ሚስጥር ለማስጠበቅ የተደረገ ትግል—አንተንም የሚመለከት ጉዳይ
ሚስጥር ለማስጠበቅ የተደረገ ትግል—አንተንም የሚመለከት ጉዳይ
ተዘበራርቀው የተቀመጡ ፊደሎችን በማስተካከል ትክክለኛ ቃላትን የመፍጠር ጨዋታ (አናግራም) ተጫውተህ ታውቃለህ? በኢንተርኔት አማካኝነት ዕቃ ገዝተህ ወይም ኮምፒውተር ተጠቅመህ የባንክ ሒሳብህን አንቀሳቅሰህ ታውቃለህ? የምታውቅ ከሆነ አንተም ኮድ፣ ሳይፈር፣ ኢንክሪፕሽንና ዲክሪፕሽን የሚባሉ ሚስጥር ለመጠበቅ የሚረዱ ዘዴዎችን ተጠቅመሃል ማለት ነው።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሚስጥራዊ ኮዶችን ይጠቀሙ የነበሩት መንግሥታት፣ አምባሳደሮች፣ ሰላዮችና ወታደራዊ ባለሥልጣናት ብቻ ነበሩ። አሁን ግን ሁኔታው ተለውጧል። ኮምፒውተርና ኢንተርኔት ከመጣ ወዲህ በጣም አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በሚስጥር ለመጠበቅ የተለያዩ ዘዴዎች ጥቅም ላይ ውለዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ተጠቃሚው መረጃውን ለማግኘት በሚሞክርበት ጊዜ ሁሉ እንደ ፓስወርድ ያሉ ነገሮች እንዲያስገባ ይጠየቃል። በእርግጥም ሚስጥር መጠበቅ የአሁኑን ያህል የዕለት ተዕለት የሕይወት ክፍል የሆነበት ጊዜ የለም።
በዚህ ምክንያት ሁላችንም እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን የተገባ ነው፦ መረጃዎቼን በሚስጥር ለመያዝ የምጠቀምበት ዘዴ ምን ያህል አስተማማኝ ነው? ይበልጥ አስተማማኝ እንዲሆንስ ምን ማድረግ እችላለሁ? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ከመመልከታችን በፊት በሚስጥር መልእክት በሚልኩና ሚስጥሩን ለመፍታት በሚሞክሩት ሰዎች መካከል ለረጅም ዓመታት ሲካሄድ የቆየውን ትግል ለአንድ አፍታ እንመልከት፤ ይህ ትግል ሐሳብን በጽሑፍ ማስፈር ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነበረ ነው ለማለት ይቻላል።
ሚስጥራዊ ጽሑፎች
ረጅም ዘመን ያስቆጠረው አንደኛው የሚስጥር አጻጻፍ ዘዴ ስቴጋኖግራፊ ወይም “ስውር ጽሑፍ” ይባላል። ሰዎች ይህን ዘዴ የሚጠቀሙት ሌሎች ሚስጥራዊ መልእክት መኖሩን እንዳይጠረጥሩ ለማድረግ ነው። ሄሮዶተስ የተባለው ጥንታዊ ታሪክ ጸሐፊ የዘገበውን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንመልከት፦ በስደት የሚኖር አንድ ግሪካዊ፣ የፋርስ መንግሥት የትውልድ አገሩን ለመውረር በዝግጅት ላይ መሆኑን
