አዲሱን ስብዕና መልበስና እንደለበስን መቀጠል
“አዲሱን ስብዕና ልበሱ።”—ቆላ. 3:10
1, 2. (ሀ) አዲሱን ስብዕና መልበስ ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር አይደለም የምንለው ለምንድን ነው? (ለ) በቆላስይስ 3:10-14 ላይ የተዘረዘሩት የአዲሱ ስብዕና ገጽታዎች የትኞቹ ናቸው?
‘አዲሱ ስብዕና።’ ይህ አገላለጽ በአዲስ ዓለም ትርጉም ውስጥ ሁለት ጊዜ ተጠቅሶ ይገኛል። (ኤፌ. 4:24፤ ቆላ. 3:10) አዲሱ ስብዕና “እንደ አምላክ ፈቃድ [የተፈጠረን]” ስብዕና ያመለክታል። እንዲህ ያለውን አዲስ ስብዕና ማዳበር ከአቅማችን በላይ የሆነ ነገር አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ የሰው ልጆችን የፈጠረው በራሱ አምሳል ነው፤ በመሆኑም ሁላችንም የእሱን ግሩም ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ አለን።—ዘፍ. 1:26, 27፤ ኤፌ. 5:1
2 እርግጥ ነው፣ ከመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በወረስነው አለፍጽምና ምክንያት አልፎ አልፎ መጥፎ ምኞት በውስጣችን ሊያቆጠቁጥ ይችላል። በተጨማሪም በዙሪያችን ያለው ዓለም ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድርብናል። ይሁንና ይሖዋ በምሕረቱ በሚያደርግልን እርዳታ እሱን የምናስደስት ዓይነት ሰዎች መሆን እንችላለን። እዚህ ግብ ላይ የመድረስ ፍላጎታችንን ይበልጥ ማጠናከር እንድንችል ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የጻፋቸውን የአዲሱን ስብዕና ገጽታዎች እንመርምር። (ቆላስይስ 3:10-14ን አንብብ።) በተጨማሪም እነዚህን ገጽታዎች በአገልግሎታችን ላይ ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
‘ሁላችሁም አንድ ናችሁ’
3. የአዲሱ ስብዕና አንዱ ገጽታ ምንድን ነው?
3 ጳውሎስ አዲሱን ስብዕና እንድንለብስ ማሳሰቢያ ከሰጠ በኋላ የአዲሱ ስብዕና አስፈላጊ ገጽታ የሆነውን ከአድልዎ ነፃ መሆንን አስመልክቶ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ግሪካዊ ወይም አይሁዳዊ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ የባዕድ አገር ሰው፣ እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ነፃ ሰው ብሎ ልዩነት የለም።” * በጉባኤ ውስጥ በዘር፣ በብሔር አሊያም በኑሮ ደረጃ ምክንያት ልዩነት ሊኖር የማይገባው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እውነተኛ የክርስቶስ ተከታዮች በሙሉ ‘አንድ ናቸው።’—ቆላ. 3:11፤ ገላ. 3:28
4. (ሀ) የይሖዋ አገልጋዮች አንዳቸው ሌላውን ሊይዙ የሚገባው እንዴት ነው? (ለ) ክርስቲያናዊ አንድነታችንን መጠበቅ ፈታኝ እንዲሆንብን የሚያደርግ ምን ሁኔታ ሊኖር ይችላል?
4 አዲሱን ስብዕና የለበሱ ሰዎች የእምነት ባልንጀሮቻቸውንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን በአክብሮት ይይዛሉ፤ ከየትኛውም ዘር ወይም የኑሮ ደረጃ ለመጡ ሰዎች አክብሮት አላቸው። (ሮም 2:11) ይሁንና በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ይህን ተግባራዊ ማድረግ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት የደቡብ አፍሪካ መንግሥት የተለያየ ዘር ያላቸው ሰዎች በተለያየ አካባቢ እንዲኖሩ የሚያዝ ሕግ አውጥቶ ነበር፤ በዚህም የተነሳ የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ አብዛኞቹ ሰዎች አሁንም የሚኖሩት በእነዚህ አካባቢዎች ነው። የበላይ አካሉ፣ በዚያ የሚኖሩ ወንድሞች እርስ በርስ እንዲቀራረቡና አንዳቸው ለሌላው ‘ልባቸውን ወለል አድርገው እንዲከፍቱ’ ለማበረታታት ሲል በጥቅምት 2013 አንድ ልዩ ዝግጅት እንዲደረግ ፈቃድ ሰጥቶ ነበር። (2 ቆሮ. 6:13) ይህ ዝግጅት ምንድን ነው?
