የሽፋኑ ርዕሰ ጉዳይ | የምትወደውን ሰው በሞት ስታጣ
ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ማጽናናት
አንድ ሰው የሚወደውን ሰው በሞት በማጣቱ የተነሳ አጠገብህ ሆኖ ሲያለቅስ ምን ማድረግ እንዳለብህ ግራ ገብቶህ ያውቃል? አንዳንድ ጊዜ ምን ማድረግ ወይም መናገር እንዳለብን ይጠፋናል፤ በመሆኑም ምንም ሳንናገር ወይም ሳናደርግ እንቀራለን። ያም ሆኖ ልናደርጋቸው የምንችላቸው ጠቃሚ ነገሮች አሉ።
ብዙውን ጊዜ በቦታው መገኘትህና የተሰማህን ሐዘን መግለጽህ በራሱ ትልቅ ነገር ነው። በብዙ ባሕሎች ሐዘንተኛውን ማቀፍ ወይም እጁን ጭብጥ ማድረግ አሳቢነት የሚገለጽበት ጥሩ መንገድ ነው። ሐዘንተኛው መናገር ከፈለገ አሳቢነት በሚንጸባረቅበት መንገድ አዳምጠው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሐዘን የደረሰበትን ቤተሰብ የሚጠቅሙ ነገሮችን አከናውን፤ ሐዘንተኛው ማድረግ ያልቻላቸውን ነገሮች ማከናወን ለምሳሌ ምግብ ማብሰል፣ ልጆቹን መንከባከብ ወይም አስፈላጊ ከሆነ ከቀብር ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ማስፈጸም ትችላለህ። እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች ማራኪ ከሆኑ ቃላት የበለጠ ኃይል አላቸው።
ጊዜ እያለፈ ሲሄድ፣ መልካም ባሕርያቱን በማንሳት አሊያም ስላሳለፋችሁት አስደሳች ጊዜ በመጥቀስ ስለ ሟቹ መናገር ትፈልግ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ጭውውቶች ሐዘንተኛውን ፈገግ ሊያሰኙት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከስድስት ዓመት በፊት ባለቤቷን ኢያንን በሞት ያጣችው ፓም “አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ከዚህ በፊት ያልሰማኋቸውን ኢያን ያደረጋቸውን ጥሩ ነገሮች ይነግሩኛል፤ ይህን ስሰማ ልቤ በደስታ ይሞላል” ብላለች።
* ሐዘን የደረሰባቸው በርካታ ሰዎች ለረጅም ጊዜ በሐዘን እንዳይዋጡ የሚያግዛቸውን እንዲህ ያለውን አሳቢነት ከፍ አድርገው ይመለከታሉ።
በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያደረጉ ባለሙያዎች ሪፖርት እንዳደረጉት፣ ሐዘንተኞች የለቅሶው ሰሞን የብዙ ሰዎችን እርዳታ የሚያገኙ ቢሆንም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወዳጆቻቸው በራሳቸው ሕይወት ሲጠመዱ ችላ ይባላሉ። በመሆኑም ሐዘኑ ካለፈ በኋላም ሐዘንተኛውን በየጊዜው ለመጠየቅ ጥረት አድርግ።በወጣትነት ዕድሜ ላይ የምትገኘውን ካኦሪ የተባለች ጃፓናዊት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ካኦሪ እናቷን በሞት ባጣች በዓመት ከሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ታላቅ እህቷ በመሞቷ ከፍተኛ ሐዘን ደርሶባት ነበር። የሚያስደስተው ከታማኝ ወዳጆቿ ቀጣይ የሆነ እርዳታ አግኝታለች። ካኦሪን በዕድሜ በጣም የምትበልጣት ሪትሱኮ የቅርብ ወዳጅ ሆነችላት። ካኦሪ እንዲህ ብላለች፦ “እውነቱን ለመናገር