“እንዲህ ያለ ፍቅር በማየታችን ልባችን በጣም ተነክቷል”
ቅዳሜ ሚያዝያ 25, 2015 ተራራማ በሆነችውና ከሕንድ በስተ ሰሜን በምትገኘው በኔፓል በመሬት መንቀጥቀጥ መለኪያ 7.8 የደረሰ የምድር ነውጥ ተከሰተ። የምድር ነውጡ የተከሰተው ከዋና ከተማው ከካትማንዱ በስተ ሰሜን ምዕራብ 80 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ ነበር። ይህ አደጋ በኔፓል ታሪክ ውስጥ ከተመዘገቡት የተፈጥሮ አደጋዎች ሁሉ የብዙ ሰዎችን ሕይወት በመቅጠፍ ረገድ ተወዳዳሪ የለውም፤ በዚህ አደጋ ምክንያት ከ8,500 የሚበልጡ ሰዎች ሕይወት አልፏል። ከግማሽ ሚሊዮን የሚበልጡ ቤቶች ወድመዋል። በኔፓል ከሚገኙት 2,200 የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አብዛኞቹ የሚኖሩት በአደጋው በተጠቃ አካባቢ ነው። የሚያሳዝነው አንዲት የይሖዋ ምሥክርና ሁለት ልጆቿ በአደጋው ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ሚሼል የተባለች አንዲት የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች፦ “የምድር ነውጡ የተከሰተው፣ ከፍተኛ ጥፋት በደረሰበት አካባቢ የሚገኙ ጉባኤዎች ክርስቲያናዊ ስብሰባ እያደረጉ ባሉበት ወቅት ነበር። አደጋው የተከሰተው ብዙዎች ቤት ባሉበት ሰዓት ቢሆን ኖሮ የተጎጂዎች ቁጥር ከዚህ የበለጠ ይሆን ነበር።” ስብሰባ ላይ የነበሩት ሰዎች ሊተርፉ የቻሉት ለምንድን ነው? የመንግሥት አዳራሾቹ * የተሠሩበት መንገድ ለዚህ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
“ጥቅሙ የታየው አሁን ነው!”
በኔፓል የሚገኙት ዘመናዊ የመንግሥት አዳራሾች የሚገነቡት የምድር ነውጥን መቋቋም እንዲችሉ ተደርገው ነው። በመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ሥራ የሚካፈለው ማን ባሃዱር እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ሰዎች በአንጻራዊ ሁኔታ አነስተኛ የሆኑ አዳራሾችን ለመገንባት እንዲህ ያለ ጠንካራ መሠረት የምንጥለው ለምን እንደሆነ ይጠይቁን ነበር። ጥቅሙ የታየው አሁን ነው!” የምድር ነውጡ ከተከሰተ በኋላ የመንግሥት አዳራሾቹ ለመጠለያነት እንዲያገለግሉ ፈቃድ ተሰጠ። ከዋናው ነውጥ በኋላ ሌሎች ነውጦች የተከሰቱ ቢሆንም በመንግሥት አዳራሾቹ ውስጥ የተጠለሉት የይሖዋ ምሥክሮችና ጎረቤቶቻቸው ምንም ስጋት አላደረባቸውም።
ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ የደረሱበት ያልታወቀ የጉባኤ አባላትን ወዲያውኑ ማፈላለግ ጀመሩ። ባቢታ የተባለች የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ብላለች፦ “ሽማግሌዎቹ ከራሳቸው ደህንነት ይበልጥ ያሳሰባቸው የጉባኤው አባላት ደህንነት ነበር። እንዲህ ያለ ፍቅር በማየታችን ልባችን በጣም ተነክቷል።” በኔፓል የሚገኙትን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በበላይነት የሚመራው ኮሚቴ አባላት የሆኑት ሦስት ወንድሞች ከቦታ ቦታ እየተጓዙ ከሚያገለግሉ ወንድሞች ማለትም ከወረዳ የበላይ ተመልካቾች ጋር አብረው በመሆን የምድር ነውጡ በተከሰተ ማግስት ጉባኤዎቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማወቅና የጉባኤ ሽማግሌዎቹን ለመደገፍ ጉባኤዎችን መጎብኘት ጀመሩ።
የምድር ነውጡ ከተከሰተ ከስድስት ቀን በኋላ በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚሠራው ጋሪ ብሮ ከባለቤቱ ከሩቢ ጋር ወደ ኔፓል ተጓዘ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ኮሚቴ አባል የሆነው ሩበን እንዲህ ብሏል፦ “ካትማንዱ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ያልተረጋጋ ስለነበርና ከዋናው ነውጥ በኋላ ሌሎች ነውጦች ስለተከሰቱ ወንድም ብሮ መምጣት እንደማይችል ተሰምቶን ነበር። ሆኖም ለመምጣት ቆርጦ ነበር፤ ደግሞም መጣ! በኔፓል ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች በእሱ መምጣት በጣም ተደስተዋል።”
“ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንደተቀራረብን ተሰምቶናል”
በኔፓል በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቢሮ ውስጥ የሚያገለግለው ሺላስ እንዲህ ብሏል፦ “ስልካችን መሥራት እንደጀመረ ያለማቋረጥ ይደወልልን ጀመር! በመላው ዓለም ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ደህንነታችን አሳስቧቸው ነበር። አንዳንዶቹ የሚናገሩት ቋንቋ ባይገባንም ምን ያህል እንደሚወዱንና እኛን ለመርዳት እንደሚጓጉ መገንዘብ ችለናል።”
የምድር ነውጡ ከተከሰተ በኋላ ባሉት ቀናት በአካባቢው የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ መንግሥት አዳራሹ ምግብ ይዘው በመምጣት ለሰዎች ይሰጡ ነበር። በተጨማሪም የአደጋ ጊዜ እርዳታ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን ወዲያውኑ ከተለያዩ አገሮች በተለይ ደግሞ ከባንግላዴሽ፣ ከሕንድና ከጃፓን እርዳታ መጉረፍ ጀመረ። ከአውሮፓ የመጡ የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፈ የሕክምና ቡድን በጥቂት ቀናት ውስጥ የመጣ ሲሆን በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ውስጥ እርዳታ ለመስጠት ዝግጅት አደረገ። የሕክምና ቡድኑ አባላት በአደጋው ለተጎዱት ሰዎች ወዲያውኑ ሕክምና መስጠት ጀመሩ፤ ሰዎቹ ለደረሰባቸው ሥነ ልቦናዊ ጉዳት መፍትሔ ለመስጠትም ጥረት አድርገዋል።
ኡተራ የተባለች ሴት የተናገረችው ሐሳብ የብዙዎችን ስሜት የሚያንጸባርቅ ነው፦ “የምድር ነውጡ በጣም አስከፊና አስፈሪ ቢሆንም ከአደጋው በኋላ ከመንፈሳዊ ቤተሰባችን ጋር ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንደተቀራረብን ተሰምቶናል።” አዎ፣ የምድር ነውጡ የይሖዋ ሕዝቦች ለአምላክና ለወንድሞቻቸው ያላቸው ፍቅር እንዲቀዘቅዝ አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ፍቅራቸውን ይበልጥ አጠናክሮታል።
^ አን.3 የመንግሥት አዳራሽ የሚባለው የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባዎቻቸውን የሚያደርጉበት ቦታ ነው።