ደስታ የሚያስገኝ መንገድ
ተስፋ
“ለእናንተ የማስበው ጥፋትን ሳይሆን ሰላምን እንዲሁም የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን ነው።”—ኤርምያስ 29:11
“ተስፋ . . . በመንፈሳዊ ሕያው ሆኖ ለመቀጠል እጅግ ወሳኝ ነገር ነው” በማለት ሆፕ ኢን ዚ ኤጅ ኦፍ አንግዛይቲ የተባለው መጽሐፍ ይገልጻል። “በተጨማሪም እንደ ባይተዋርነት፣ ፍርሃትና ረዳት የለሽነት ላሉት ስሜቶች ፍቱን መድኃኒት ነው።”
መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ለሰው ልጆች በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይናገራል፤ በተጨማሪም ተስፋችንን አስተማማኝ ባልሆኑ ነገሮች ላይ መጣል የሚያስከትለውን አደጋ ይገልጻል። መዝሙር 146:3 “በመኳንንትም ሆነ ማዳን በማይችሉ ሰዎች አትታመኑ” ይላል። መዳን ለማግኘት በሰው ልጆች ከመታመን ይልቅ ቃል የገባቸውን ነገሮች ሁሉ የመፈጸም ኃይል ባለው በፈጣሪያችን ላይ መታመናችን ብልህነት ነው። ታዲያ ፈጣሪያችን ምን ተስፋ ሰጥቶናል? እስቲ የሚከተሉትን እንመልከት፦
ክፋት ይጠፋል፤ ከዚያም ጻድቃን ዘላቂ ሰላም ያገኛሉ፦ መዝሙር 37:10, 11 እንዲህ ይላል፦ “ለጥቂት ጊዜ ነው እንጂ ክፉዎች አይኖሩም፤ . . . የዋሆች ግን ምድርን ይወርሳሉ፤ በብዙ ሰላምም እጅግ ደስ ይላቸዋል።” በተጨማሪም ቁጥር 29 ‘ጻድቃን በምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ’ ይላል።
ጦርነት ይወገዳል፦ “[ይሖዋ] ጦርነትን ከመላው ምድር ላይ ያስወግዳል። ቀስትን ይሰባብራል፤ ጦርንም ያነክታል፤ የጦር ሠረገሎችን በእሳት ያቃጥላል።”—መዝሙር 46:8, 9
ሕመም፣ ሥቃይ ወይም ሞት አይኖርም፦ “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ . . . እሱም እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።”—ራእይ 21:3, 4
ሁሉም ሰው በቂ ምግብ ያገኛል፦ “በምድር ላይ እህል ይትረፈረፋል፤ በተራሮችም አናት ላይ በብዛት ይኖራል።”—መዝሙር 72:16
መላው ዓለም ፍትሐዊ በሆነው የክርስቶስ መንግሥት አገዛዝ ሥር ይሆናል፦ “ከተለያዩ ብሔራትና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሕዝቦች ሁሉ እንዲያገለግሉት የገዢነት ሥልጣን፣ ክብርና መንግሥት [ለኢየሱስ ክርስቶስ] ተሰጠው። የገዢነት ሥልጣኑ የማያልፍና ዘላለማዊ፣ መንግሥቱም የማይጠፋ ነው።”—ዳንኤል 7:14
እነዚህ ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ያደረጋቸው ነገሮች፣ ንጉሥ ሆኖ ለመግዛት ብቃቱን እንደሚያሟላ ያረጋግጣሉ። ለምሳሌ የታመሙትን ፈውሷል፣ ድሆችን መግቧል እንዲሁም የሞቱ ሰዎችን አስነስቷል። ከእነዚህ ተአምራት የበለጠ ቦታ የሚሰጣቸው ግን ኢየሱስ ያስተማራቸው ትምህርቶች ናቸው፤ ምክንያቱም እነዚህ ትምህርቶች ሰዎች በሰላምና በአንድነት ለዘላለም አብረው እንዲኖሩ የሚያስችሉ መመሪያዎችን የያዙ ናቸው። በተጨማሪም ኢየሱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አስቀድሞ ተናግሯል፤ ይህም አሁን ያለው ዓለም የሚጠፋበት ጊዜ መቅረቡን የሚጠቁመውን ምልክት ይጨምራል።
ከሰላሙ በፊት የሚከሰተው ማዕበል
ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ሰላምና ደህንነት እንደሚሰፍን ሳይሆን ከዚህ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮች እንደሚከሰቱ ትንቢት ተናግሯል! “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ” ምልክት ክፍል እንደሆኑ ከገለጻቸው ነገሮች መካከል በዓለም ዙሪያ የሚከሰት ጦርነት፣ የምግብ እጥረት፣ ቸነፈርና ከባድ የምድር ነውጥ ይገኙበታል። (ማቴዎስ 24:3, 7፤ ሉቃስ 21:10, 11፤ ራእይ 6:3-8)) በተጨማሪም ኢየሱስ “ክፋት እየበዛ ስለሚሄድ የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” ብሏል።—ማቴዎስ 24:12
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሰዎች ፍቅር መቀዝቀዙ የሚታይባቸውን የተለያዩ መንገዶች በ2 ጢሞቴዎስ 3:1-5 ላይ አስፍሯል። ዘገባው እንደሚገልጸው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” የሚኖሩ ሰዎች በጥቅሉ ሲታይ ስለ ራሳቸው ብቻ የሚያስቡ፣ ገንዘብንና ደስታን የሚወዱ፣ ትዕቢተኞች እንዲሁም ጨካኞች ይሆናሉ። በተጨማሪም በቤተሰብ አባላት መካከል ያለው ተፈጥሯዊ ፍቅር እንደሚጠፋና ልጆች ለወላጆቻቸው የማይታዘዙ እንደሚሆኑ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ግብዝነት እንደሚስፋፋ ተገልጿል።
እንደ ማዕበል ያሉት እነዚህ ሁኔታዎች የዚህ ዓለም መጨረሻ መቅረቡን ያረጋግጣሉ። በተጨማሪም በአምላክ መንግሥት አማካኝነት ሰላም የሚሰፍንበት ጊዜ እንደቀረበ ይጠቁማሉ። ኢየሱስም ቢሆን ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት በተናገረው ትንቢት ውስጥ የሚከተለውን ማረጋገጫ አካቷል፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴዎስ 24:14
ይህ ምሥራች ለክፉዎች ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ሲሆን ለጻድቃን ደግሞ ቃል የተገቡላቸው በረከቶች በቅርቡ እንደሚፈጸሙ ማረጋገጫ ይሰጣል። ስለ እነዚህ በረከቶች ይበልጥ ማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ የዚህን መጽሔት የጀርባ ገጽ እንድትመለከት እንጋብዝሃለን።