ከአዝጋሚ ሞት ወደ አስደሳች ሕይወት
ከአዝጋሚ ሞት ወደ አስደሳች ሕይወት
ዚያማንቲ ዛቴሴሪስ እንደተናገረችው
‘የመሞቻዬ ቀን ተቆርጧል።’ሆስፒታል ተኝቼ የተሰጠኝ ደም ጠብ ጠብ እያለ ሲወርድ እየተመለከትኩ ይህን አብሰለስል ነበር። እንግዲህ ይህም እንደመኖር ከተቆጠረ በሕይወት መቀጠል የምችለው በዚህ መንገድ ብቻ እንደሆነ ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ሲነገረኝ ቆይቷል።
የግሪክ ደሴት በሆነችው በቀርጤስ፣ ኢራፔትራ በተባለ ቦታ በ1969 ከተወለድኩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወላጆቼ የሚያሳዝን ነገር ተነገራቸው። ልጃቸው ቤታ ታላሴሚያ ወይም ኩሊስ አኒሚያ የሚባለው የደም ማነስ በሽታ እንደያዛት ዶክተሮች ነገሯቸው። ቤታ ታላሴሚያ የሚባለው ከባድ የደም ማነስ በሽታ ብዙውን ጊዜ በግሪክ፣ በኢጣሊያ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በደቡብ እስያ ወይም አፍሪካዊ ዝርያ ያላቸውን ሕዝቦች የሚያጠቃ በዘር የሚተላለፍ የደም በሽታ ነው።
ዶክተሮቹ ለወላጆቼ እንዳስረዷቸው ከሆነ እንደዚህ ያለ የጤና ችግር ያለበት ሰው ቀይ የደም ሴሎቹ ኦክስጂንን ለሴሎች የሚያጓጉዘውን ፕሮቲን ማለትም ሄሞግሎቢንን በበቂ መጠን አያመነጭም። ስለሆነም ወደ ሴሎቼ በቂ ኦክስጅን አይደርስም። ጉበቴና ጣፊያዬ ቀይ የደም ሴሎችን ስለሚገድሏቸውና ስለሚያስወግዷቸው በደሜ ውስጥ የሚቆዩት ለአጭር ጊዜ ብቻ ነው። የተበላሹ ወይም ከጥቅም ውጪ የሆኑ ቀይ የደም ሴሎችን ማስወገድ የእነዚህ የሰውነት አካላት ተግባር ነው።
ታላሴሚያ የያዘውን ሰው ማከም የሚቻለው ዘወትር ደም በመስጠትና በሰውነቱ ውስጥ የሚከማቸውን ብረት በማስወገድ እንደሆነ ለወላጆቼ ተነገራቸው። ይሁን እንጂ ዶክተሮች እንደተናገሩት ደም በመስጠት ሕክምና ማድረጉ በልብና በጉበት ውስጥ ብረት እንዲከማች ስለሚያደርግ ሞት ሊያስከትል ይችላል። ደም በመስጠት የሚደረገው ሕክምና በሽተኛው በቀጣዮቹ አሥር ዓመታት ውስጥ እንዳይሞት ሊረዳው ይችላል። በዚህ መንገድ የሚሰጠው ሕክምና የብረት መመረዝ ስለሚያስከትል ከጊዜ በኋላ ለሞት ሊዳረግ ይችላል። እንደ እኔ ሥር የሰደደው ታላሴሚያ የያዘው በሽተኛ ብዙውን ጊዜ 30 ዓመት ከመኖሩ በፊት በልብ ሕመም ይሞታል።
“ሞት ተቀጥሮልኝ” የመራሁት ሕይወት
ሞት ያጠላብኝ ገና ከልጅነቴ ጀምሮ ነበር። እንደዚህ ባለ ሁኔታ ሥር መኖር ምን ያክል እንደሚከብድ ለመናገር ቃላት ያጥሩኛል። ስለ ወደፊቱ ጊዜ እቅድ አላወጣም፤ እንዲሁም ማንኛውም ሰው የሚመራውን ዓይነት ሕይወት እኖራለሁ ብዬ ማሰብ የማይታለም ነው። የያዘኝ በሽታ ለእኔ ጊዜውን ጠብቆ እንደሚፈነዳ ቦምብ ነበር።
ወላጆቼ የጤንነቴ ጉዳይ ከመጠን በላይ ያስጨንቃቸው ነበር። እንዳላደርግ የምከለከላቸው በጣም ብዙ ነገሮች ነበሩ። “አትሩጪ!” “በጣም አትሳቂ!” “ጥንቃቄ አድርጊ!” እባል ነበር።
