ፍቅር በጠፋበት ትዳር ተጠምዶ መኖር
ፍቅር በጠፋበት ትዳር ተጠምዶ መኖር
“ፍቺ በተስፋፋበት ኅብረተሰብ ውስጥ ደስታ ርቋቸው በፍቺ የሚያከትሙ ትዳሮች ቁጥር ብቻ ሳይሆን ደስታ እየራቃቸው ያሉ ትዳሮች ቁጥርም እየጨመረ መሄዱ አይቀርም።” —በአሜሪካ ለሚገኙ ቤተሰቦች የተቋቋመ ምክር ቤት
ከሕይወት የሚገኘው ደስታም ሆነ ሐዘንና ምሬት በአብዛኛው የሚመነጨው ከአንድ ምንጭ፣ ማለትም ከትዳር እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል። በእርግጥም የትዳርን ያህል ብዙ ደስታ ወይም ብዙ ምሬትና ችግር የማስከተል አቅም ያላቸው ነገሮች በጣም ጥቂቶች ናቸው። ከዚህ ጽሑፍ ጋር በአባሪነት የቀረበው ሳጥን እንደሚያሳየው ትዳር የምሬትና የችግር ምንጭ የሆነባቸው ባለትዳሮች ቁጥር ቀላል አይደለም።
ይሁን እንጂ ስለ ፍቺ የሚቀርቡ አኃዛዊ መረጃዎች የችግሩን ስፋት ሙሉ በሙሉ አያሳዩም። በፍቺ እንዳከተሙት ትዳሮች ወደ አዘቅት ባይወርዱም ማዕበል ባናወጠው ባሕር ላይ ወደፊትም ሆነ ወደኋላ መሄድ የተሳናቸው ትዳሮች በጣም ብዙ ናቸው። ከ30 ዓመት በላይ በትዳር የኖረች አንዲት ሴት “ደስታ የሰፈነበት ቤተሰብ ነበረን፣ ያለፉት 12 ዓመታት ግን በጣም አስቸጋሪ ሆነውብናል” ስትል ገበናዋን ገልጣ ተናግራለች። “ባለቤቴ ስለ ስሜቴ ፈጽሞ ደንታ የለውም። በእርግጥ የእርሱን ያህል በስሜቴ ላይ ክፉ ጠላት የሆነብኝ የለም።” በተመሳሳይም 25 ዓመት ያህል በትዳር የኖረ አንድ ባል እንደሚከተለው በማለት ምሬቱን ገልጿል:- “ባለቤቴ ለእኔ ያላት ፍቅር ተሟጥጦ እንዳለቀ ነግራኛለች። እንደ ደባል ሆነን ብንኖርና በመዝናኛ ጊዜያት የየራሳችንን የተለያየ አቅጣጫ ብንከተል ምናልባት እንቻቻል ይሆናል ትለኛለች።”
እርግጥ፣ እንዲህ ባለው አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ከወደቁት መካከል አንዳንዶቹ ትዳራቸውን ያፈርሳሉ። ለአብዛኞቹ ግን ፍቺ ሊታሰብ የማይችል አማራጭ ነው። ለምን? ዶክተር ካረን ካይዘር እንደሚሉት ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ያላቸው ፍቅር ተሟጥጦ ቢያልቅም በልጆቻቸው፣ ማኅበረሰቡ በሚያሳድርባቸው ጫና፣ በገንዘብ ነክ ችግሮች፣ በቤተ ዘመድ፣ በወዳጆች ወይም በሃይማኖታዊ እምነታቸውና በመሳሰሉት ምክንያቶች ተገድደው አብረው ይኖራሉ። “እነዚህ ባልና ሚስቶች በሕግ አይፋቱ እንጂ በስሜት ከፈቷቸው የትዳር ጓደኞች ጋር አብረው ለመኖር ይመርጣሉ።”
ታዲያ እንደነዚህ ያሉት የእርስ በርስ ዝምድናቸው የቀዘቀዘባቸው ባልና ሚስቶች ይህን የመሰለውን አሳዛኝ ኑሮ የግዴታ ተቀብለው መኖር አለባቸው ማለት ነውን? ከፍቺ ሌላ ያለው አማራጭ ፍቅር በጠፋበት ትዳር መኖር ብቻ ነውን? ብዙዎቹን በችግር የተዋጡ ትዳሮች ፍቺ ከሚያስከትለው ምሬት ብቻ ሳይሆን ፍቅር ማጣት ከሚያስከትለው ሐዘን ጭምር መታደግ እንደሚቻል በተሞክሮ ተረጋግጧል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ፍቺ በዓለም አካባቢ
• አውስትራሊያ:- ከ1960ዎቹ መጀመሪያ ወዲህ የፍቺ መጠን በአራት እጥፍ ጨምሯል።
• ብሪታንያ:- ከ10 ትዳሮች መካከል አራቱ በፍቺ እንደሚያከትሙ ተተንብዮአል።
• ካናዳ እና ጃፓን:- ሲሶ የሚያክሉ ትዳሮች ዕጣቸው ፍቺ ይሆናል።
• ዩናይትድ ስቴትስ:- ከ1970 ወዲህ ትዳር የሚመሠርቱ ባልና ሚስቶች አብረው የመዝለቅ አጋጣሚያቸው 50 በመቶ ሆኗል።
• ዚምባብዌ:- ከአምስት ትዳሮች ውስጥ ሁለቱ በፍቺ ያከትማሉ።