እንዲህ ማድረጓ ብዙም አላስደሰተኝም ነበር። ማንም ሰው የእናቴን ቦታ እንዲወስድ አልፈለግኩም፤ እንዲሁም እሷን ሊተካ የሚችል እንዳለ አልተሰማኝም። ያም ቢሆን ማማ ሪትሱኮ እኔን የያዘችበት መንገድ እንድቀርባት አደረገኝ። በየሳምንቱ አብረን እንሰብካለን፤ እንዲሁም ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች አብረን እንሄዳለን። ሻይ እንድንጠጣ ትጋብዘኛለች፣ ምግብ ታመጣልኛለች፤ እንዲሁም ብዙ ጊዜ ደብዳቤ ጽፋና ካርድ አዘጋጅታ ትሰጠኛለች። ማማ ሪትሱኮ የነበራት አዎንታዊ አመለካከት በእኔ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል።”
የካኦሪ እናት ከሞቱ 12 ዓመታት ያለፉ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እሷና ባለቤቷ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ናቸው። ካኦሪ እንዲህ ብላለች፦ “ማማ ሪትሱኮ አሁንም ታስብልኛለች። ወደ ቤት ስመለስ ሁልጊዜ ሄጄ እጠይቃታለሁ፤ ጥሩ ጊዜም እናሳልፋለን።”
ፖሊ በቆጵሮስ የምትኖር የይሖዋ ምሥክር ናት፤ ሐዘን ከደረሰባት በኋላ ቀጣይ የሆነ ማበረታቻ በማግኘቷ ተጠቅማለች። የፖሊ ባለቤት የነበረው ሶዞስ ደግ፣ አፍቃሪና ምሳሌ የሚሆን ክርስቲያን እረኛ ነበር፤ ወላጆቻቸውንና የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ቤቱ ምግብ ጋብዞ አብሯቸው የመጫወት ልማድ ነበረው። (ያዕቆብ 1:27) በጣም የሚያሳዝነው ሶዞስ አንጎሉ ውስጥ በተፈጠረው ዕጢ የተነሳ በ53 ዓመቱ ሞተ። ፖሊ “በትዳር ዓለም ለ33 ዓመት አብሮኝ ያሳለፈውን ታማኝ ባለቤቴን አጣሁ” ብላለች።
ከቀብር ሥነ ሥርዓቱ በኋላ ፖሊ፣ 15 ዓመት የሆነውን የመጨረሻ ልጇን ዳንኤልን ይዛ ወደ ካናዳ ሄደች። በዚያም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መሰብሰብ ጀመሩ። ፖሊ እንዲህ ብላለች፦ “በአዲሱ ጉባኤ ውስጥ ያሉት ወንድሞችና እህቶች ስላሳለፍነው ሕይወትም ሆነ ስላጋጠመን ችግር የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ይህ ግን እኛን ከመቅረብና ከማበረታታት ወደኋላ እንዲሉ አላደረጋቸውም፤ እንዲያውም በአሳቢነት ያነጋግሩንና ጠቃሚ እርዳታ ይሰጡን ነበር። ልጄ፣ አባቱ በጣም በሚያስፈልገው በዚያ ወቅት እንዲህ ያለ እርዳታ ማግኘቱ ትልቅ ነገር ነው! በጉባኤው ውስጥ አመራር የሚሰጡት ወንድሞች ዳንኤልን በጣም ያቀርቡት ነበር። በተለይ አንደኛው ወንድም ከጉባኤው አባላት ጋር ሲዝናኑም ሆነ ኳስ ሲጫወቱ ዳንኤልን አስታውሶ ይጠራዋል።” በአሁኑ ጊዜ ፖሊና ልጇ በጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ።
ሐዘን የደረሰባቸውን ሰዎች ለመርዳትና ለማጽናናት የተለያዩ ነገሮችን ማድረግ እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የያዘው የሚያጓጓ ተስፋም ቢሆን አጽናኝ ነው።
^ አን.6 አንዳንዶች በዕለቱ ወይም በዚያ ሰሞን ሐዘንተኞቹን አስታውሰው ማጽናናት እንዲችሉ ግለሰቡ የሞተበትን ዕለት በቀን መቁጠሪያቸው ላይ አስፍረዋል።