5, 6. (ሀ) በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለውን አንድነት ለማጠናከር በአንድ አገር ውስጥ ምን ዝግጅት ተደርጎ ነበር? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) ይህ ዝግጅት ምን ውጤት አስገኝቷል?
5 በቋንቋ አሊያም በዘር የተለያዩ ሁለት ጉባኤዎች አልፎ አልፎ ቅዳሜንና እሁድን አብረው እንዲያሳልፉ ዝግጅት ተደረገ። በሁለቱም ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ወንድሞችና እህቶች አብረው በስብከቱ ሥራ ይካፈላሉ፣ አንድ ላይ ይሰበሰባሉ እንዲሁም አንዳቸው ሌላውን ቤታቸው ይጋብዛሉ። በመቶዎች የሚቆጠሩ ጉባኤዎች በዚህ ዝግጅት የተጠቀሙ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ያልሆኑ ሰዎችን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ለዚህ ዝግጅት ያላቸውን አድናቆት ለቅርንጫፍ ቢሮው ገልጸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የሃይማኖት መሪ እንዲህ ሲል አስተያየት ሰጥቷል፦ “እኔ የይሖዋ ምሥክር አይደለሁም፤ ሆኖም የስብከት ሥራችሁ ምን ያህል የተደራጀ እንደሆነ እንዲሁም የተለያየ ዘር ቢኖራችሁም አንድነት እንዳላችሁ መናገር እፈልጋለሁ።” ወንድሞችና እህቶችስ ስለዚህ ዝግጅት ምን ተሰምቷቸዋል?
6 የቆሳ ቋንቋ ተናጋሪ የሆነችው ኖማ መጀመሪያ አካባቢ፣ በእንግሊዝኛ ቋንቋ በሚደረግ ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ ነጭ ወንድሞችን በደሳሳ ጎጆዋ ውስጥ ለመጋበዝ አመንትታ ነበር። ይሁንና ከእነዚህ ወንድሞች ጋር አብራ ካገለገለችና ቤታቸው ተጋብዛ ከተስተናገደች በኋላ “ልክ እንደ እኛው ያሉ ሰዎች ናቸው!” በማለት ተናግራለች። በመሆኑም በቆሳ ቋንቋ የሚደረገው ኖማ ያለችበት ጉባኤ የእንግሊዝኛ ጉባኤን የሚያስተናግድበት ተራ ሲደርስ ምግብ አዘጋጅታ አንዳንድ ወንድሞችን ጋበዘች። ከጋበዘቻቸው ወንድሞች መካከል ነጭ የጉባኤ ሽማግሌ ይገኝበታል። ኖማ “ወንድም በጣም አጭር የፕላስቲክ ሣጥን ላይ መቀመጡ አስገረመኝ” በማለት ተናግራለች። ይህ ቀጣይ ዝግጅት በርካታ ወንድሞችና እህቶች አዳዲስ ጓደኞችን እንዲያፈሩ ያስቻላቸው ሲሆን የተለያየ ዘርና ቋንቋ ላላቸው ሰዎች ልባቸውን ወለል አድርገው እንዲከፍቱ አነሳስቷቸዋል።
‘ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄና ደግነት’
7. ምንጊዜም ርኅራኄ ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
7 የሰይጣን ዓለም እስካለ ድረስ ሁላችንም መከራ ይደርስብናል። ሥራ ልናጣ፣ በጠና ልንታመም፣ ስደት ሊደርስብን፣ የተፈጥሮ አደጋ ሊያጋጥመን፣ በወንጀል ምክንያት ንብረታችንን ልናጣ አሊያም ሌሎች ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። መከራ ወይም ችግር ሲያጋጥመን እርስ በርሳችን ለመረዳዳት፣ አንዳችን ለሌላው ከልብ የመነጨ ርኅራኄ ሊኖረን ይገባል። ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄ ካለን ኤፌ. 4:32) እነዚህ የአዲሱ ስብዕና ገጽታዎች አምላክን በመምሰል ሌሎችን ማጽናናት እንድንችል ይረዱናል።—2 ቆሮ. 1:3, 4
