ተስፋ ቢስ የነበርኩ ቢሆንም አሁን ደስተኛ ሆኛለሁ
ተስፋ ቢስ የነበርኩ ቢሆንም አሁን ደስተኛ ሆኛለሁ
ቢሴንቴ ጎንዛሌዝ እንደተናገረው
ጎረቤቶቼ በራሴ ላይ አራት ጥይት ብተኩስም አለመሞቴን ሲሰሙ፣ ከሰው በላይ የሆነ ችሎታ እንዳለው አስመስሎ በሚተውን አንድ ታዋቂ የፊልም ተዋናይ ስም (ሱፐርማን) ይጠሩኝ ጀመር። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እንዲህ ዓይነት ችሎታ አልነበረኝም። እስቲ ሕይወቴን በገዛ እጄ ለማጥፋት የተነሳሁት ለምን እንደሆነ ልንገራችሁ።
በ1951 በኢኳዶር በምትገኘው በጉዋያኪል ተወለድኩ። ወላጆቼ ከዘጠኝ ልጆቻቸው ጋር የሚኖሩት ወረራ ተብሎ በሚጠራ ባሕር አካባቢ በሚገኝ ሥፍራ ነበር። ድሃ የሆኑ ቤተሰቦች አካባቢውን ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ “ወርረው” የቆርቆሮ ጣሪያ ያለው የቀርከሃ ቤት በመሥራት በዚያ ይኖሩ ነበር። ቤታቸውን የሚሠሩት ማንግሮቭ የሚባል ዛፍ በሚበቅልበት ረግረጋማ በሆነ አካባቢ ስለሆነ ቤቶቹ የሚገነቡት ከመሬት ከፍ ብሎ በተሠራ የእንጨት ርብራብ ላይ ነበር። ኤሌክትሪክ አልነበረንም። ምግባችንን የምናበስለው በከሰል ምድጃ ሲሆን የሚጠጣ ውኃ የምንቀዳው ከሰፈራችን አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኝ ቦታ ነበር።
ታላላቆቼ ቤተሰባችንን ለመደጎም ገና በለጋ ዕድሜያቸው ሥራ ጀመሩ። እኔም 16 ዓመት ሲሞላኝ ትምህርቴን አቋርጬ ስለነበር በአንድ ፋብሪካ ውስጥ የተላላኪነት ሥራ አገኘሁ። በዚህ ጊዜ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን አልኮል መጠጣትና ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት መፈጸም ጀመርኩ። ባደረግሁት ነገር ሕሊናዬ ሲወቅሰኝ ኃጢአቴን ለመናዘዝ ወደ ቤተ ክርስቲያን እሄዳለሁ። ከተናዘዝኩ በኋላ ቄሱ ምንም ዓይነት መንፈሳዊ እርዳታ ሳያደርጉልኝ “ልጄ፣ ጥሩ ኑዛዜ አድርገሃል” ይሉኝ ነበር። ስለዚህ ያንኑ ኃጢአት ደጋግሜ እሠራ ነበር። የኋላ ኋላ ግን ነጋ ጠባ ኃጢአት መሥራትና መናዘዝ ትርጉም የለሽ ስለሆነብኝ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ተውኩኝ። በዚሁ ጊዜ ላይ በዙሪያዬ ባለው ኅብረተሰብ ውስጥ የሚፈጸመውን የፍትሕ መዛባት አስተዋልኩ። አብዛኛው ሕዝብ ድሃ ሲሆን ኑሮን ለማሸነፍ ይታገላል፤ ጥቂት ባለጠጎች ግን በቅንጦት ይኖሩ ነበር። ሕይወት ትርጉም አልባ ሆነብኝ። ሕይወቴ ዓላማ ቢስ እንደሆነና ለወደፊቱም ተስፋ እንደሌለኝ ተሰማኝ።
