ከውጥረት እፎይታ ማግኘት
ውጥረትን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?
ውጥረትን በተሳካ ሁኔታ መቋቋም ከፈለግክ ስለ ጤንነትህ፣ ከሌሎች ጋር ስላለህ ግንኙነት እንዲሁም ስለ ግቦችህና በሕይወትህ ውስጥ ትልቅ ቦታ ስለምትሰጣቸው ነገሮች ቆም ብለህ ማሰብ ይኖርብሃል። ይህ ርዕስ ውጥረትን በተሻለ መንገድ ለመቋቋም አልፎ ተርፎም ለመቀነስ የሚረዱ ጠቃሚ ምክሮችን ይዟል።
ስለ ዛሬ ብቻ ለማሰብ ሞክር
“ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት።”—ማቴዎስ 6:34
ምን ማለት ነው? ጭንቀት የሚፈጥር ነገር በየዕለቱ ያጋጥመናል። ስለዚህ በዛሬው ጭንቀት ላይ የነገን ጭንቀት በመጨመር ሁኔታውን አታባብስ። ስለ ዛሬ ብቻ ለማሰብ ሞክር።
-
ውጥረት ወደ ጭንቀት ሊያድግ ይችላል። ስለዚህ እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ በመጀመሪያ፣ ውጥረትን ሙሉ በሙሉ ማስቀረት እንደማይቻል አምነህ ተቀበል። ማስቀረት በማትችለው ነገር ላይ መብሰልሰል ውጥረትህን ይጨምረዋል። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ የፈራነው ነገር ላይደርስ እንደሚችል አስታውስ።
ምክንያታዊ ሁን
‘ከሰማይ የሆነው ጥበብ ምክንያታዊ ነው።’—ያዕቆብ 3:17
ምን ማለት ነው? ከራስህም ሆነ ከሌሎች በምትጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ ሁን፤ ፍጽምና አትጠብቅ።
-
ልክህን እወቅ፤ ምክንያታዊ ሁን እንዲሁም አንተም ሆንክ ሌሎች ሰዎች የአቅም ገደብ እንዳለባችሁ አትርሳ። እንዲህ ካደረግክ የራስህንም ሆነ የሌሎችን ውጥረት መቀነስ ትችላለህ፤ ይህ ደግሞ አንተም ሆንክ በዙሪያህ ያሉት ሰዎች በሥራችሁ የተሻለ ውጤት እንድታገኙ ያደርጋል። እንዲሁም ስቆ ማለፍን ተማር። ችግር በሚፈጠርበት ጊዜም ጭምር ስቀህ ለማለፍ የምትሞክር ከሆነ ውጥረትህን መቀነስና ደስተኛ መሆን ትችላለህ።
ውጥረት የሚፈጥርብህን ነገር ለይተህ እወቅ
“ጥልቅ ግንዛቤ ያለው [ሰው] የተረጋጋ ነው።”—ምሳሌ 17:27
ምን ማለት ነው? እንደ ብስጭት፣ ጭንቀትና ትዕግሥት ማጣት ያሉት አሉታዊ ስሜቶች በትክክል እንዳታስብ ሊያደርጉህ ስለሚችሉ ለመረጋጋት ሞክር።
-
ውጥረት የሚፈጥርብህን ነገር ለይተህ እወቅ እንዲሁም የምትሰጠውን ምላሽ አስተውል። ለምሳሌ ውጥረት ውስጥ ስትሆን የሚኖርህን አስተሳሰብ፣ ስሜት እንዲሁም ባሕርይ ልብ ብለህ አጢን፤ ምናልባትም እነዚህን ነገሮች በጽሑፍ ማስፈር ትችል ይሆናል። ለውጥረት የምትሰጠውን ምላሽ በደንብ ማስተዋልህ ውጥረትን በተሻለ መንገድ ለመቋቋም ሊረዳህ ይችላል። በተጨማሪም ውጥረት የሚፈጥሩ ነገሮችን ማስወገድ የምትችልበትን መንገድ ለማሰብ ሞክር። ማስወገድ የማይቻል ከሆነ ደግሞ እነዚህ ነገሮች የሚያስከትሉብህን ተጽዕኖ ለመቀነስ ጥረት አድርግ፤ ለምሳሌ ሥራህን የምታከናውንበትን መንገድ ወይም የጊዜ አጠቃቀምህን ማስተካከል ትችል ይሆናል።
-
አመለካከትህን ለማስተካከል ሞክር። ለአንተ ውጥረት የሚፈጥርብህ ነገር ለሌላ ሰው ውጥረት አይፈጥር ይሆናል። ልዩነቱ ያለው አመለካከት ላይ ሊሆን ይችላል። የሚከተሉትን ሦስት ሐሳቦች ልብ በል፦
-
ሰዎች ሆን ብለው እንደጎዱህ ለማሰብ አትቸኩል። ለምሳሌ ሰልፍ ላይ እያለህ አንድ ሰው ሰልፉን ጥሶ ገባ እንበል። ግለሰቡ ይህን ያደረገው በንቀት እንደሆነ ካሰብክ ትበሳጭ ይሆናል። ከዚህ ይልቅ ግለሰቡ ይህን ያደረገው በክፋት ተነሳስቶ እንዳልሆነ ለማሰብ ብትሞክርስ? እውነታው እንደዚያ ሊሆን ይችላል!
