ተስፋ ለማድረግ የሚያበቃ ምክንያት ይኖር ይሆን?
ተስፋ ለማድረግ የሚያበቃ ምክንያት ይኖር ይሆን?
“ውጥረት የነገሠባቸው ትዳሮች ካሉባቸው ችግሮች አንዱ ሁኔታው ሊሻሻል አይችልም የሚል አፍራሽ አስተሳሰብ ማሳደራቸው ነው። እንዲህ ያለው እምነት ማንኛውንም ዓይነት ገንቢ ጥረት ለማድረግ እንዳትነሳሳ ስለሚያደርግ ትልቅ እንቅፋት ይሆናል።”—ዶክተር አሮን ቲ ቤክ
ከባድ ሕመም ስለሚሰማህ ምርመራ ለማድረግ ወደ ሐኪም ሄደሃል እንበል። በጣም አሳስቦሃል። ጤንነትህ፣ ሕይወትህም ጭምር አደጋ ላይ ወድቆ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሐኪሙ አስፈላጊውን ምርመራ ካደረገ በኋላ ያጋጠመህ ችግር በቀላሉ የሚታይ ባይሆንም በሕክምና ሊረዳ የሚችል እንደሆነ ቢነግርህስ? እንዲያውም ሐኪሙ ጤናማ የሆነ የአመጋገብና የአካላዊ እንቅስቃሴ ልማድ ብትከተል ሙሉ በሙሉ ልትድን እንደምትችል ነገረህ እንበል። ትልቅ የእፎይታ ስሜት እንደሚሰማህና ምክሩን በደስታ እንደምትቀበል አያጠራጥርም!
ይህንን ሁኔታ ከተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ ጋር አነጻጽር። በትዳርህ ውስጥ አንዳንድ ችግሮች መከሰት ጀምረዋልን? እርግጥ ነው፣ ማንኛውም ትዳር ቢሆን ችግሮችና አለመግባባቶች ያጋጥሙታል። ስለዚህ በዝምድናችሁ መካከል አልፎ አልፎ አስቸጋሪ ወቅቶች ቢከሰቱ በትዳራችሁ ውስጥ ፍቅር ጠፍቷል ማለት አይደለም። ይሁን እንጂ የተፈጠረው ችግር ለሳምንታት፣ ለወራት እንዲያውም ለዓመታት ቢቀጥልስ? ይህ በቀላሉ የሚታይ ነገር ስላልሆነ ሊያሳስባችሁ ይገባል። እንዲያውም ጠቅላላ ሕይወታችሁ፣ የልጆቻችሁ ሕይወት ሳይቀር በትዳራችሁ ሁኔታ ሊነካ ይችላል። ለምሳሌ በጋብቻ ውስጥ የሚከሰት ችግር ለመንፈስ ጭንቀት፣ ለምርታማነት መቀነስ፣ ለልጆች በትምህርት መድከምና ለመሳሰሉት ችግሮች ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ይታመናል። ይሁን እንጂ በዚህ ብቻ አያበቃም። ክርስቲያኖች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ያላቸው ዝምድና ከአምላክ ጋር ያላቸውን ዝምድና ጭምር ሊነካባቸው እንደሚችል ይገነዘባሉ።—1 ጴጥሮስ 3:7
በአንተና በትዳር ጓደኛህ መካከል ችግሮች መከሰታቸው ተስፋ ከሌለው ሁኔታ ላይ መድረሳችሁን አያመለክትም። አንድ ባልና ሚስት በትዳር ውስጥ ችግር ማጋጠሙ የማይቀር መሆኑን መገንዘባቸው የችግራቸውን ትክክለኛ ገጽታ እንዲመለከቱና መፍትሄ ለማግኘት ጥረት እንዲያደርጉ ሊረዳቸው ይችላል። አይዚክ የተባለ አንድ ባል እንዲህ ብሏል:- “ባልና ሚስት በትዳር ሕይወታቸው ውስጥ የሚከፉበትም ሆነ የሚደሰቱበት ጊዜ መኖሩ የማይቀር መሆኑን አላውቅም ነበር። የኛ ትዳር አንድ ዓይነት ችግር ሳይኖረው አይቀርም ብዬ አስብ ነበር!”
