በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት እንድንጥል የሚያደርጉ ምክንያቶች
1. ታሪኮቹ ትክክል መሆናቸው
የተሳሳቱ መረጃዎችን በያዘ መጽሐፍ ላይ እምነት መጣል አስቸጋሪ ነው። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በ1800ዎቹ ዓመታት እንደተካሄደ ወይም የዩናይትድ ስቴትስን ፕሬዚዳንት ንጉሥ ብሎ የሚጠራ አንድ ዘመናዊ የታሪክ መጽሐፍ እያነበብክ ነው እንበል። መጽሐፉ እንዲህ ያሉ የተሳሳቱ ሐሳቦችን የያዘ መሆኑ የአጠቃላዩን መጽሐፍ ተዓማኒነት እንድትጠራጠር አያደርግህም?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ታሪኮች ትክክለኛ ናቸው የሚለውን ሐሳብ ውድቅ ማድረግ የቻለ አንድም ሰው የለም። መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወት የነበሩ ሰዎችንና በእርግጥ የተፈጸሙ ክንውኖችን ይጠቅሳል።
ሰዎች።
የመጽሐፍ ቅዱስ ተቺዎች ኢየሱስ እንዲሰቀል አሳልፎ የሰጠው ሮማዊ የይሁዳ ገዢ ጳንጥዮስ ጲላጦስ በእርግጥ በሕይወት የነበረ ሰው መሆኑን ተጠራጥረው ነበር። (ማቴዎስ 27:1-26) ይሁንና በ1961 በሜድትራንያን የወደብ ከተማ በሆነችው በቂሳርያ፣ ጲላጦስ በአንድ ወቅት የይሁዳ ገዢ እንደነበረ የሚያሳይ ጽሑፍ የተቀረጸበት ድንጋይ ተገኝቷል።
ከ1993 በፊት፣ ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ለመሆን የበቃው ደፋሩ የበግ እረኛ ዳዊት በታሪክ የነበረ ሰው መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጪ አልነበረም። ይሁን እንጂ በዚያ ዓመት አርኪኦሎጂስቶች በሰሜናዊ እስራኤል የተቀረጸ ጽሑፍ ያለበት ጥቁር ድንጋይ በቁፋሮ አገኙ። ባለሙያዎች እንደሚሉት በድንጋዩ ላይ ያለው ጽሑፍ “የዳዊት ቤት” እና “የእስራኤል ንጉሥ” የሚሉትን ቃላት የያዘ ሲሆን ከክርስቶስ ልደት በፊት በዘጠነኛው መቶ ዘመን እንደተጻፈም ታውቋል።
ክንውኖች።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በርካታ ምሑራን ኤዶማውያን ከእስራኤላውያን ጋር እንደተዋጉ ስለሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ትክክለኛነት ይጠራጠሩ ነበር። (2 ሳሙኤል 8:13, 14) እነዚህ ምሑራን ኤዶም ከብዙ ጊዜያት በኋላ ካልሆነ በስተቀር በዳዊት ዘመን በከብት አርቢነት የሚተዳደር ተራ ኅብረተሰብ ስለነበረ በበቂ ሁኔታ ተደራጅቶ በእስራኤል ላይ ስጋት ሊፈጥር አይችልም ብለው ይከራከሩ ነበር። ይሁን እንጂ በቅርብ ጊዜ የተደረገ የመሬት ቁፋሮ እንደሚጠቁመው “በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እንደተገለጸው ኤዶም በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ጀምሮ የሠለጠነ ኅብረተሰብ ነበር” በማለት ቢብሊካል አርኪኦሎጂ ሪቪው የተሰኘ መጽሔት ይናገራል።
ትክክለኛ የማዕረግ ስሞች።
መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈባቸው 1,600 ዓመታት ውስጥ በዓለም መድረክ ላይ ብቅ ያሉ ብዙ ገዢዎች ነበሩ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ገዢዎች በሚናገርበት ቦታ ላይ ሁልጊዜ ትክክለኛውን የማዕረግ ስም ይጠቀማል። ለምሳሌ ያህል፣ ሄሮድስ አንቲጳስ ‘የአራተኛው ክፍል ገዥ’ ሲሆን ጋልዮስ ደግሞ “አገረ ገዥ” እንደነበሩ በትክክል ይገልጻል። (ሉቃስ 3:1፤ የሐዋርያት ሥራ 18:12 የ1954 ትርጉም) ዕዝራ 5:6 [የ1954 ትርጉም] ከኤፍራጥስ ‘ወንዝ ማዶ’ የምትገኝ የአንዲት የፋርስ ግዛት ገዢ ስለነበረ ተንትናይ ስለሚባል ሰው ይናገራል። በአራተኛው መቶ ዘመን ከክርስቶስ ልደት በፊት የተቀረጸ አንድ ሳንቲምም ማዛዩስ “ከወንዙ ማዶ” የሚገኘው የፋርስ ግዛት አስተዳዳሪ እንደነበረ በመናገር ተመሳሳይ አገላለጽ ይጠቀማል።
መጽሐፍ ቅዱስ ዝርዝር በሆኑ ጉዳዮች ረገድ ትክክለኛ ዘገባ ማስፈሩ ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ጥቃቅን በሚመስሉ ጉዳዮችም እንኳ ሳይቀር ሊታመኑ የሚችሉ መሆናቸው በጻፏቸው ሌሎች ነገሮች ላይ ያለንን እምነት አያጠናክርልንም?