-
አዎንታዊውን ጎን ለመመልከት ሞክር። ሐኪም ቤት ወይም ፌርማታ ሆነህ ለረጅም ሰዓት ስትጠብቅ ጊዜውን ለማንበብ፣ ኢሜይል ለመላክ ወይም ከሥራ ጋር የተያያዙ ነገሮችን ለማከናወን ከተጠቀምክበት ሁኔታው ያን ያህል ውጥረት አይፈጥርብህም።
-
አመለካከትህን ለማስፋት ሞክር። ‘ይህን ጉዳይ ነገ ወይም የሚቀጥለው ሳምንት ላይ ሆኜ ባስበው ይህን ያህል ያስጨንቀኛል?’ በማለት ራስህን ጠይቅ። ቀላል ወይም ዘላቂ ያልሆኑ ችግሮችን ከከባድ ችግሮች መለየት ተማር።
-
የተደራጀህ ሁን
“ሁሉም ነገር በአግባብና በሥርዓት ይሁን።”—1 ቆሮንቶስ 14:40
ምን ማለት ነው? ሕይወትህን በተደራጀ መንገድ ለመምራት ሞክር።
-
ሁላችንም በተወሰነ መጠን ሕይወታችን የተደራጀ እንዲሆን እንፈልጋለን። የተደራጀን እንዳንሆንና ውጥረት እንዲፈጠርብን የሚያደርገው አንዱ ነገር ደግሞ ዛሬ ነገ የማለት ልማድ ነው፤ ይህ ልማድ ሥራ እንዲከመርብህ ሊያደርግ ይችላል። የሚከተሉትን ሁለት ሐሳቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክር።
-
ምክንያታዊ የሆነ ፕሮግራም አውጣ እንዲሁም በፕሮግራምህ ተመራ።
-
ዛሬ ነገ እንድትል የሚያደርጉህን ምክንያቶች ለይተህ ለማወቅና ለማስተካከል ጥረት አድርግ።
-
ሚዛናዊ ሕይወት ለመምራት ሞክር
“ብዙ በመልፋትና ነፋስን በማሳደድ ከሚገኝ ሁለት እፍኝ ይልቅ ጥቂት እረፍት በማድረግ የሚገኝ አንድ እፍኝ ይሻላል።”—መክብብ 4:6
ምን ማለት ነው? ከመጠን በላይ ሥራ የሚወዱ ሰዎች ‘ብዙ በመልፋት ያገኙትን ሁለት እፍኝ’ ማጣጣም አይችሉም። በሥራቸው ውጤት ለመደሰት የሚችሉበት ጊዜና ጉልበት ላይኖራቸው ይችላል።
-
ለሥራ እና ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ። ብዙ ገንዘብ ስላለህ ብቻ ይበልጥ ደስተኛ ትሆናለህ ወይም ውጥረትህ ይቀንሳል ማለት አይደለም። እንዲያውም እውነታው የዚህ ተቃራኒ ሊሆን ይችላል። መክብብ 5:12 “ባለጸጋ ሰው ያለው ብዙ ሀብት . . . እንቅልፍ ይነሳዋል” ይላል። ስለዚህ ገቢህን አብቃቅተህ ለመኖር ሞክር።
-
ዘና የምትልበት ጊዜ ይኑርህ። የምትወደውን ነገር ስታደርግ ውጥረትህ ይቀንሳል። ሆኖም ቴሌቪዥን እንደ ማየት ያሉ ተመልካች ብቻ የሚያደርጉ መዝናኛዎች ውጥረትህን ለመቀነስ ላይረዱህ ይችላሉ።
-
በቴክኖሎጂ አጠቃቀምህ ላይ ገደብ አብጅ። ኢሜይልና የጽሑፍ መልእክት በማንበብ እንዲሁም ማኅበራዊ ሚዲያ በመጠቀም የምታሳልፈውን ጊዜ ቀንስ። አስገዳጅ ካልሆነብህ በቀር የሥራ ኢሜይሎችን ከሥራ ሰዓት ውጭ አታስተናግድ።
ጤንነትህን ተንከባከብ
“የአካል ብቃት እንቅስቃሴ . . . ይጠቅማል።”—1 ጢሞቴዎስ 4:8
ምን ማለት ነው? አዘውትሮ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ለጤና ጠቃሚ ነው።
-
ለጤና የሚጠቅሙ ልማዶችን አዳብር። አካላዊ እንቅስቃሴ ደስተኛ እንድትሆንና ሰውነትህ ውጥረትን በተሻለ መንገድ መቋቋም እንዲችል ይረዳሃል። የተመጣጠነ ምግብ ተመገብ፤ ቁርስ፣ ምሳ ወይም ራት ላለመዝለል ጥረት አድርግ። እንዲሁም በቂ እረፍት ለማግኘት ሞክር።
-
ለውጥረት መፍትሔ ተደርገው የሚታሰቡ ጎጂ ነገሮችን አስወግድ፤ ለምሳሌ ከሲጋራ፣ ከዕፅ ወይም ከመጠጥ ሱስ ራቅ። እነዚህ ነገሮች ጤናህን ስለሚጎዱ እንዲሁም ለፍተህ ያገኘኸውን ገንዘብ ስለሚያባክኑብህ ውሎ አድሮ ውጥረት ይጨምሩብሃል።
-
ውጥረት ከአቅምህ በላይ እንደሆነብህ ከተሰማህ ሐኪም አማክር። የሕክምና እርዳታ ማግኘት የሚያሳፍር ነገር አይደለም።
ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን ለይ
“ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።”—ፊልጵስዩስ 1:10
ምን ማለት ነው? ለየትኞቹ ነገሮች ቅድሚያ መስጠት እንዳለብህ በጥንቃቄ አስብ።
-
ልታከናውናቸው የሚገቡ ነገሮችን በአስፈላጊነታቸው ቅደም ተከተል መሠረት አስፍር። ይህም ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑት ሥራዎች ላይ ለማተኮር ይረዳሃል፤ እንዲሁም የትኞቹን ሥራዎች ለሌላ ጊዜ ማስተላለፍ፣ ለሌላ ሰው መስጠት ወይም ከናካቴው መተው እንደምትችል ለማወቅ ያስችልሃል።
-
ለአንድ ሳምንት ያህል ጊዜህን እንዴት እንደተጠቀምክበት በጽሑፍ አስፍር። ከዚያም ጊዜህን በተሻለ መንገድ መጠቀም የምትችለው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር። የጊዜ አጠቃቀምህን በሚገባ ከተቆጣጠርክ የሚሰማህ ውጥረት ይቀንሳል።
-
ለእረፍት ጊዜ መድብ። ለጥቂት ደቂቃም ቢሆን እረፍት ማድረግህ ኃይልህ እንዲታደስና ውጥረትህ እንዲቀንስ ያደርጋል።
እርዳታ ጠይቅ
“በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።”—ምሳሌ 12:25
ምን ማለት ነው? ሌሎች የሚናገሩት ደግነትና ርኅራኄ የሚንጸባረቅበት ንግግር ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ ሊያደርግ ይችላል።
-
ስሜትህን ለሚረዳልህ ሰው ችግርህን አካፍል። እንዲህ ያለው ወዳጅ አመለካከትህን እንድታስተካክል ወይም ያላስተዋልከውን መፍትሔ እንድታይ ሊረዳህ ይችላል። ደግሞም ስሜትህን አውጥተህ መናገርህ በራሱ ውጥረቱ ቀለል እንዲልህ ያደርጋል።
-
የሌሎችን እገዛ ጠይቅ። ሥራህን ለሌላ ሰው መስጠት ወይም ማካፈል ትችል ይሆን?
-
የሥራ ባልደረባህ ውጥረት የሚፈጥርብህ ከሆነ ሁኔታውን ማሻሻል የምትችልበትን መንገድ ለማሰብ ሞክር። ለምሳሌ በደግነትና በጥበብ ለግለሰቡ ስሜትህን ልትነግረው ትችል ይሆን? (ምሳሌ 17:27) ካልተሳካልህ ደግሞ ከግለሰቡ ጋር የምታሳልፈውን ጊዜ ለመቀነስ ጥረት ማድረግ ትችላለህ።
መንፈሳዊ ፍላጎትህን ለማርካት ጥረት አድርግ
“መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው።”—ማቴዎስ 5:3
ምን ማለት ነው? የሰው ልጆች መሠረታዊ ፍላጎት ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ብቻ አይደለም። መንፈሳዊ ፍላጎትም አለን። ደስተኞች መሆን ከፈለግን መንፈሳዊ ፍላጎት እንዳለን መገንዘብና ይህን ፍላጎት ለማርካት ጥረት ማድረግ አለብን።
-
ጸሎት በእጅጉ ሊረዳህ ይችላል። አምላክ ‘ስለሚያስብልህ የሚያስጨንቅህን ነገር ሁሉ በእሱ ላይ እንድትጥል’ ግብዣ አቅርቦልሃል። (1 ጴጥሮስ 5:7) መጸለይና በሚያንጹ ነገሮች ላይ ማሰላሰል ውስጣዊ ሰላም ለማግኘት ይረዳል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7
-
መንፈሳዊነትህን የሚገነቡ ነገሮችን አንብብ። በዚህ መጽሔት ውስጥ የሰፈሩት ምክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ የተገኙ ናቸው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማርካት ታስቦ የተዘጋጀ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክሮች “ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን” እንድናዳብር ይረዱናል። (ምሳሌ 3:21) ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ ለምን ግብ አታወጣም? ከምሳሌ መጽሐፍ መጀመር ትችል ይሆናል።