የእኔ ሁኔታ የግሪክ ኦርቶዶክስ አማኝ የሆነችውን እናቴን ከመጠን በላይ ሃይማኖተኛ እንድትሆን አድርጓት ነበር። ሃይማኖታዊ ሥዕሎች እንዲረዷት አጥብቃ ትማጸን ነበር። ያለብኝን ችግር ለማስተካከል ስትል የእምነት ፈውስ በማካሄድ ወደሚታወቁ ሩቅ ገዳማት ይዛኝ ትሄድና የተለያዩ ክታቦችን ታስደርግልኝ ነበር። ምንም ለማይፈይዱት ለእነዚህ ነገሮች ገንዘብዋን አጥፍታለች።
እንዴት እንደማመልከው አልወቅ እንጂ በአምላክ አምናለሁ እንዲሁም እወደዋለሁ። ተስፋ መቁረጥ ሲሰማኝ “አምላክ ሆይ፣ በእርግጥ ካለህና የምትወደኝ ከሆነ እባክህን እርዳኝ” ብዬ እያለቀስኩ እጸልይ ነበር።
መጽናኛ ለማግኘት የነበረኝ ከፍተኛ ጉጉት
ትልቅ ስሆን በተለይም በደሜ ውስጥ ያለው የብረት ክምችት እየጨመረ በመምጣቱ የጤንነቴ ሁኔታ ይበልጥ እያሽቆለቆለ ይሄድ ጀመር። በደም ውስጥ ያለውን የብረት መጠን የሚቀንስ መሣሪያ እጠቀም ነበር። በደሜ ውስጥ ያለውን ብረት ቀስ በቀስ ሰብስቦ እንዲያወጣልኝ ማታ ማታ እስከ ንጋት የሚቆይ መርፌ ከሆዴ በታች እሰካ ነበር። የሚያሰቃይ ቢሆንም ማታ ማታ እንደዚህ ማድረግ ነበረብኝ። ብዙውን ጊዜ እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር በማሳልፋቸው በእነዚያ ሌሊቶች ሞቴን እመኝ ነበር። አምላክ ለእርዳታ ያቀረብኩትን ምልጃ እንዳላደመጠ ተሰማኝ።
አሥራ ስድስት ዓመት ሲሆነኝ የሄቪ ሜታል ሙዚቃ ማዳመጥ ከሚያዘወትሩ ወጣቶች ጋር ገጠምኩ። መጽናኛ ለማግኘት ከነበረኝ ከፍተኛ ጉጉት የተነሳ ጭካኔን፣ ኢሰብዓዊ ድርጊቶችንና ሰይጣናዊ አምልኮን የሚያወድሱ ዘፈኖችን በማዳመጥ መጽናኛ እንደማገኝ ተሰማኝ። ደግሞም በሄድኩበት ክፉ ነገሮችን ስለምመለከት ጽንፈ ዓለምን የሚቆጣጠረው ክፉ ኃይል ነው በሚለው ሐሳብ ተስማማሁ። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ ዕፅና ሰይጣናዊ አምልኮ ችግር እንደሚያስከትል እመለከት ጀመር። ጓደኞቼ ሁልጊዜ ከፖሊስ እንደሸሹ ነው።
በየጊዜው የምወስደው ደም ሰውነቴን አበላሸው። በደሜ ውስጥ የተከማቸው ብረት ፊቴ ላይ ጥቋቁር ነጠብጣቦች ያወጣብኝ ሲሆን ቆዳዬም ገረጣ። ጓደኞቼ አዘውትረው የሚለብሱት ብረታ ብረት የተለጣጠፈበትና የራስ ቅል ሥዕል ያለበት ጥቁር ልብስና የቆዳ ጃኬት መልበሴ መልኬን ሊደብቅልኝ አልቻለም። ደግነቱ አንድም ቀን ዕፅ ወስጄ አላውቅም።
ስለ ሞት፣ ስለ ዕፅ፣ ስለ አጋንንት ስለ መናፍስትነትና ስለ ደም የተዘፈኑትን የሄቪ ሜታል ዘፈኖች ማዳመጤን በቀጠልኩ ቁጥር ሰይጣን ቀስ በቀስ በቁጥጥሩ ሥር እያደረገኝ እንዳለ ተሰማኝ። ማታ ማታ ጭንቀት ስለሚሰማኝ ብዙውን ጊዜ አለቅስ ነበር። በሕይወቴ ውስጥ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀው በጭንቀት ተውጬ በነበረበት በዚህ ጊዜ ነው።
በሕይወቴ ውስጥ ያደረግኩት ከፍተኛ ለውጥ