ለሌሎች ደግነት ለማሳየት እንነሳሳለን። (8. ለሁሉም የጉባኤው አባላት ርኅራኄና ደግነት ማሳየታችን ምን ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል? ምሳሌ ስጥ።
8 ከሌላ አገር ለመጡ አሊያም በሌሎች ዘንድ ዝቅ ተደርገው ለሚታዩ ሰዎች ለየት ያለ አሳቢነት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህን ሰዎች ልንቀርባቸው እንዲሁም በጉባኤው ውስጥ ተፈላጊ መሆናቸውን እንዲገነዘቡ ልንረዳቸው ይገባል። (1 ቆሮ. 12:22, 25) ከፊሊፒንስ ወደ ጃፓን ተዛውሮ መኖር የጀመረውን የዳኒካርልን ምሳሌ እንመልከት። የሌላ አገር ሰው በመሆኑ በሥራ ቦታው አድልዎ ይደረግበት ነበር። አንድ ቀን በይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኘ። ዳኒካርል እንዲህ ብሏል፦ “በስብሰባው ላይ የተገኙት በሙሉ ጃፓናውያን ነበሩ ማለት ይቻላል፤ ይሁንና ሁሉም ከዚህ በፊት የምንተዋወቅ ይመስል ሞቅ ያለ አቀባበል አደረጉልኝ።” እነዚህ ወንድሞች ያሳዩት ቀጣይ የሆነ ደግነት ዳኒካርል መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርግና እንዲጠመቅ ረድቶታል። በአሁኑ ጊዜ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል። አብረውት የሚያገለግሉት ሽማግሌዎች ዳኒካርልና ባለቤቱ ጄኒፈር ለጉባኤው በረከት እንደሆኑ ይሰማቸዋል። ሽማግሌዎቹ እነዚህን ባልና ሚስት በተመለከተ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “ኑሯቸውን ቀላል አድርገው በአቅኚነት ስለሚያገለግሉ መንግሥቱን በማስቀደም ረገድ ግሩም ምሳሌዎች ናቸው።”—ሉቃስ 12:31
9, 10. በአገልግሎት ላይ ርኅራኄ ማሳየት የሚያስገኘውን በረከት የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
9 የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ስንናገር ‘ለሁሉም መልካም የምናደርግበት’ ግሩም አጋጣሚ እናገኛለን። (ገላ. 6:10) በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ለስደተኞች ባላቸው ርኅራኄ ተነሳስተው አዲስ ቋንቋ ለመማር ጥረት እያደረጉ ነው። (1 ቆሮ. 9:23) ይህም የተትረፈረፈ በረከት አስገኝቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ቲፈኒ የተባለች በአውስትራሊያ የምትኖር እህት በብሪዝበን ከተማ ውስጥ የሚገኝን በስዋሂሊ ቋንቋ የሚመራ ጉባኤ ለመደገፍ ስትል ስዋሂሊ ተማረች። ቲፈኒ ቋንቋውን መማር ተፈታታኝ ቢሆንባትም እንዲህ ማድረጓ ብዙ በረከት አስገኝቶላታል። እንዲህ ብላለች፦ “በአገልግሎታችሁ መደሰት ከፈለጋችሁ አዲስ ቋንቋ እንድትማሩ አበረታታችኋለሁ። አዲስ ቋንቋ መማር፣ ካላችሁበት ከተማ ሳትወጡ ሌላ አገር እንደመሄድ ነው። ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበራችንንና ያለውን አስደናቂ አንድነት በገዛ ዓይናችሁ ማየት ትችላላችሁ።”
