በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰላም ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

ሰላም ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?

የምንኖረው ሁከት በነገሠበት ዓለም ውስጥ በመሆኑ ሰላማዊ ሕይወት ለመምራት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅብናል። በተወሰነ መጠን ሰላማዊ ሕይወት ቢኖረንም እንኳ ይህን ሰላም ላለማጣት ብዙውን ጊዜ መታገል ያስፈልገናል። ታዲያ የአምላክ ቃል፣ እውነተኛና ዘላቂ ሰላም ማግኘት እንድንችል የሚረዳ ምን ጠቃሚ ሐሳብ ይዟል? ሌሎችም እንዲህ ያለውን ሰላም እንዲያገኙ መርዳት የምንችለውስ እንዴት ነው?

እውነተኛ ሰላም ለማግኘት ምን ያስፈልጋል?

እውነተኛ ሰላም እንድናገኝ ከተፈለገ ከስጋት ነፃ ልንሆንና የደህንነት ስሜት ሊኖረን ይገባል። በተጨማሪም ከሌሎች ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት ያስፈልገናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ዘላቂ ሰላም ለማግኘት ከአምላክ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት ይኖርብናል። ለመሆኑ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት የምንችለው እንዴት ነው?

ብዙዎች ሰላማቸውን እንዲያጡ የሚያደርጉ አስጨናቂ ሁኔታዎች አሉ

ጽድቅ የሚንጸባረቅባቸውን የይሖዋ ትእዛዛትና መሠረታዊ ሥርዓቶች ስናከብር በእሱ እንደምንታመንና ከእሱ ጋር ሰላማዊ ዝምድና መመሥረት እንደምንፈልግ እናሳያለን። (ኤር. 17:7, 8፤ ያዕ. 2:22, 23) እንዲህ ካደረግን፣ እሱም በምላሹ ወደ እኛ የሚቀርብ ከመሆኑም ሌላ ውስጣዊ ሰላም በመስጠት ይባርከናል። ኢሳይያስ 32:17 “የእውነተኛ ጽድቅ ውጤት ሰላም፣ የእውነተኛ ጽድቅ ፍሬም ዘላቂ ጸጥታና ደህንነት ይሆናል” ይላል። በእርግጥም፣ ይሖዋን ከልብ ከታዘዝን እውነተኛ ውስጣዊ ሰላም ማግኘት እንችላለን።—ኢሳ. 48:18, 19

በተጨማሪም በሰማይ ካለው አባታችን የምናገኘው አንድ አስደናቂ ስጦታ ዘላቂ ሰላም እንዲኖረን ይረዳናል፤ ይህ ስጦታ መንፈስ ቅዱስ ነው።—ሥራ 9:31

የአምላክ መንፈስ ሰላም እንዲኖረን ይረዳናል

ሐዋርያው ጳውሎስ ከዘረዘራቸው “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታዎች መካከል ሦስተኛው ሰላም ነው። (ገላ. 5:22, 23) እውነተኛ ሰላም የአምላክ መንፈስ ፍሬ አንዱ ገጽታ ስለሆነ እንዲህ ያለውን ሰላም ለማግኘት በመንፈስ ቅዱስ ለመመራት ፈቃደኞች መሆን ያስፈልገናል። ይሁንና የአምላክ መንፈስ ሰላም እንድናገኝ ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው? እስቲ ሁለት መንገዶችን እንመልከት።

አንደኛ፣ አምላክ በመንፈሱ መሪነት ያስጻፈውን ቃሉን አዘውትረን ማንበባችን ሰላም ለማግኘት ይረዳናል። (መዝ. 1:2, 3) በመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ላይ ስናሰላስል፣ ይሖዋ ስለተለያዩ ነገሮች ያለውን አመለካከት እንድናስተውል የአምላክ መንፈስ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ሰላሙን ጠብቆ መቆየት የቻለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ለሰላም ትልቅ ቦታ የሚሰጥበትን ምክንያት እንረዳለን። ከአምላክ ቃል ላይ የምናገኛቸውን እንዲህ ያሉ ትምህርቶች በሥራ ላይ ስናውል ይበልጥ ሰላማዊ የሆነ ሕይወት መምራት እንችላለን።—ምሳሌ 3:1, 2

ሁለተኛ፣ የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት መጸለይ አለብን። (ሉቃስ 11:13) የይሖዋን እርዳታ አጥብቀን የምንሻ ከሆነ “ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት [ልባችንንና አእምሯችንን እንደሚጠብቅ]” ይሖዋ ቃል ገብቶልናል። (ፊልጵ. 4:6, 7) አዘውትረን በመጸለይ የይሖዋን መንፈስ ለማግኘት ከለመንን፣ አምላካችን ከእሱ ጋር ጥሩ ዝምድና ያላቸው ሰዎች ብቻ የሚያገኙትን ውስጣዊ ሰላም ይሰጠናል።—ሮም 15:13

መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን ምክር በተግባር በማዋል፣ ውስጣዊ ሰላም ማግኘት እንዲሁም ከይሖዋና ከሰዎች ጋር ሰላማዊ ዝምድና መመሥረት የቻሉ ሰዎችን ምሳሌ እስቲ እንመልከት። እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያሉ ለውጦችን ማድረግ የቻሉት እንዴት ነው?