የ20 ዓመት ወጣት ሳለሁ አንድ ቀን ጓደኛዬ ከይሖዋ ምሥክሮች ያገኘችውን አንድ መጽሐፍ ሰጠችኝ። ርዕሱ መጽሐፍ ቅዱስ—የአምላክ ቃል ነው ወይስ የሰው? ይላል። * እሷ መጽሐፉን ማንበብ አልፈለገችም ነበር፤ እኔ ግን አለፍ አለፍ እያልኩ ሳነበው መሰጠኝ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የአንድን ሰው ሕይወት ሊያሻሽሉ እንደሚችሉ በግልጽ አስቀምጧል። በተጨማሪም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ያሳለፉትን ስደትና ለእምነታቸው ሲሉ ሕይወታቸውን እንኳ መሥዋዕት ለማድረግ ያሳዩትን ፈቃደኝነት ስረዳ በጣም ተደነቅሁ። መጽሐፉን አንብቤ ስጨርስ እነዚህን ነገሮች ለሌሎች ማካፈል ፈለግሁ። ማኖሊስ ከሚባል ሰው ጋር የተዋወቅኩት በዚህ ጊዜ ነው። አንዳንድ ዘመዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናቸው ስለ ይሖዋና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኘው መልእክት ያውቅ ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ወደሚያደርጉበት ቦታ የወሰደኝ ሲሆን እነርሱም በ1990 የበጋ ወራት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠኑኝ ጀመር።
መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና ፈጣሪያችን በእርግጥ እንደሚያስብልንና በብዙዎቻችን ላይ ለሚደርሰው ሕመምና ስቃይ ተጠያቂው እሱ አለመሆኑን ተረዳሁ። (1 ጴጥሮስ 5:7) ኃጢአትንና ሞትን ወደ ዓለም ያመጣው ሰይጣን እንደሆነ እንዲሁም ይሖዋ በቅርቡ ይህን አሮጌ ሥርዓት አስወግዶ ፍጹም በሆነ አዲስ ዓለም በመተካት የሰይጣንን ሥራ እንደሚሽር ተማርኩ። (ዕብራውያን 2:14) ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ሰዎች በገነታዊ ሁኔታዎች ሥር ወደ ሰብዓዊ ፍጽምና እንዲደርሱ ይደረጋል። ከዚያ በኋላ ማንም ሰው “ታምሜአለሁ አይልም።”—ኢሳይያስ 33:24
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከደም ራቁ’ እንደሚል ሥራ 15:20, 29፤ ዘፍጥረት 9:4) ሕሊናዬ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ከፍተኛ የሥነ ምግባር ደረጃዎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች አማካኝነት ሲቀረጽና ሲሰለጥን ደምን በሚመለከት የራሴን ውሳኔ ለማድረግ ተገፋፋሁ። ከዚያ በኋላ ደም ላለመውሰድ ወሰንኩ።
ተረዳሁ። (ዘወትር ደም ካልወሰድኩ በስተቀር በሕይወት መቆየት እንደማልችል ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ሲነገረኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን መመሪያ መታዘዜ በገዛ እጄ መቃብሬን መማስ ይሆንብኛልን? ደም አልወስድም ብል ወላጆቼ ምን ይሰማቸዋል? ዶክተሮቼና ሌሎች የሕክምና ባለሙያዎች ሊያስገድዱኝ ይሞክሩ ይሆን?