10 በጃፓን የሚኖርን አንድ ቤተሰብ ምሳሌም እንመልከት። ሴት ልጃቸው ሳኪኮ እንዲህ ብላለች፦ “በ1990ዎቹ አካባቢ በመስክ አገልግሎት ላይ ከብራዚል የመጡ በርካታ ስደተኞችን እናገኝ ነበር። ከፖርቱጋልኛ መጽሐፍ ቅዱሳቸው ላይ እንደ ራእይ 21:3, 4 እና መዝሙር 37:10, 11, 29 ያሉ ጥቅሶችን ስናሳያቸው በትኩረት ያዳምጣሉ፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ያለቅሳሉ።” ይህ ቤተሰብ እንዲህ በማድረግ ብቻ ረክቶ አልተቀመጠም። ሳኪኮ እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎቹ ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸውን ጥማት ስናይ በቤተሰብ ደረጃ ፖርቱጋልኛ ለመማር ተነሳሳን።” ከጊዜ በኋላ ቤተሰቡ የፖርቱጋልኛ ቋንቋ ጉባኤ እንዲቋቋም በመርዳት ረገድ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል። ይህ ቤተሰብ ባለፉት ዓመታት ውስጥ በርካታ ስደተኞች የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ ረድቷል። ሳኪኮ አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ፖርቱጋልኛ መማር ቀላል አይደለም፤ ሆኖም ያገኘነው በረከት ከከፈልነው መሥዋዕት ጋር ሊወዳደር አይችልም። ይሖዋን በጣም እናመሰግነዋለን።”—የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35ን አንብብ።
‘ትሕትናን ልበሱ’
11, 12. (ሀ) በትክክለኛው የልብ ዝንባሌ ተነሳስተን አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ምንጊዜም ትሑት ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል?
11 አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ጥረት የምናደርገው ይሖዋን ለማስከበር እንጂ የሰዎችን ውዳሴ ለማግኘት መሆን አይኖርበትም። በአንድ ወቅት ፍጹም የነበረ መንፈሳዊ ፍጡርም እንኳ በውስጡ ኩራት እንዲያድር በመፍቀዱ ኃጢአት እንደሠራ እናስታውስ። (ከሕዝቅኤል 28:17 ጋር አወዳድር።) ኃጢአተኛ ለሆንነው ለእኛ ደግሞ ከኩራትና ከትዕቢት መራቅ ምን ያህል ከባድ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም! ያም ቢሆን ትሕትናን መልበስ እንችላለን። እንዲህ ለማድረግ ምን ሊረዳን ይችላል?
12 ምንጊዜም ትሑት መሆን ከፈለግን በየዕለቱ የአምላክን ቃል የምናነብበትና ባነበብነው ላይ የምናሰላስልበት ጊዜ መመደብ ይኖርብናል። (ዘዳ. 17:18-20) በተለይም ደግሞ ኢየሱስ ባስተማራቸው ትምህርቶችና በትሕትና በማገልገል ረገድ በተወው ግሩም ምሳሌ ላይ ጊዜ ወስደን ማሰላሰላችን ይጠቅመናል። (ማቴ. 20:28) ኢየሱስ የሐዋርያቱን እግር እስከማጠብ ድረስ ትሑት መሆኑን አሳይቷል። (ዮሐ. 13:12-17) ትሕትናን ለመልበስ የሚረዳን ሌላው ነገር ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጠን አዘውትረን መጸለያችን ነው፤ ከሌሎች የተሻልን እንደሆንን በትንሹም እንኳ የሚሰማን ከሆነ የአምላክ መንፈስ ይህን ዝንባሌ ከሥሩ ነቅለን መጣል እንድንችል ይረዳናል።—ገላ. 6:3, 4፤ ፊልጵ. 2:3
13. ትሑት መሆን ምን በረከት ያስገኛል?