ዘላቂ ሰላም ያገኙት እንዴት ነው?

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ቀደም ሲል ‘በቀላሉ ይቆጡ’ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ይበልጥ አሳቢ፣ ደግ፣ ታጋሽ እና ሰላማዊ ሆነዋል። * (ምሳሌ 29:22) ቁጣን በማስወገድ ከሌሎች ጋር በሰላም መኖር የቻሉ ሁለት ክርስቲያኖች ተሞክሮ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል።

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ማዋልና የአምላክን መንፈስ ለማግኘት መጸለይ ሰላም እንድናገኝ ይረዳናል

ዴቪድ የነበረው መጥፎ አመለካከት በንግግሩም ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር። እውነትን ከማወቁ በፊት በትንሽ በትልቁ ሌሎችን ይተች የነበረ ሲሆን ቤተሰቦቹንም ያመናጭቅ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ዴቪድ ለውጥ ማድረግና ሰላማዊ ሰው መሆን እንደሚያስፈልገው ተገነዘበ። ታዲያ ሰላማዊ መሆን የቻለው እንዴት ነው? እንዲህ ብሏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወቴ ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ጀመርኩ፤ በዚህም ምክንያት ከቤተሰቦቼ ጋር የነበረኝ ዝምድና ተሻሻለ።”

የሬቸል አስተዳደግ ቁጡ እንድትሆን አድርጓት ነበር። “አብዛኞቹ የቤተሰባችን አባላት ቁጡ ነበሩ፤ በዚህም ምክንያት አሁንም ድረስ ቁጣዬን መቆጣጠር ያስቸግረኛል” በማለት በሐቀኝነት ተናግራለች። ታዲያ ይበልጥ ሰላማዊ እንድትሆን የረዳት ምንድን ነው? “ይሖዋ እንዲረዳኝ አዘውትሬ መጸለዬ ነው” በማለት መልሱን ሰጥታለች።

ዴቪድና ሬቸል፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ማዋል እንዲሁም አምላክ መንፈስ ቅዱስን በመስጠት እንዲረዳን መጠየቅ ሰላም እንደሚያስገኝ ከሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎች መካከል ሁለቱ ብቻ ናቸው። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ የምንኖረው በጥላቻ በተሞላ ዓለም ውስጥ ቢሆንም እንኳ ውስጣዊ ሰላም ማግኘት እንችላለን፤ እንዲህ ያለው ውስጣዊ ሰላም ከቤተሰባችን አባላትም ሆነ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ተስማምተን ለመኖር ይረዳናል። ሆኖም ይሖዋ “ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም [እንድንኖር]” ይፈልጋል። (ሮም 12:18) ይህ በእርግጥ የሚቻል ነገር ነው? ደግሞስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት ማድረጋችን ምን ጥቅም ያስገኛል?

ከሌሎች ጋር በሰላም ለመኖር ጥረት አድርጉ

ሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት ከሚገልጸው ሰላም የሚሰጥ መልእክት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በስብከቱ ሥራ አማካኝነት እንጋብዛቸዋለን። (ኢሳ. 9:6, 7፤ ማቴ. 24:14) ደስ የሚለው ብዙዎች ግብዣውን ተቀብለዋል። ይህም በዙሪያቸው ሲፈጸም በሚመለከቱት ነገር የተነሳ በተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዳይዋጡ ወይም ከልክ በላይ እንዳይበሳጩ አድርጓቸዋል። ከዚህም ሌላ ለወደፊቱ ጊዜ እውነተኛ ተስፋ ያገኙ ሲሆን ‘ሰላምን ለመፈለግና ለመከተል’ ተነሳስተዋል።—መዝ. 34:14