የትዳራችሁ ሁኔታ በጣም ተበላሽቶ ፍቅር የጠፋበት እስከመሆን ቢደርስም ከመፍረስ ሊድን ይችላል። እርግጥ የተናጋ ዝምድና፣ በተለይ ችግሩ ለዓመታት የቆየ ከሆነ የሚያስከትለው ቁስል በቀላሉ ሊሽር እንደማይችል የታወቀ ነው። ያም ሆኖ ግን ተስፋ ለማድረግ የሚያበቃ ጠንካራ ምክንያት አለ። ወሳኙ ነገር በቁርጠኝነት መነሳት ነው። ትዳራቸው በእጅጉ የተናጋባቸው *
ሁለት ግለሰቦች እንኳን ለትዳራቸው ትልቅ ግምት ከሰጡ ሊያድሱት ይችላሉ።ስለዚህ ‘እርካታ የሚያስገኝ ዘላቂ ዝምድና ለመመሥረት ያለኝ ፍላጎት ምን ያህል ጠንካራ ነው?’ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። እናንተም ሆናችሁ የትዳር ጓደኛችሁ ትዳራችሁን ለማደስ የሚያስችል እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ናችሁ? ቀደም ብለን የጠቀስናቸው ዶክተር ቤክ “ባለትዳሮች የትዳራቸውን ደካማ ጎን ለመጠገንና ጠንካራውን ጎን ደግሞ ይበልጥ ለማጠናከር አብረው ሲጥሩ በጣም መጥፎ መስሎ ይታይ የነበረው ትዳር እንኳን ተሻሽሎ በማየቴ በጣም ተደንቄአለሁ” ብለዋል። ይሁን እንጂ የትዳር ጓደኛችሁ ለመተባበር ፈቃደኛ ባይሆንስ? ወይም ችግር መኖሩን እንኳን ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆንስ? ትዳራችሁን ለመታደግ የምታደርጉት የአንድ ወገን ጥረት ከንቱ ልፋት ነውን? በፍጹም አይደለም! “እናንተ አንዳንድ ለውጦች ብታደርጉ” ይላሉ ዶክተር ቤክ፣ “ይህ ብቻውን የትዳር ጓደኛችሁ ለውጥ እንዲያደርግ ሊያነሳሳው ይችላል። አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ለውጥ ያደርጋል።”
ይህ ፈጽሞ በእኔ ሁኔታ አይሠራም ብላችሁ በችኮላ አትደምድሙ። በትዳራችሁ ላይ ትልቅ አደጋ የሚያደርሰው እንዲህ ዓይነቱ አስቀድሞ ሽንፈትን የመቀበል አዝማሚያ ሊሆን ይችላል! ከሁለት አንዳችሁ የመጀመሪያውን እርምጃ መውሰድ ይኖርባችኋል። ታዲያ የመጀመሪያውን እርምጃ ራሳችሁ ልትወስዱ ትችላላችሁን? የለውጡ እንቅስቃሴ አንዴ መታየት ከጀመረ የትዳር ጓደኛችሁ ደስተኛ ቤተሰብ በመገንባቱ ጥረት ቢተባበራችሁ ጥቅም እንደሚያገኝ ሊገነዘብ ይችላል።
ታዲያ ብቻችሁንም ሆነ ከትዳር ጓደኛችሁ ጋር ሆናችሁ ትዳራችሁን ለመታደግ ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? በዚህ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ ትልቅ እርዳታ ያበረክታል። እስቲ እንመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.6 በአንዳንድ ከበድ ያሉ ሁኔታዎች ባልና ሚስት ለመለያየት የሚያደርሳቸው በቂ ምክንያት ሊኖር ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 7:10, 11) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ በዝሙት ምክንያት መፋታት እንደሚቻል ይገልጻል። (ማቴዎስ 19:9) ዝሙት የፈጸመውን የትዳር ጓደኛ መፍታትም ሆነ አለመፍታት የግል ውሳኔ ነው። ሌሎች ሰዎች ተበዳዩ ወገን በሚያደርገው ውሳኔ ላይ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ ማሳደር የለባቸውም።—ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 158-61 ተመልከት።