13 ምሳሌ 22:4ን አንብብ። ትሕትና ከእያንዳንዱ የአምላክ አገልጋይ የሚጠበቅ ብቃት ሲሆን ይህን ባሕርይ ማዳበር ብዙ በረከት ያስገኛል። ትሕትና በጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ያደርጋል። በተጨማሪም ትሕትናን ማዳበራችን የአምላክን ጸጋ ለማግኘት ያስችለናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል፦ “እርስ በርስ ባላችሁ ግንኙነት ሁላችሁም ትሕትናን ልበሱ፤ ምክንያቱም አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።”—1 ጴጥ. 5:5
“ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ”
14. ገርነትንና ትዕግሥትን በማንጸባረቅ ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ የሚሆነን ማን ነው?
14 በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ገርና ታጋሽ የሆኑ ሰዎች ደካማ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ። ይህ አስተሳሰብ ምንኛ ከእውነት የራቀ ነው! የእነዚህ ግሩም ባሕርያት ምንጭ በጽንፈ ዓለሙ ውስጥ ከሁሉ የላቀ ኃይል ያለው አካል ነው። ይሖዋ አምላክ ገርነትን እና ትዕግሥትን በማንጸባረቅ ረገድ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ነው። (2 ጴጥ. 3:9) አብርሃምና ሎጥ ጥያቄ ባቀረቡለት ወቅት ወኪሎቹ በሆኑት መላእክት አማካኝነት ምላሽ የሰጠበትን መንገድ እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። (ዘፍ. 18:22-33፤ 19:18-21) በተጨማሪም ይሖዋ ወላዋይ የሆነውን የእስራኤልን ብሔር ከ1,500 ለሚበልጡ ዓመታት ታግሷል።—ሕዝ. 33:11
15. ኢየሱስ ገርነትና ትዕግሥት በማሳየት ረገድ ምን ምሳሌ ትቶልናል?
15 ኢየሱስ “ገር” ነበር። (ማቴ. 11:29) የተከታዮቹን ድክመት ችሎ በማለፍ በጣም ትዕግሥተኛ እንደሆነ አሳይቷል። ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ጊዜ ሁሉ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች የሚሰነዝሩበትን ትችት ተቋቁሞ ጸንቷል። ያለጥፋቱ እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ ገርና ታጋሽ መሆኑን አስመሥክሯል። በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በከባድ ሥቃይ ውስጥ በነበረበት ወቅትም እንኳ “የሚያደርጉትን ስለማያውቁ ይቅር በላቸው” ብሎ በመጸለይ አባቱ ገዳዮቹን ይቅር እንዲላቸው ጠይቋል። (ሉቃስ 23:34) በእርግጥም ኢየሱስ ከባድ ሥቃይና መከራ በሚያስከትል ሁኔታም ሥር ገርና ታጋሽ በመሆን ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!—1 ጴጥሮስ 2:21-23ን አንብብ።
16. ገርነትና ትዕግሥት ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
ቆላ. 3:13) ይህን ትእዛዝ ለመፈጸም ገርና ታጋሽ መሆን እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። ይቅር ባዮች በመሆን የጉባኤው አንድነት ተጠብቆ እንዲቀጥል አስተዋጽኦ እናደርጋለን።
16 ገርነትና ትዕግሥት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህን ማድረግ ከምንችልባቸው መንገዶች መካከል አንዱን እንደሚከተለው በማለት ገልጿል፦ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።” (17. ገርነትና ትዕግሥት ማሳየታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
17 እያንዳንዱ ክርስቲያን ገርነትንና ትዕግሥትን የመልበስ ግዴታ አለበት፤ ይህ ለምርጫ የተተወ ጉዳይ አይደለም። ገርነትንና ትዕግሥትን መልበስ ለመዳን የግድ አስፈላጊ የሆነ ብቃት ነው። (ማቴ. 5:5፤ ያዕ. 1:21) ከሁሉ በላይ ደግሞ እነዚህን ባሕርያት በማንጸባረቅ ይሖዋን ማስከበርና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ እንዲያደርጉ መርዳት እንችላለን።—ገላ. 6:1፤ 2 ጢሞ. 2:24, 25
“ፍቅርን ልበሱ”
18. በፍቅርና ከአድልዎ በመራቅ መካከል ምን ዝምድና አለ?
18 እስካሁን ያየናቸው ባሕርያት በሙሉ ከፍቅር ጋር በጥብቅ የተቆራኙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ በወቅቱ የነበሩት ወንድሞች በሀብታሙና በድሃው መካከል አድልዎ ያደርጉ ስለነበር ይህን ጉዳይ በተመለከተ ምክር መስጠት አስፈልጎታል። እንዲህ ያለው ምግባር “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለውን ንጉሣዊ ሕግ የሚጻረር እንደሆነ ተናግሯል። አክሎም “ማዳላታችሁን የማትተዉ ከሆነ . . . ኃጢአት እየሠራችሁ ነው” ብሏል። (ያዕ. 2:8, 9) በተቃራኒው ግን ፍቅር በትምህርት ደረጃ፣ በዘር አሊያም በኑሮ ደረጃ አድልዎ ከማድረግ እንድንርቅ ያነሳሳናል። በእርግጥም አድልዎ አለማድረግ እንደ ጭንብል ከላይ የምናጠልቀው ነገር መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ እውነተኛ የስብዕናችን ገጽታ ሊሆን ይገባል።
19. ፍቅርን መልበሳችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
19 በተጨማሪም ፍቅር “ታጋሽና ደግ ነው” እንዲሁም “አይታበይም።” (1 ቆሮ. 13:4) የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች ሰዎች መናገር ትዕግሥት፣ ደግነትና ትሕትና ማሳየትን እንደሚጠይቅ አይካድም። (ማቴ. 28:19) እነዚህን ባሕርያት ማንጸባረቃችን በጉባኤያችን ውስጥ ካሉት ከሁሉም ወንድሞችና እህቶች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረንም ይረዳናል። እንዲህ ያለውን ፍቅር ማሳየት ምን በረከት ያስገኛል? ጉባኤዎቻችን አንድነት እንዲኖራቸውና ይሖዋን የሚያስከብሩ እንዲሆኑ ያስችላል። ይህ ደግሞ አዳዲሶች ወደ ይሖዋ ቤት እንዲሳቡ ያደርጋል። ስለ አዲሱ ስብዕና የሚናገረው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የሚከተለውን ሐሳብ በመናገር የሚደመደም መሆኑ የተገባ ነው፦ “በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ላይ ፍቅርን ልበሱ፤ ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነውና።”—ቆላ. 3:14
‘እየታደሳችሁ መሄዳችሁን ቀጥሉ’
20. (ሀ) ራሳችንን የትኞቹን ጥያቄዎች መጠየቅ ይኖርብናል? ለምንስ? (ለ) የትኛውን ጊዜ በናፍቆት እንጠባበቃለን?
20 እያንዳንዳችን ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘መጥፎ ልማዶችን በማስወገድና እንዳያገረሹብኝ በመከላከል ረገድ ምን ማሻሻያ ማድረግ ይኖርብኛል?’ የአምላክን መንግሥት እንዳንወርስ እንቅፋት የሚሆንብንን ማንኛውንም ዝንባሌ ወይም ልማድ ለማሸነፍ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንዲሁም ይሖዋ እንዲረዳን ልባዊ ጸሎት ማቅረብ ያስፈልገናል። (ገላ. 5:19-21) በተጨማሪም ‘አእምሮዬን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ እንዲሄድ እያደረግኩ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል። (ኤፌ. 4:23, 24) አዲሱን ስብዕና ሙሉ በሙሉ መልበስ የምንችልበት ጊዜ እስኪመጣ ድረስ እያንዳንዳችን ይህን ስብዕና ለመልበስና እንደለበስን ለመቀጠል የማያቋርጥ ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። በዙሪያችን ያሉት ሰዎች ሁሉ አዲሱን ስብዕና ፍጹም በሆነ መንገድ የሚለብሱበት ጊዜ ሲመጣ ሕይወት ምንኛ አስደሳች እንደሚሆን እስቲ አስቡት!
^ አን.3 በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እስኩቴሶች ያልሠለጠኑ ሰዎች እንደሆኑ ተደርገው ስለሚታዩ በማኅበረሰቡ ዘንድ የተናቁ ነበሩ።