ይሁን እንጂ መልእክታችንን የሚቀበለው ሁሉም ሰው አይደለም፤ ከጊዜ በኋላ መልእክታችንን የሚቀበሉ ሰዎች እንኳ መጀመሪያ ላይ አዎንታዊ ምላሽ አይሰጡ ይሆናል። (ዮሐ. 3:19) ያም ቢሆን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ፣ ምሥራቹን ሰላማዊ በሆነና አክብሮት በተሞላበት መንገድ ለእነሱ ለማቅረብ ጥረት እናደርጋለን። ይህም ኢየሱስ በማቴዎስ 10:11-13 ላይ ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ያስችለናል፦ “ወደ ቤትም ስትገቡ ቤተሰቡን ሰላም በሉ። ቤቱ የሚገባው ሆኖ ከተገኘ ሰላማችሁ ይድረሰው፤ የማይገባው ከሆነ ግን ሰላማችሁ ወደ እናንተ ይመለስ።” መልእክታችንን የሚቃወም ሰው ሲያጋጥመን የኢየሱስን ምክር መከተላችን ሰላማችንን እንዳናጣ ብሎም ሌላ ጊዜ ግለሰቡን የመርዳት አጋጣሚ እንድናገኝ ሊያደርገን ይችላል።

በተጨማሪም ሥራችንን የሚቃወሙትን ጨምሮ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፊት ስንቀርብ እነሱን አክብሮት በተሞላበት መንገድ በማነጋገር ሰላም ፈጣሪ መሆን እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ የአንዲት የአፍሪካ አገር መንግሥት በጭፍን ጥላቻ ተነሳስቶ የስብሰባ አዳራሾችን ለመገንባት ፈቃድ እንዳናገኝ ከልክሎ ነበር። ጉዳዩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ሲባል፣ ቀደም ሲል በዚያች አገር ሚስዮናዊ ሆኖ ያገለግል የነበረ አንድ ወንድም በለንደን፣ እንግሊዝ ውስጥ ያለውን የዚያች አገር አምባሳደር ሄዶ እንዲያነጋግር ተመደበ። ይህ ወንድም በዚያች አገር የሚኖሩት የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት ሥራ ሰላማዊ እንደሆነ ለአምባሳደሩ እንዲያስረዳ ታስቦ ነበር። ታዲያ ወንድም አምባሳደሩን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት ምን ውጤት አስገኘ?

ወንድም እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “ወደ እንግዶች መቀበያ ክፍሉ ስደርስ፣ በዚያ የምትሠራውን ሴት አለባበስ በመመልከት የየትኛው ጎሳ አባል እንደሆነች ተገነዘብኩ፤ እኔ ደግሞ የዚያን ጎሳ ቋንቋ ተምሬ ነበር። ስለዚህ በራሷ ቋንቋ ሰላምታ ሰጠኋት። እሷም በመደነቅ ‘ወደዚህ የመጣህበት ምክንያት ምንድን ነው?’ ብላ ጠየቀችኝ። እኔም አምባሳደሩን ማነጋገር እንደምፈልግ በትሕትና ነገርኳት። ከዚያም ለአምባሳደሩ ስልክ ደወለችለት፤ እሱም ወደ እኔ በመምጣት በአገሩ ቋንቋ ሰላምታ ሰጠኝ። ቀጥሎም የይሖዋ ምሥክሮች ስለሚያከናውኑት ሰላማዊ ሥራ ስገልጽለት በጥሞና አዳመጠኝ።”

ወንድም ለአምባሳደሩ አክብሮት በተሞላበት መንገድ ጉዳዩን ማስረዳቱ፣ አምባሳደሩ ሥራችንን በተመለከተ የነበረውን የተሳሳተ አመለካከትና ጭፍን ጥላቻ በእጅጉ ለመቀነስ ረድቶታል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የዚያች አገር መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮች በሚያከናውኑት የግንባታ ሥራ ላይ የጣለውን እገዳ አነሳ። ወንድሞች እንዲህ ያለ ውጤት በመገኘቱ እጅግ ተደስተዋል! በእርግጥም ሌሎችን በአክብሮት መያዝ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል፤ ሌሎች በርካታ ጥቅሞችንም ያስገኛል።

ለዘላለም በሰላም መኖር

በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ሕዝቦች የሚኖሩት ሰላም በሰፈነበት መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው። አንተም በግል ሕይወትህ የመንፈስ ፍሬ ገጽታ የሆነውን ሰላምን ይበልጥ ለማዳበር ስትጥር በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ያለው ሰላም እንዲጨምር አስተዋጽኦ ታበረክታለህ። ከሁሉም በላይ ደግሞ የይሖዋን ሞገስ ማግኘት ትችላለህ፤ እንዲሁም በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም እጅግ ሰላማዊ የሆነ ሕይወት የመምራት አጋጣሚ ታገኛለህ።—2 ጴጥ. 3:13, 14

^ አን.13 ስለ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች ከሚያብራሩት ተከታታይ ርዕሶች አንዱ ስለ ደግነት የሚያወሳ ይሆናል።