅህ የልቡን አውጥቶ ሲነግርህ ጊዜ ሰጥተህ አዳምጠኸው ታውቃለህ? ታዲያ በዚያ ወቅት አንድን ሰው በማገዝህ ደስ አላለህም?
ከሁሉ የላቀ ደስታ የምናገኘው፣ ብድር እንዲመለስልን ሳንጠብቅ ለሌሎች በምንሰጥበት ጊዜ ነው። አንድ ደራሲ “ብድራት እንዲመለስልህ ሳትጠብቅ ለሌሎች በልግስና የምትሰጥ ከሆነ ከሰጠኸው በላይ ማግኘትህ የማይቀር ነው” ብለዋል። በተለይ ደግሞ ውለታ ለመመለስ አቅም ለሌላቸው ሰዎች ስንሰጥ ወሮታ እናገኛለን። በእርግጥም እንዲህ ስናደርግ ከፈጣሪያችን ጋር አብረን እየሠራን ነው ማለት ይቻላል፤ ምክንያቱም አምላክ ለሌሎች የምናሳየውን ደግነት ለእሱ እንዳበደርነው አድርጎ ይቆጥረዋል። (ምሳሌ 19:17) አምላክ ችግረኛ ለሆኑ ሰዎች የምናሳየውን ደግነት ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ሲሆን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት በመስጠት ወሮታውን እንደሚከፍለን ቃል ገብቷል፤ ይህ በእርግጥም አስደሳች የሆነ ተስፋ ነው!—መዝሙር 37:29፤ ሉቃስ 14:12-14 *
ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን ማምለካችን ሕይወታችን ዓላማ እንዲኖረው እንደሚያደርግ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። የአምላክ ቃል ለፈጣሪያችን የሚገባውን ውዳሴና ክብር እንድንሰጠው እንዲሁም እንድንታዘዘው ያበረታታናል። (መክብብ 12:13፤ ራእይ 4:11) እንዲህ ማድረጋችን አስገራሚ ውጤት ይኖረዋል፤ ይኸውም ፈጣሪያችንን እናስደስታለን። ደግሞም ፈጣሪ “ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው” ብሎናል። (ምሳሌ 27:11) እስቲ አስበው፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን መመሪያዎች ተጠቅመን ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎች ስናደርግ አፍቃሪ የሆነውን የሰማዩ አባታችንን ልብ ደስ እናሰኛለን። ይሖዋ የሚደሰተው ለምንድን ነው? ስለ እኛ ስለሚያስብና የእሱን መመሪያዎች በመከተል ጥቅም እንድናገኝ ስለሚፈልግ ነው። (ኢሳይያስ 48:17, 18) በእርግጥም የአጽናፈ ዓለሙን ሉዓላዊ ጌታ ከማምለክና የእሱን ልብ በሚያስደስት መንገድ ከመኖር ይበልጥ ዓላማ ያለው ሕይወት ለመምራት የሚያስችል ነገር የለም።
2 ከፈጣሪያችን ጋር ወዳጅነት መመሥረት
መጽሐፍ ቅዱስ ከፈጣሪያችን ጋር ወዳጅነት እንድንመሠርትም ያበረታታናል። “ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል” ይላል። (ያዕቆብ 4:8) ሁሉን ቻይ ከሆነው ፈጣሪ ጋር ወዳጅነት መመሥረት መቻላችንን እንጠራጠር ይሆናል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ‘አምላክን ከፈለግነው እንደምናገኘው’ ማረጋገጫ ይሰጠናል፤ ምክንያቱም አምላክ “ከእያንዳንዳችን የራቀ . . . አይደለም።” (የሐዋርያት ሥራ 17:27) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ወዳጅ እንድንሆን የሚሰጠን ምክር ለወደፊት ሕይወታችን በጣም ጠቃሚ ነው። ይህ ሲባል ምን ማለት ነው?
እስቲ አስበው፦ ማናችንም ብንሆን የቱንም ያህል ብንፍጨረጨር የመጨረሻው ጠላታችን የሆነውን ሞትን በራሳችን ጥረት ልናመልጠው አንችልም። (1 ቆሮንቶስ 15:26) አምላክ ግን ዘላለማዊ ነው። እሱ ፈጽሞ አይሞትም፤ ወዳጆቹም ቢሆኑ ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል። “ለዘላለም ተደስታችሁ ኑሩ” የሚለው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ይሖዋ አጥብቀው ለሚሹት ሰዎች ያለውን ምኞት ግሩም አድርጎ ይገልጸዋል።—መዝሙር 22:26
ታዲያ ከአምላክ ጋር ዘላለማዊ ወዳጅነት መመሥረት የምትችለው እንዴት ነው? ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን በማንበብ ስለ እሱ መማርህን ቀጥል። (ዮሐንስ 17:3፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:16) መጽሐፍ ቅዱስን መረዳት እንድትችል የእሱን እርዳታ አጥብቀህ ፈልግ። አምላክ ጥበብ እንዲሰጥህ ‘ያለማሰለስ ከለመንከው’ እንደሚሰጥህ መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጣል። * (ያዕቆብ 1:5) በመጨረሻም የምትማረውን ነገር በሥራ ላይ ለማዋል ጥረት አድርግ፤ ይህም የአምላክ ቃል አሁንም ሆነ ለዘላለም ‘ለእግርህ መብራት ለመንገድህም ብርሃን’ እንዲሆንልህ ያደርጋል።—መዝሙር 119:105
^ አን.8 አምላክ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጠን የገባውን ቃል በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያስተምረናል? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3 ተመልከት።
^ አን.13 የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን በነፃ ያስተምራሉ፤ ይህ ትምህርት ስለ አምላክ ቃል ያለህ እውቀት እያደገ እንዲሄድ ይረዳሃል። የትምህርት ፕሮግራሙ እንዴት እንደሚካሄድ ለማወቅ መጽሐፍ ቅዱስ የምናስጠናው እንዴት ነው? የተባለውን jw.org/am ላይ የሚገኝ ቪዲዮ እንድትመለከት እናበረታታሃለን።
አምላክ ዘላለማዊ ነው፤ ወዳጆቹም ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል