በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ቃለ ምልልስ | ራጄሽ ካላርያ

በአንጎል ላይ ጥናት የሚያካሂዱ አንድ ፕሮፌሰር ስለሚያምኑበት ነገር ምን ይላሉ?

በአንጎል ላይ ጥናት የሚያካሂዱ አንድ ፕሮፌሰር ስለሚያምኑበት ነገር ምን ይላሉ?

የኒውካስል ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ፕሮፌሰር ራጄሽ ካላርያ ከ40 ዓመት በላይ በሰው አንጎል ላይ ጥናት ሲያካሂዱ ቆይተዋል። እኚህ ሰው በዝግመተ ለውጥ ያምኑ ነበር። በኋላ ግን የአመለካከት ለውጥ አደረጉ። ንቁ! መጽሔት ለእኚህ ሰው ስለ ሥራቸውና ስለሚያምኑበት ነገር ቃለ መጠይቅ አድርጎላቸዋል።

እስቲ ስለ ቀድሞ ሃይማኖትዎ ይንገሩን።

አባቴ የተወለደው በሕንድ ሲሆን እናቴ ደግሞ የሕንድ ዝርያ የነበራት ቢሆንም የተወለደችው በኡጋንዳ ነው። ወላጆቼ የሂንዱ ልማዶችን ይከተሉ ነበር። በቤተሰባችን ውስጥ ሦስት ልጆች የነበርን ሲሆን እኔ ሁለተኛ ልጅ ነኝ። የምንኖረው ናይሮቢ፣ ኬንያ ውስጥ ነበር። በአካባቢያችን ብዙ ሂንዱዎች ይኖሩ ነበር።

ስለ ሳይንስ ለማጥናት የተነሳሱት ለምንድን ነው?

ስለ እንስሳት ማወቅ ያስደስተኝ ነበር፤ አስደናቂ የሆኑትን የዱር አራዊት ለማየት ብዙ ጊዜ ከጓደኞቼ ጋር ወደ ጫካ እንሄድ ነበር። መጀመሪያ ላይ የእንስሳት ቀዶ ጥገና ሐኪም የመሆን ፍላጎት ነበረኝ። በናይሮቢ ከሚገኝ የቴክኒክ ኮሌጅ ከተመረቅኩ በኋላ ግን በለንደን ዩኒቨርሲቲ ስለ ጤና ችግሮች ለማጥናት ወደ እንግሊዝ አገር ሄድኩ። ከጊዜ በኋላ በሰው አንጎል ላይ ያተኮረ ልዩ ሥልጠና ወሰድኩ።

የተማሩት ትምህርት በሃይማኖታዊ አመለካከትዎ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ይሰማዎታል?

አዎ። በሳይንሱ መስክ ይበልጥ ምርምር ባደረግኩ መጠን እንስሳትንና ምስሎችን ማምለክም ሆነ በሌሎቹ የሂንዱ ወጎችና አፈ ታሪኮች ማመን እየከበደኝ መጣ።

በዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እንዲያምኑ ያደረግዎት ምን ነበር?

ወጣት ሳለሁ በዙሪያዬ የነበሩ ብዙ ሰዎች የሰው ልጅ የዝግመተ ለውጥ ሂደት የጀመረው በአፍሪካ ነው ብለው ያምኑ ነበር፤ በትምህርት ቤትም ይህንኑ ጽንሰ ሐሳብ እንማር ነበር። በተጨማሪም መምህራንና የዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች አንቱ የሚባሉ ሳይንቲስቶች በሙሉ በዝግመተ ለውጥ ያምናሉ ብለን እንድናስብ ያደርጉን ነበር።

ታዲያ ከጊዜ በኋላ ‘ሕይወት የተገኘው እንዴት ነው?’ የሚለውን ጥያቄ እንደገና መመርመር የጀመሩት ለምንድን ነው?

ለተወሰኑ ዓመታት ባዮሎጂና አናቶሚ ሳጠና ከቆየሁ በኋላ አንድ አብሮኝ የሚማር ተማሪ የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያስተማሩትን ትምህርት ነገረኝ። በዚህ ጊዜ የማወቅ ጉጉት አደረብኝ። ስለዚህ የይሖዋ ምሥክሮች ናይሮቢ ውስጥ በኮሌጃችን አዳራሽ ባደረጉት ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። በኋላም የይሖዋ ምሥክሮች ከሆኑ ሁለት ሚስዮናውያን ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት አደረግን። እነዚህ ሚስዮናውያን ከሕይወት ጋር በተያያዘ ለሚነሱ ትላልቅ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጥ አንድ ታላቅ ንድፍ አውጪ አለ ብለው ያምኑ ነበር፤ ይህ እምነታቸው በተረት ላይ የተመሠረተ አልነበረም። ያቀረቡልኝ ማስረጃ ምክንያታዊ ነበር።

በሕክምናው መስክ ያገኙት እውቀት በፈጣሪ እንዳያምኑ አድርጎዎታል?