ከዚያም አንድ ቀን አራት እህቶቼ በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ጽሑፎችን እንደሚያነቡ አወቅሁ። እኔም ጽሑፎቹን ማንበብ ጀመርኩ። በተለይ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውነት የሚል ርዕስ ያለው አንድ መጽሐፍ ትኩረቴን ሳበው። መጽሐፉ በብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ትምህርቶች ላይ አሳማኝ መልስ ሰጠኝ። ‘እውነት ማለት ይኼ ነው!’ ብዬ ለራሴ መናገሬ ትዝ ይለኛል። ዳሩ ግን በቀጣዮቹ 15 ዓመታት እንዳየሁት ከእውነት ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ፈጽሞ ሌላ ጉዳይ ነው።
በ22 ዓመት ዕድሜዬ በባንክ ውስጥ መሥራት ጀመርኩ። ከዚያም አንድ ቀን አንድ የሥራ ባልደረባዬ እንዴት አድርጎ በምስጢር ከባንኩ ገንዘብ “እንደሚበደር” እና በኋላም “ብድሩን” እንደሚመልስ አሳየኝ። እኔም ለራሴ “ብድር” መስጠት ጀመርኩ፤ በኋላ ግን ብዙ ገንዘብ ከመውሰዴ የተነሳ ወንጀሌን መሸፋፈን የማልችልበት ደረጃ ላይ ደረስኩ። ገንዘቡን መቼም ቢሆን መክፈል እንደማልችል ስለተሰማኝ ተስፋ ቆረጥኩ። ስለዚህ ወንጀሌን ለመናዘዝና ራሴን ለመቅጣት ስል ሕይወቴን ለማጥፋት ወሰንኩ።
ለባንኩ ደብዳቤ ከጻፍኩኝ በኋላ አንዲት ትንሽ ሽጉጥ ገዝቼ በባሕሩ ዳርቻ ሰው ወደሌለበት ቦታ ሄድኩና ሁለት ጊዜ ጭንቅላቴ ላይ፣ ሁለት ጊዜ ደግሞ ደረቴ ላይ ተኮስኩ። ከባድ ጉዳት ቢደርስብኝም አልሞትኩም። አንድ ሰው በብስክሌት ሲያልፍ አግኝቶኝ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል እንድወሰድ አደረገ። ሲሻለኝ በስርቆት ወንጀል ተከሰስኩኝና ወደ እስር ቤት ተላክሁ። ከእስር ቤት
ከተለቀቅሁ በኋላ ከእንግዲህ የምታወቀው በወንጀለኝነት ታሪኬ መሆኑን ሳስበው በሃፍረትና በሐዘን ተዋጥኩ። ከአራት ጥይት በመትረፌ ጎረቤቶቼ ‘ከሰው በላይ የሆነ ችሎታ ያለው’ የሚል ትርጉም ባለው ቅጽል ስም (ሱፐርማን) ይጠሩኝ ጀመር።የመለወጥ አጋጣሚ አገኘሁ
በዚሁ ጊዜ ላይ ፖል ሳንቼዝ የተባለ አንድ የይሖዋ ምሥክር አነጋገረኝ። ፖል ሚስዮናዊ ሲሆን መጀመሪያ ሲያነጋግረኝ የማረከኝ ብሩህ ፈገግታው ነበር። በጣም ደስተኛና ብሩህ አመለካከት ያለው ሰው ስለነበረ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳጠና ያቀረበልኝን ግብዣ ተቀበልኩ። ‘ምናልባት እኔም ደስታ እንዳገኝና ሕይወቴ ትርጉም እንዲኖረው ይረዳኝ ይሆናል’ ብዬ አሰብኩ።
ፖል ባደረገልኝ እርዳታ፣ አምላክ ለሰዎች ዓላማ እንዳለው እንዲሁም እሱን የሚወዱትና የሚታዘዙት ሰዎች በምድራዊ ገነት የሚኖሩበት ቀን እንደሚመጣ ተገነዘብኩ። (መዝሙር 37:29) በተጨማሪም የፍትሕ መዛባትና ድህነት አምላክ ያመጣቸው ነገሮች ሳይሆኑ የሰው ልጅ በአምላክ ላይ በማመጹ ምክንያት የመጡ መሆናቸውን ተረዳሁ። (ዘዳግም 32:4, 5) እነዚህ እውነቶች በሕይወቴ ውስጥ ብርሃን ፈነጠቁልኝ። ይሁንና ባሕሪዬን መለወጥ መጽሐፍ ቅዱስን እንደማጥናቱ ቀላል አልነበረም።
በአንድ ኩባንያ ውስጥ በገንዘብ ያዥነት ተቀጠርኩ። አሁንም እንደገና በፈተናው ተሸነፍኩና መስረቅ ጀመርኩ። ስርቆቴን መደበቅ የማልችልበት ደረጃ ላይ ስደርስ ኢኳዶር ውስጥ ወደሚገኝ ሌላ ከተማ ሸሸሁና ለአንድ ዓመት ከተደበቅሁ በኋላ ከአገር ለመውጣት ሞከርሁ፤ ይሁን እንጂ ሊሳካልኝ ስላልቻለ ወደ ቀድሞ ቤቴ ተመለስኩ።
ፖል እንደገና አገኘኝና ጥናታችንን ቀጠልን። በዚህ ጊዜ ግን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወቴ ውስጥ በሥራ ላይ ለማዋልና ይሖዋን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። ለዚህም ስል ቀደም ሲል የፈጸምኩትን እምነት የማጉደል ድርጊት ለፖል ነገርኩት፤ እሱም ግልጽ ምክር ሰጠኝ። “ይሰርቅ የነበረ ከእንግዲህ አይስረቅ፤ ነገር ግን . . . በገዛ እጆቹ በጎ የሆነውን እየሠራ ለማግኘት ይድከም” እንደሚለው እንደ ኤፌሶን 4:28 ያሉ ጥቅሶችን አሳየኝ። ስለዚህ ሕግ ፊት ቀርቤ መስረቄን መናዘዝና ድርጊቱ የሚያስከትልብኝን ቅጣት መቀበል እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።
ስለዚህ ሁኔታ እያሰብኩ እያለ በግሌ ሠዓሊ ሆኜ መሥራት ጀመርኩ። አንድ ቀን አንድ ሰው ወደምሠራበት ቦታ መጣና የሠራሁትን ሥዕል እንደወደደው ገለጸልኝ። ይሁን እንጂ ግለሰቡ የወንጀል መርማሪ ስለነበር በተገኘሁበት ተይዤ እንድቀርብ የሚያዝዝ የፍርድ ቤት ወረቀት አሳየኝ። ስለዚህ እንደገና ፍርድ ቤት ቀረብኩና ወኅኒ ወረድኩ። ፖል እስር ቤት ድረስ መጥቶ ይጠይቀኝ ነበር፤ “እኔን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር ስትል በመልፋትህ እንድትቆጭ አላደርግም” ስል ቃል ገባሁለት። እስር ቤት ሆኜ ከፖል ጋር ማጥናቴን ቀጠልኩ።
ከልቤ መሆኑን በተግባር አሳየሁ
ከእስር ቤት ስለቀቅ ይሖዋን በሙሉ ልቤ ለማገልገል ቆርጬ ነበር፤ ውሳኔዬ ከልቤ መሆኑንም በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በተግባር አሳየሁ። በ1988 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ። ያባከንኩትን ጊዜ ለማካካስ ስል አቅኚ ሆኜ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ፤ ምሥራቹን በቡድን ለተደራጁ ወጣት ወሮበሎች ለማድረስ ልዩ ጥረት አደርግ ነበር።
አንድ የወሮበሎች ቡድን የመንግሥት አዳራሻችን ግድግዳ ላይ ብዙ ጊዜ እየሞነጫጨረ ያበላሽብን ነበር። የቡድኑን አባላትና መኖሪያቸውን ስለማውቅ ቤታቸው ድረስ ሄድኩና የመንግሥት አዳራሹ የተሠራበትን ዓላማ በመግለጽ ንብረታችንን እንዲያከብሩልን በደግነት ጠየቅኳቸው። ከዚያ ወዲህ ተሞነጫጭሮብን አያውቅም።
ቆየት ብሎ አዳራሹን በምናድስበት ጊዜ የቆየውን ቀለም ቅብ ስንፍቅ ፈርናንዶ የሚባል አንድ ወጣት ወንድም “እንቁራሪቱ” (በስፓንኛ ቋንቋ ላ ራና) የሚል ጽሑፍ አገኘ። ወንድም ወደ ጽሑፉ እያመለከተ “ቅጽል ስሜ ነበር” አለን። ፈርናንዶ በመንግሥት አዳራሹ ግድግዳ ላይ የቅጽል ስሙን የጻፈው የወሮበሎች ቡድን አባል በነበረበት ጊዜ ሲሆን በዚያን ወቅት ግን ግድግዳው ላይ የሞነጫጨረውን ጽሑፍ እያጠፋ ነበር!
ፈርናንዶን መጀመሪያ ያገኘሁት ዕለት ዕፅ ወስዶ ናላው ዞሮ ነበር። እናቱ ከዚህ ልማድ እንዲላቀቅ ሁለት ጊዜ ወደ ተሃድሶ ማዕከሎች እንዲገባ ብታደርግም አልተሳካላትም። በመሆኑም እሱን ለመርዳት የምታደርገውን ጥረት እርግፍ አድርጋ በመተው ቤቱን ጥላለት ሄደች። ፈርናንዶ ለዕፅ መግዣ ገንዘብ ለማግኘት ሲል ዋጋ ሊያወጣለት የሚችለውን ነገር ሁሉ ሌላው ቀርቶ መዝጊያዎቹን፣ መስኮቶቹንና የቤቱን ጣራ ሳይቀር ሸጧል። አንድ ቀን በመንገድ ላይ አገኘሁትና ለስላሳ መጠጥ ጋብዤው መጽሐፍ ቅዱስ ከእኔ ጋር እንዲያጠና
ሐሳብ አቀረብኩለት። እሱም ግብዣዬን ተቀብሎ ለእውነት ጥሩ ምላሽ ሲሰጥ በጣም ተደሰትኩ። የነበረበትን የወሮበሎች ቡድን ትቶ ወጣ፤ ዕፅ የመውሰድ ልማዱንም አቋረጠ። ቀጥሎም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት የጀመረ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ተጠመቀ።ፈርናንዶና እኔ ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ስንሰብክ ሰዎች ብዙ ጊዜ ስለሚያውቁን በቅጽል ስማችን ይጠሩናል፤ አክለውም ቤታቸው የመጣነው ለምን እንደሆነ ይጠይቁን ነበር። የቀድሞው የወሮበሎች ቡድን አባልና የቀድሞው ሌባ መጽሐፍ ቅዱስ በእጃችን ይዘን ልናነጋግራቸው ቤታቸው በመሄዳችን ይገረሙ ነበር።
አንድ ቀን ፈርናንዶና እኔ ከቤት ወደ ቤት ስናገለግል እኔ ለአንድ ሰው እየመሠከርኩ ሳለሁ እሱ ደግሞ ከሰውየው ጎረቤት ጋር እየተነጋገረ ነበር። የማነጋግረው ሰው ወደ ፈርናንዶ እያመለከተ “ያንን ሰው አየኸው? አንድ ጊዜ ራሴ ላይ ሽጉጥ ደግኖ አስፈራርቶኝ ነበር” አለኝ። እኔም ፈርናንዶ የቀድሞ አኗኗሩን ትቶ አሁን ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር ተስማምቶ እየኖረ መሆኑን በመግለጽ አረጋጋሁት። ፈርናንዶ ሲያነጋግረው ከነበረው ሰው ጋር ውይይቱን ሲጨርስ ጠራሁትና እኔ እያነጋገርኩት ከነበረው ሰው ጋር አስተዋወቅሁት። ሰውየውም “ይህን ያህል መለወጥ በመቻልህ ልትመሰገን ይገባሃል” አለው።
ፈርናንዶና እኔ ብዙ ጊዜ እንደዚህ ያለ አስተያየት ተሰጥቶናል። እነዚህ አስተያየቶች ጥሩ ምሥክርነት ለመስጠት መንገድ ስለሚከፍቱልን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማግኘት ችለናል። በእርግጥም፣ እኔም ሆንኩ ፈርናንዶ እንደ ይሖዋ ምሥክር ለመታወቅ በመብቃታችን ክብር ይሰማናል።
በሕይወቴ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተልኝ
በ2001 ሃምሳ ዓመት ሲሞላኝ፣ በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት እንድካፈል የተጋበዝኩ ሲሆን ትምህርቱ የሚሰጠው ፔሩ ውስጥ ነበር። በሁኔታው በጣም ብገረምም ይህን መብት በማግኘቴ በደስታ ፈነጠዝኩ። ይህ ትምህርት ቤት፣ ብቃቱን ያሟሉ የይሖዋ ምሥክሮችን በአገልግሎታቸው ለማሠልጠን ስምንት ሳምንታት የሚፈጅ ጥልቀት ያለው መንፈሳዊ ትምህርት ይሰጣል።
ከአንድ ነገር በቀር፣ ይኸውም ገና ሳስበው በጣም ከሚያስፈራኝ በሕዝብ ፊት ከመናገር ሌላ በትምህርት ቤቱ ያገኘሁት ሥልጠና በሙሉ በጣም አስደሳች ነበር። ወጣት ከሆኑት ተማሪዎች ውስጥ ብዙዎቹ በጣም ጥሩ ንግግር የሚሰጡ ሲሆን በልበ ሙሉነት መናገር ይችሉ ነበር። እኔ ግን የመጀመሪያውን ንግግሬን ለማቅረብ ገና መድረኩ ላይ ስወጣ ከልጅነቴ ጀምሮ ያስቸግረኝ የነበረው የበታችነት ስሜት መጣብኝ። እግሮቼ ተብረከረኩ፤ ላብ ያሰመጣቸው እጆቼም ተንቀጠቀጡ። ድምፄም በፍርሃት ይርገበገብ ጀመር። ይሁንና ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱና አፍቃሪ በሆኑ ወንድሞች አማካኝነት አጠንክሮኛል። ከአስተማሪዎቻችን አንዱ ለእኔ በግል ትኩረት በመስጠት ከትምህርት ሰዓት ውጪ ጊዜ ወስዶ የማቀርባቸውን ንግግሮች እንድዘጋጅ ይረዳኝ ነበር። ከሁሉ በላይ በይሖዋ እንድተማመን አስተምሮኛል። በሥልጠናው መጨረሻ ላይ፣ በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ በሕዝብ ፊት ቀርቤ በመናገር ደስታ ማግኘት ቻልኩ።
ተረጋግቼና በልበ ሙሉነት የመናገር ችሎታዬ ትልቅ ፈተና ላይ የወደቀው በጓያኪል በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ወቅት ነበር። በ25,000 ሕዝብ ፊት ቀርቤ እንዴት ወደ እውነት እንደመጣሁ ተሞክሮዬን ተናገርኩ። ይሁን እንጂ በምናገርበት ጊዜ ብዙ ሰዎችን ለማበረታታት አጋጣሚ በማግኘቴ በስሜት ተውጬ ስለነበር ድምፄ መንቀጥቀጥ ጀመረ። ከስብሰባው በኋላ ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ ወደ እኔ ቀርቦ “ወንድም ጎንዛሌዝ፣ ተሞክሮህን ስትናገር በተሰብሳቢው መሃል ያላለቀሰ ሰው አልነበረም” አለኝ። ከምንም በላይ የፈለግሁት የቀድሞ አኗኗራቸውን ለመተው እየታገሉ ላሉ ሰዎች የእኔ ታሪክ የብርታት ምንጭ እንዲሆንላቸው ነበር።
አሁን ሽማግሌና የዘወትር አቅኚ ሆኜ አገለግላለሁ፤ እንዲሁም 16 ሰዎች ትክክለኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንዲያውቁ በመርዳት ደስታ አግኝቻለሁ። ወላጆቼና አራቱ እህቶቼም ሕይወታቸውን ለይሖዋ ወስነው በመጠመቃቸው በጣም ተደስቻለሁ። እናቴ በ2001 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ለአምላክ ታማኝ ሆና ኖራለች። ይሖዋ እንዳውቀው ስለፈቀደልኝ እጅግ አመሰግነዋለሁ፤ ለእሱ ያለኝን አድናቆት ለመግለጽ ሌሎችም እንደ እኔ ወደ እሱ እንዲቀርቡ ከመርዳት የተሻለ መንገድ ያለ አይመስለኝም።—ያዕቆብ 4:8
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እንቁራሪቱ በመባል የሚጠራውና እውነትን እንዲያውቅ የረዳሁት ቀድሞ የወሮበሎች ቡድን አባል የነበረው ፈርናንዶ
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፖል ሳንቼዝ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኝ ሚስዮናዊ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቢሴንቴ ጎንዛሌዝ በአሁኑ ጊዜ