ሞተህ መገላገል ስትመኝ
በሕይወትህ በጣም ከመመረርህ የተነሳ ሞትህን የተመኘህበት ጊዜ አለ? ከሆነ የአድሪያናን ስሜት መረዳት አይከብድህም። አድሪያና ሥር በሰደደ ጭንቀት የምትሠቃይ ከመሆኑም ሌላ ሐዘንና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ይሰማታል። አድሪያና ከባድ የመንፈስ ጭንቀት እንዳለባት በሕክምና ምርመራ ታውቆ ነበር።
ታማሚ የሆኑ አረጋዊ ወላጆቹን ይንከባከብ የነበረውን ካኦሩ የተባለ ጃፓናዊ ሁኔታም ተመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “በወቅቱ በሥራ ቦታ የሚደርስብኝ ከፍተኛ ጫና ከአቅሜ በላይ ሆኖብኝ ነበር። ውሎ አድሮ የምግብ ፍላጎቴ የጠፋ ሲሆን እንቅልፍም እምቢ ይለኝ ጀመር። ስለዚህ ‘ምነው ሞቼ በተገላገልኩ’ ብዬ ማሰብ ጀመርኩ።”
ኦጄቦዲ የተባለ ናይጄሪያዊም እንዲህ ብሏል፦ “ሁልጊዜ በከባድ ሐዘን ከመዋጤ የተነሳ አለቅስ ነበር፤ ስለዚህ ሕይወቴን የማጠፋበት መንገድ መፈለግ ጀመርኩ።” ደግነቱ ኦጄቦዲ፣ ካኦሩና አድሪያና ሕይወታቸውን አላጠፉም። ሆኖም በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጠፋሉ።
እርዳታ ማግኘት የሚቻለው ከየት ነው?
የራሳቸውን ሕይወት ከሚያጠፉት ሰዎች መካከል አብላጫውን ቁጥር የሚይዙት ወንዶች ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል አብዛኞቹ ኃፍረት ስለሚሰማቸው የሌሎችን እርዳታ አይጠይቁም። ኢየሱስ የታመሙ ሰዎች ሐኪም እንደሚያስፈልጋቸው ተናግሯል። (ሉቃስ 5:31) በመሆኑም አንተም ከላይ የተጠቀሰው ዓይነት ስሜት ካለህ እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ አትበል። የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው በርካታ ሰዎች የሕክምና እርዳታ ማግኘታቸው ሕመሙን ለመቋቋም እንደረዳቸው ተገንዝበዋል። ኦጄቦዲ፣ ካኦሩና አድሪያናም የሕክምና ባለሙያ እርዳታ ያገኙ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
ሐኪሞች መድኃኒቶችን በመጠቀም አሊያም ታማሚው ስሜቱን አውጥቶ እንዲናገር በማድረግ የመንፈስ ጭንቀትን ያክማሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሁለቱንም ዘዴዎች አጣምረው ሊጠቀሙ ይችላሉ። በተጨማሪም የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ስሜታቸውን የሚረዱላቸው እንዲሁም ታጋሽና አሳቢ የሆኑ ቤተሰቦቻቸው ብሎም ወዳጆቻቸው ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ማንም ሰው ሊኖረው የሚችለው ከሁሉ የላቀ ወዳጅ ይሖዋ አምላክ ነው፤ እሱ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ይደግፋቸዋል።
ዘላቂ መፍትሔ ይኖረው ይሆን?
በአብዛኛው የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ረዘም ላለ ጊዜ የሚዘልቅ ሕክምና ማግኘት የሚያስፈልጋቸው ከመሆኑም ሌላ በአኗኗራቸው ላይ ማስተካከያ ማድረግ ይኖርባቸዋል። ሆኖም ወደፊት የሚመጣውን አስደሳች ጊዜ በተስፋ መጠባበቅ ይችላሉ፤ ኦጄቦዲን የረዳው እንዲህ ማድረጉ ነው። እንዲህ ብሏል፦ “በምድር ላይ የሚኖር ማንኛውም ሰው ‘ታምሜአለሁ’ የማይልበት ጊዜ እንደሚመጣ የሚናገረውን በኢሳይያስ 33:24 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ፍጻሜ በናፍቆት እጠባበቃለሁ።” አንተም ልክ እንደ ኦጄቦዲ፣ አምላክ “ሥቃይ” የማይኖርበት “አዲስ ምድር” እንደሚያመጣ በሰጠው ተስፋ መጽናናት ትችላለህ። (ራእይ 21:1, 4) ይህ ተስፋ ማንኛውም ዓይነት አእምሯዊና ስሜታዊ ሥቃይ እንደሚወገድ ያረጋግጣል። አሁን የሚያሠቃዩህ መጥፎ ስሜቶች በሙሉ ለዘላለም ይወገዳሉ። እነዚህ ስሜቶች ዳግመኛ “አይታሰቡም፤ ወደ ልብም አይገቡም።”—ኢሳይያስ 65:17