ፍቅር የሚቀዘቅዘው ለምንድን ነው?
ፍቅር የሚቀዘቅዘው ለምንድን ነው?
“እንደተፋቀሩ መኖር በፍቅር የመያዝን ያህል አይቀልም።”—ዶክተር ካረን ካይዘር
ፍቅር ያጡ ትዳሮች እንደ አሸን መፍላታቸው የሚያስደንቅ ነገር ላይሆን ይችላል። ጋብቻ በጣም ውስብስብ የሆነ ሰብዓዊ ዝምድና ሲሆን ብዙዎቹ የሚገቡበት በቂ ዝግጅት ሳያደርጉ ነው። “የመንጃ ፈቃድ ስናወጣ መጠነኛ የሆነ ችሎታ ያለን መሆኑን እንድናሳይ እንጠየቃለን። የጋብቻ የምሥክር ወረቀት ለማግኘት ግን የሚጠየቀው ፊርማ ብቻ ነው” ሲሉ ዶክተር ዲን ኤስ ኢዴል ተናግረዋል።
ስለዚህ እንደለመለሙ የሚኖሩና ደስታ የሰፈነባቸው ትዳሮች በርካታ ቢሆኑም ጥቂት ያይደሉ ትዳሮች ችግር ያጋጥማቸዋል። አንዱ ወይም ሁለቱም ባለትዳሮች ዘላቂ ዝምድና ለመመሥረት የሚያስችል ብቃት ሳይኖራቸው እንዲሁ ከትዳር ሕይወት ብዙ ነገር በመጠበቅ ጋብቻ መሥርተው ይሆናል። ዶክተር ሐሪ ራይስ ሲያብራሩ “ሰዎች መቀራረብ እንደጀመሩ አንዳቸው በሌላው ላይ ከፍተኛ የሆነ የመተማመን ስሜት ያድርባቸዋል” ሲሉ ገልጸዋል። ከጓደኛቸው “በስተቀር የእነርሱ ዓይነት አመለካከት ያለው ሰው በምድር ላይ እንዳልተፈጠረ” ሆኖ ይሰማቸዋል። “እንዲህ ያለው ስሜት እየሞተ የሚሄድበት ጊዜ አለ። በሚሞትበት ጊዜ ደግሞ በትዳሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያስከትላል።”
የሚያስደስተው ግን ብዙዎቹ ትዳሮች እዚህ ደረጃ ላይ አይደርሱም። ይሁንና ለአንዳንድ ትዳሮች ፍቅር መቀዝቀዝ ምክንያት የሚሆኑትን ጥቂት ምክንያቶች እንመልከት።
ብስጭት—“የጠበቅኩት ይህን አልነበረም”
“ጂምን ባገባሁ ጊዜ” ትላለች ሮዝ “በአካባቢያችን ያሉትን በሙሉ የሚያስቀና ፍቅርና መተሳሰብ የሰፈነበት ትዳር የምንመሠርት መስሎኝ ነበር።” ከጊዜ በኋላ ግን የሮዝ ባል እንዳሰበችው ሳይሆን ቀረ። “በመጨረሻ የነበረኝ ተስፋ በሙሉ ተሟጠጠ” ትላለች።
ብዙ ፊልሞች፣ መጻሕፍትና ተወዳጅ ዘፈኖች ፍቅርን ስለው የሚያቀርቡበት መንገድ በገሐዱ ዓለም የሌለ ነው። አንድ ወንድና ሴት ለጋብቻ በሚጠናኑበት ወቅት ሕልማቸው በሙሉ እውን የሆነላቸው መስሎ ሊሰማቸው ይችላል። ከጥቂት ዓመታት የትዳር ኑሮ በኋላ ግን በእውነትም እውን ሊሆን በማይችል ሕልም ውስጥ ነበርኩ ብለው ያስባሉ። ትዳራቸው በልብ ወለድ ታሪኮች ያነበቡትን ዓይነት ካልሆነ ያልተሳካ ሆኖ ይታያቸዋል።