ከባድ ውሳኔዎችን ማድረግ
ከልብ በመጸለይ ጭንቀቴን ሁሉ በይሖዋ ላይ ጣልኩ። (መዝሙር 55:22) እንዲሁም ሌላ ዓይነት ሕክምና ለማግኘት ወሰንኩ። ከብዙ ጥረት በኋላ ደም በመውሰድ ፋንታ በብረትና በቫይታሚኖች የበለጸጉ የተመረጡ ምግቦችን መመገብ እንደምችል ተረዳሁ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው የአምላክ ሕግ ጋር ተስማምቼ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ።
ወላጆቼ በዚህ በጣም ተበሳጭተው እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። እነሱ በሕይወት እንድቆይ ለማድረግ ሲሉ ከሕፃንነቴ ጀምሮ የተቻላቸውን ሁሉ ቢያደርጉም ይኸው እዚህ ደርሼ ደም አልወስድም እያልኩ ነው! ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ በዚህ ረገድ የማደርገውን የግል ውሳኔ እንደሚያከብሩ ነገሩኝ።
ከዚያም ደም በመውሰድ ፋንታ አማራጭ የሕክምና መንገዶችን በጥብቅ እንደምከተል በመንገር ሃይማኖታዊ አቋሜን ለሆስፒታሉ የሕክምና ሠራተኞች አስረዳሁ። ዶክተሮቹ ቅር ቢላቸውም ውሳኔዬን ለማክበር ተስማሙ።
ደም ስወስድ በቆየሁባቸው ዓመታት የታላሴሚያ ሕመምተኛ ከሆኑ አንዳንድ ወጣቶች ጋር ጓደኝነት መሥርቼ ነበር። ደም አልወስድም ማለቴ ግራ አጋባቸው። አንዷ ጓደኛዬ “እንግዲያው በቃሬዛ የምትወሰጂበት ጊዜ ሩቅ አይደለም” ስትል በቀልድ መልክ ተናገረች። እንደምሞት ለመናገር አንድ የግሪክኛ አባባል መጠቀምዋ ነበር። የሚያሳዝነው ግን የተበከለ ደም ተሰጥቷቸው ከሞቱት አምስት በሽተኞች መካከል አንዷ እሷ ነበረች!
ከነሐሴ 1991 ጀምሮ ደም ወስጄ አላውቅም። ሲነገር የነበረው ነገር ሁሉ ቀርቶ ይኸው እስከ አሁን በመጠነኛ ጤንነት በሕይወት እኖራለሁ። የያዘኝ የታላሴሚያ በሽታ አልፎ አልፎ የጤና መታወክና የፈለግኩትን እንዳላደርግ አቅም ቢያሳጣኝም በቫይታሚኖችና በብረት የበለጸጉ ምግቦችን ስለምመገብ መጠነኛ ጤንነት አለኝ።
ይሁን እንጂ ከሁሉም በላይ ደስ የሚለው ከፈጣሪዬ ከይሖዋ አምላክ ጋር የቅርብ ወዳጅነት በመመሥረት ትርጉም ያለው ሕይወት መምራት ችያለሁ። ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን ለማሳየት ሐምሌ 1992 ተጠመቅኩ። ከፍተኛ ድጋፍ ከሆነኝ የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጋር እንድተዋወቅ የረዳኝ ማኖሊስ የሚባለው ውድ ጓደኛዬም በዚያው ዕለት ተጠመቀ። ከአንድ ዓመት ከስድስት ወር በኋላ ተጋባን። ከጊዜ በኋላ እናቴና እኅቴ የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች ሲሆኑ በማየቴ ተደስቻለሁ። አባቴ ለይሖዋ ምሥክሮች የነበረው አመለካከት የተቀየረ ሲሆን አልፎ አልፎ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይገኛል።
ሞት ጠላት ቢሆንም ከመጠን ያለፈ ሊፈራ የሚገባው ጠላት አለመሆኑን አውቄያለሁ። (መዝሙር 23:4) በሕይወት ብንኖርም ብንሞትም ለይሖዋ ነው። ሕይወታችን በእሱ እጅ ነው። (ሮሜ 14:8) የምሞትበትን ጊዜ ከመጠባበቅ ስላዳነኝ ምንጊዜም አመሰግነዋለሁ። እንዲያውም የዘላለም ሕይወት ተስፋ እንዲኖረኝ አድርጎኛል!—ራእይ 21:1-4
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.18 ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽናኛ ለማግኘት በጣም እጓጓ ነበር
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከማኖሊስ ጋር