በፍጹም! በሰውም ሆነ በእንስሳት አካል ላይ ያደረግኩት ጥናት ሕያዋን ፍጥረታት አስደናቂና እጅግ ውስብስብ የሆነ አሠራር እንዳላቸው እንዳስተውል አድርጎኛል። እጅግ የረቀቀ አሠራር ያላቸው እነዚህ ፍጥረታት የመጡት እንዲሁ በአጋጣሚ ነው ብሎ ማመን ምክንያታዊ ሊሆንልኝ አልቻለም።

ምሳሌ ሊሰጡን ይችላሉ?

ከ1970ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ የሰውን አንጎል በተመለከተ ጥናት ሳካሂድ ቆይቻለሁ፤ ሆኖም አሁንም ድረስ የአንጎላችን አሠራር በጣም ያስደንቀኛል። አንጎል የሰውን ሐሳብም ሆነ ትዝታዎች በሙሉ የያዘ የአካል ክፍል ሲሆን የሌሎቹን የአካል ክፍሎች ሥራም ይቆጣጠራል። በተጨማሪም አንጎል ከሰውነታችን ውስጥም ሆነ ከሰውነታችን ውጭ የሚመጡትን መረጃዎች በሙሉ የሚያስተናግድ የስሜት ማዕከል ነው።

አንጎላችን ሥራውን የሚያከናውነው በውስጥ በሚካሄደው ውስብስብ የሆነ ኬሚካላዊ ሂደትና ኒውሮንስ የሚባሉት ዋነኛ የአንጎል ሴሎች ባሏቸው የረቀቁ የመገናኛ መስመሮች አማካኝነት ነው። የሰው አንጎል አክሰን በሚባሉ ድሮች አማካኝነት እርስ በርሳቸው የሚገናኙ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ኒውሮኖች አሉት። አንዱ ነጠላ ኒውሮን ዴንድራይት በሚባሉ ድሮች አማካኝነት ከሌሎች ኒውሮኖች ጋር በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የመገናኛ መስመሮች ሊፈጥር ይችላል። በዚህ የተነሳ በአንጎል ውስጥ ያሉት የመገናኛ መስመሮች በጣም በርካታ ናቸው። ከዚህ ይበልጥ የሚያስገርመው ደግሞ እነዚህ ኒውሮኖችና ዴንድራይቶች እርስ በርስ የተሳሰሩት እንዲሁ በዘፈቀደ ሳይሆን ሥርዓት ባለው መንገድ መሆኑ ነው። እነዚህ መስመሮች የተዘረጉበትና የተገናኙበት መንገድ እጅግ አስደናቂ ነው።

ይህን ይበልጥ ሊያብራሩልን ይችላሉ?

አንድ ሕፃን ማህፀን ውስጥ እያለም ሆነ ከተወለደ በኋላ በአንጎሉ ውስጥ ያሉት የመገናኛ መስመሮች ሥርዓት ባለው መንገድ መስፋፋታቸውን ይቀጥላሉ። ኒውሮኖች ጥቂት ሴንቲ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኙ ኒውሮኖች ድሮቻቸውን ይዘረጋሉ፤ ይህ ርቀት ከሴሎች አንጻር ሲታይ በጣም ረጅም ርቀት ነው። ድሩ ሄዶ የሚገናኘው እንዲሁ ከአንድ ሴል ጋር ሳይሆን በአንድ ሴል ውስጥ ካለ የተወሰነ ክፍል ጋር ሊሆን ይችላል።

አንድ አዲስ ድር ከአንድ ኒውሮን ወደ ሌላ ኒውሮን በሚዘረጋበት ጊዜ “ቁም፣” “ሂድ” ወይም “ተመለስ” እንደሚሉት ባሉ ጠቋሚ ምልክቶች እየተመራ ወደተፈለገው ቦታ ይደርሳል። እነዚህ ድሮች ግልጽ መመሪያ ካላገኙ ወዲያውኑ መንገዳቸውን ይስታሉ። በዲ ኤን ኤ ላይ ከተጻፉት መመሪያዎች አንስቶ መላው ሂደት በጣም በተራቀቀና በተቀናጀ መንገድ ይከናወናል።

ይሁንና አንጎላችን እንዴት እንደሚያድግና ተግባሮቹን እንደሚያከናውን እንዲሁም ትዝታዎች፣ ስሜቶችና ሐሳቦች በአንጎል ውስጥ የሚፈጠሩት እንዴት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ገና ብዙ ይቀረናል። የአንጎላችን አሠራር በጣም አስገራሚ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ የተለያዩ ነገሮችን ማከናወን መቻሉ በራሱ የላቀ ጥበብ ያለው ፈጣሪ እንዳለ እንዳምን አድርጎኛል።

የይሖዋ ምሥክር የሆኑት ለምንድን ነው?

የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አሳዩኝ። ለምሳሌ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መጽሐፍ ባይሆንም ሳይንሳዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የሚሰጠው መረጃ ሁሉ ትክክል ነው። በተጨማሪም በትክክል ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችን ይዟል። ከዚህም ሌላ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ምክር የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል። የራሴ ሕይወት ለዚህ ማስረጃ ነው። የይሖዋ ምሥክር ከሆንኩበት ከ1973 ጀምሮ የምመራው በመጽሐፍ ቅዱስ ነው። በዚህም የተነሳ ሕይወቴ አስደሳችና ዓላማ ያለው ሆኖልኛል።