እርግጥ ከጋብቻ ሊጠበቁ የሚገባቸው አንዳንድ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ከትዳር ጓደኛ ፍቅር፣ ትኩረትና ድጋፍ ለማግኘት መጠበቅ ተገቢ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ እንኳን ሳይገኙ ሊቀሩ ይችላሉ። በሕንድ የምትኖረውና ወጣት ሙሽራ የሆነችው ሚና “እንዳገባሁ ሆኖ አይሰማኝም። ብቸኛና የተጣልኩ እንደሆንኩ ይሰማኛል” ብላለች።
አለመጣጣም—“አንድም የምንመሳሰልበት ነገር የለም”
አንዲት ሴት “እኔና ባለቤቴ በሁሉም ነገሮች ላይ ማለት ይቻላል፣ 180 ዲግሪ የተራራቅን ነን” ብላለች። “ለምን አገባሁት ብዬ ሳልፀፀት ያሳለፍኩት አንድም ቀን የለም። ፈጽሞ ልንጣጣም የማንችል ሰዎች ነን።”
አብዛኛውን ጊዜ ባልና ሚስቶች በሚጠናኑበት ወቅት መስሏቸው የነበረውን ያህል የማይመሳሰሉ መሆናቸውን ለመገንዘብ ብዙ ጊዜ አይወስድባቸውም። ዶክተር ኒና ኤስ ፊልድስ “ብዙውን ጊዜ ጋብቻ ባልና ሚስቱ በነጠላነታቸው ዘመን ከራሳቸው ሳይቀር ደብቀው ያቆዩአቸውን ባሕርያት ገሐድ ያወጣል” ሲሉ ጽፈዋል።
በዚህ ምክንያት አንዳንድ ባልና ሚስቶች ከተጋቡ በኋላ ፈጽሞ ሊጣጣሙ የማይችሉ እንደሆኑ ወደ መደምደም ሊደርሱ ይችላሉ። ዶክተር አሮን ቲ ቤክ “አብዛኞቹ ሰዎች መጠነኛ የሆነ የምርጫና የባሕርይ መመሳሰል ቢኖራቸውም ወደ ትዳር የሚገቡት ዋነኛ የሆኑ የአኗኗር፣ የልማድና የአመለካከት ልዩነት ይዘው ነው” ብለዋል። ብዙ ባልና ሚስቶች እነዚህን ልዩነቶች እንዴት እንደሚያስታርቁ አያውቁም።
ግጭት—“ሁልጊዜ እንደተጨቃጨቅን ነው”
ሲንዲ ስለትዳርዋ የመጀመሪያ ዓመታት ስትናገር “ምን ያህል እንጣላ፣ እንጯጯህና ይባስ ብሎ ደግሞ ተኮራርፈን በውስጣችን እንጨስ እንደነበር ስናስበው ይደንቀናል” ትላለች።
በትዳር ውስጥ አለመግባባቶች መነሳታቸው የማይቀር ነው። ግን መፈታት ያለባቸው እንዴት ነው? ዶክተር ዳንኤል ጎልማን “ጤናማ በሆነ ትዳር ውስጥ ባልና ሚስት ቅሬታቸውን ለማሰማት ነፃነት ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ ክርክሩ በሚጋጋልበት ጊዜ ቅሬታው በትዳር ጓደኛ ባሕርይ ላይ ቀጥተኛ ጥቃት እንደመሰንዘር ባለ አፍራሽ መንገድ ይገለጻል” ብለዋል።
ይህ በሚሆንበት ጊዜ የቃላት ልውውጡ ሁለቱም ሽንጣቸውን ገትረው የየግል አመለካከታቸውን የሚከላከሉበት ጦር ሜዳ ይሆናል። ቃላት የሐሳብ መግለጫ መሣሪያዎች መሆናቸው ቀርቶ የመዋጊያ መሣሪያዎች ይሆናሉ። አንድ የጠበብት ቡድን እንዲህ ብሏል:- “ተጋግለው ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ጭቅጭቆች ከሚያስከትሏቸው እጅግ ጎጂ የሆኑ ነገሮች አንዱ ባለትዳሮቹ ሳያስቡት ትዳራቸውን ፈጽሞ ሊገድል የሚችል ነገር መናገራቸው ነው።”
ግድየለሽ መሆን—“ተስፋዬ ተሟጥጧል”
አንዲት ሴት ከአምስት ዓመት የትዳር ሕይወት በኋላ “ትዳራችን እንዲሳካ ሳደርግ የቆየሁትን ጥረት ተስፋ ቆርጬ አቁሜአለሁ። ከዚህ በኋላ ትዳራችን ሊሰምር እንደማይችል ተገንዝቤአለሁ። የሚያሳስበኝ የልጆቻችን ጉዳይ ብቻ ነው” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች።
የፍቅር ትክክለኛ ተቃራኒ ጥላቻ ሳይሆን ግድየለሽ መሆን እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል። በእርግጥም ደንታቢስነት ትዳርን በማፍረስ ረገድ ከጥላቻ በምንም መንገድ አይተናነስም።
የሚያሳዝነው ግን አንዳንድ ባለትዳሮች ፍቅር ከጠፋበት ትዳራቸው ጋር በጣም በመላመዳቸው የተነሳ ምንም ዓይነት ለውጥ ለማድረግ አለመጣራቸው ነው። ለምሳሌ አንድ ባል በትዳር ስላሳለፈው 23 ዓመት ሲናገር “በማትወደው ሥራ ላይ ከመቆየት ጋር ይመሳሰላል” ብሏል። በማከልም “ሁኔታው የሚፈቅድልህን ከማድረግ ሌላ ምንም አማራጭ አይኖርህም” ብሏል። ዌንዲ የተባለች ሚስትም በተመሳሳይ ከሰባት ዓመት ባለቤቷ ጋር ያላትን ዝምድና ለማሻሻል የነበራት ተስፋ ተሟጥጦ እንዳለቀ ተናግራለች። “ብዙ ጊዜ ሞከርኩ። ሁልጊዜም ጥረቴን ከንቱ አድርጎብኛል። ያተረፍኩት ነገር ቢኖር የመንፈስ ጭንቀት ብቻ ነበር። ያ ሁኔታ እንዲመለስ አልፈልግም። ተስፋ ማድረግ ብጀምር መጎዳቴ የማይቀር ነው። ምንም ዓይነት መሻሻል ይኖራል ብዬ ተስፋ ባላደርግ ይሻለኛል። ደስታ እንደማላገኝ አውቃለሁ። ቢሆንም ቢያንስ የመንፈስ ጭንቀት አይደርስብኝም” ብላለች።
ብስጭት፣ አለመጣጣም፣ ግጭትና ግድየለሽ መሆን ለፍቅር መቀዝቀዝ አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዳንዶቹ ናቸው። ሌሎች ምክንያቶችም እንደሚኖሩ የታወቀ ነው። ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ ገጽ 5 ላይ በሚገኘው ሣጥን ውስጥ ሰፍረዋል። ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን፣ ፍቅር በጠፋበት ትዳር ውስጥ ተጠምደው የሚኖሩ ባልና ሚስቶች ተስፋ ይኖራቸው ይሆን?
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ፍቅር ለጠፋበት ትዳር ምክንያት የሚሆኑ ሌሎች ነገሮች
• ገንዘብ፦ “አንድ ሰው፣ ባልና ሚስት አብረው የጋራ ባጀት ማውጣታቸው ተባብረው እንዲሠሩ፣ ለኑሮ የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮች ለማግኘት ገቢያቸውን እንዲያብቃቁና በድካማቸው ፍሬ እንዲደሰቱ በማድረግ አንድ ሆነው እንዲንቀሳቀሱ ይረዳቸዋል ብሎ ሊያስብ ይችላል። ይሁን እንጂ እዚህም ላይ ባልና ሚስቱን ለጋራ ዓላማ ሊያስተሳስራቸው ይገባ የነበረው ነገር አብዛኛውን ጊዜ ሲያለያያቸው ይታያል።”—ዶክተር አሮን ቲ ቤክ
• ወላጅነት፦ “67 በመቶ የሚሆኑ ባልና ሚስቶች የመጀመሪያ ልጃቸው ከተወለደ በኋላ ከትዳራቸው ያገኙ የነበረው እርካታ በከፍተኛ ደረጃ እንደቀነሰ አስተውለናል። በመካከላቸው የሚነሳው ግጭት በስምንት እጥፍ አድጓል። በተወሰነ ደረጃ ለዚህ ምክንያት የሚሆነው ነገር ወላጆች በጣም የሚደክማቸው መሆኑና ለራሳቸው የሚያውሉት ጊዜ የሚያጥርባቸው መሆኑ ነው።”—ዶክተር ጆን ጎትማን
• ማታለል፦ “ለትዳር ጓደኛ ታማኝ አለመሆን አብዛኛውን ጊዜ ማታለልን የሚጨምር ሲሆን አታላይነት ደግሞ እምነት ማጉደል ነው። መተማመን የሁሉም ዘላቂ የሆኑና የተሳኩ ትዳሮች ዋነኛ ባሕርይ እንደሆነ የተረጋገጠ በመሆኑ ማታለል የጋብቻን ዝምድና ሊያፈርስ የሚችል መሆኑ ሊያስደንቅ ይገባልን?”—ዶክተር ኒና ኤስ ፊልድስ
• ወሲባዊ ግንኙነት:- “ፍቺ የሚጠይቁ ብዙ ባልና ሚስት ለበርካታ ዓመታት ወሲባዊ ግንኙነት ከማድረግ ተከላክለው የቆዩ መሆናቸው በጣም የተለመደ ነው። አንዳንዶቹ እንዲያውም ከመጀመሪያ ጀምሮ የሰመረ ወሲባዊ ግንኙነት ያልነበራቸው ሲሆኑ ለሌሎቹ ደግሞ ወሲባዊ ግንኙነት የራስን አካላዊ ፍላጎት መወጫ ከመሆን አላለፈም።”—ጁዲት ኤስ ዋለርስታይን፣ ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ልጆች የሚነኩት እንዴት ነው?
የትዳራችሁ ሁኔታ ልጆቻችሁን ሊነካ ይችላል? በባለትዳሮች ላይ 20 ዓመት ያህል የፈጀ ጥናት ያደረጉት ዶክተር ጆን ጎትማን እንደሚሉት ከሆነ መልሱ አዎን ነው። “እያንዳንዳቸው አሥር ዓመት በፈጁ ሁለት ጥናቶች በትዳራቸው የማይደሰቱ ወላጆች ያሏቸው ልጆች በጨዋታ ጊዜ የሚኖራቸው የልብ ምት ከፍተኛ እንደሆነና ራሳቸውንም ማረጋጋት እንደማይችሉ ተገንዝበናል። የትዳር ችግር እየቆየ ሲሄድ የልጆቹ ብልህነት መጠን (IQ) ምንም ያህል ቢሆን የትምህርት ቤት ውጤታቸው እያሽቆለቆለ እንዲሄድ ያደርጋል” ብለዋል። በአንጻሩ ደግሞ ተግባብተው የሚኖሩ ወላጆች ያሏቸው ልጆች “ሌሎች ሰዎችን እንዴት በአክብሮት እንደሚይዙና እንዴት ስሜታቸውን እንደሚቆጣጠሩ ከወላጆቻቸው ስለሚማሩ በትምህርታቸውም ሆነ በማኅበራዊ ግንኙነታቸው የተሻሉ ይሆናሉ” ሲሉ ዶክተር ጎትማን ገልጸዋል።