አስተዋለ። ይህ ሰው ወገኖቹን ለማስጠንቀቅ ስለፈለገ በእንጨት ላይ መልእክቱን ጽፎ ጽሑፉን ለመሰወር ሲል እንጨቶቹን ሰም ቀባቸው፤ የሚገርመው ነገር ሮማውያንም በዚህ ዘዴ ይጠቀሙ ነበር። ሄሮዶተስ እንደተረከው፣ ይህ ግሪካዊ ቀላል ዘዴ ተጠቅሞ የአገሩን ሰዎች በማስጠንቀቁ ምክንያት የፋርሱ ንጉሥ ጠረክሲስ ያሰበውን ድንገተኛ ወረራ ማካሄድ አልቻለም፤ በዚህም ሳቢያ ሠራዊቱ ድል ሊመታ ችሏል።በዘመናችን ስቴጋኖግራፊ ጥቅም ላይ ከሚውልባቸው ዘዴዎች መካከል የባለቤትነት መብትን ለማስከበር ሲባል በሰነዶች ላይ ስውር ምልክቶችን ማድረግና ምስሎችን ወደ አነስተኛ ነጥብነት (ማይክሮዶት) መቀየር ይገኙበታል። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ማይክሮዶት ጥቅም ላይ የዋለው ፎቶግራፎችን በጣም አሳንሶ ነጥብ እንዲያክሉ በማድረግ ነው። መልእክቱ የተላከለት ሰው ነጥቡን በማሳደግ ፎቶግራፉን መመልከት ይችላል። በዛሬው ጊዜ ሕገወጥ የብልግና ሥዕሎችን የሚሸጡ ሰዎች ተመሳሳይ ዘዴ ይጠቀማሉ። እነዚህ ሰዎች በኮምፒውተር ፕሮግራሞች በመታገዝ የብልግና ሥዕሎችን ምንም ነውር የሌለባቸው ምስሎች፣ ጽሑፎች ወይም የድምፅ ፋይሎች አስመስለው ይልካሉ።
ይህ ዘዴ ስውር መልእክት መኖሩን እንኳ ስለማያስጠረጥር ላኪውም ሆነ ተቀባዩ የሌሎችን ትኩረት አይስቡም። ስውር መልእክት መኖሩ ከታወቀ ግን ላኪው መልእክቱን ለመሰወር ኢንክሪፕሽን የተባለውን ዘዴ ካልተጠቀመ በስተቀር ያገኘው ሰው መልእክቱን ያለምንም ችግር ማንበብ ይችላል።
ትርጉሙን መሰወር
ክሪፕቶሎጂ ወይም “ስውር ቃል” መልእክቱን ሳይሆን የመልእክቱን ትርጉም በመሰወር የመልእክት ልውውጦችን ሚስጥራዊ ማድረግ የሚቻልበት ዘዴ ነው። ይህ ዘዴ ቀደም ሲል ሁለት ወገኖች ባወጡት ደንብ መሠረት መረጃዎችን ማዘበራረቅና እንደገና ማስተካከል ይጠይቃል፤ የመልእክቱን ይዘት በትክክል ማወቅ የሚችሉት ሚስጥሩ እንዴት እንደሚፈታ የተነገራቸው ሰዎች ብቻ ናቸው።
የጥንቶቹ ስፓርታውያን ስኪታሊ ተብሎ የሚጠራ ተራ የሆነ አጭር ዱላ በመጠቀም ሚስጥራዊ መልእክቶችን ይላላኩ ነበር። ሚስጥሩን የሚጽፈው ሰው ቀጠን ያለ ረጅም ቆዳ ወይም ብራና በዱላው ላይ ይጠመጥምና መልእክቱን ከላይ ወደታች ይጽፋል። ቆዳው ሲፈታ የሚታየው ነገር ቢኖር ምንም ትርጉም የማይሰጡ ፊደሎች ብቻ ነው። መልእክቱ የተላከለት ሰው ከመጀመሪያው ጋር እኩል የሆነ ውፍረት ባለው ሌላ ዱላ ላይ ቆዳውን መልሶ ጠቅልሎ መልእክቱን በቀላሉ ማንበብ ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ መልእክተኛው ጽሑፉን በውስጠኛው በኩል አድርጎ ቆዳውን ልክ እንደ ቀበቶ በወገቡ ላይ በማሰር ስቴጋኖግራፊ የተባለውን ዘዴ ሊጠቀም ይችላል።
ጁሊየስ ቄሳር ከጦር ሜዳ መልእክቶችን ሲልክ መልእክቱን ሚስጥራዊ ለማድረግ ሳይፈር ተብሎ የሚጠራውን እያንዳንዱን ፊደል በሌላ የመተካት ቀላል ዘዴ ይጠቀም ነበር። በዚህ ዘዴ መሠረት መልእክት ሲላክ የፊደል ቅደም ተከተል ትልቅ ሚና ይጫወታል። ለምሳሌ ያህል፣ ሀ ለመጻፍ ሦስት ፊደል ተዘሎ መ ይጻፋል፤ ለ ለመጻፍ ደግሞ ሠ ይጻፋል።
ሚስጥራዊ የአጻጻፍ ዘዴ በአውሮፓ የተሐድሶ ዘመን ይበልጥ ተራቀቀ። ይህን ዘዴ ይበልጥ እንዲራቀቅ ካደረጉት በርካታ ግለሰቦች መካከል በ1523 የተወለደው ብሌዝ ደ ቪኜረ የተባለ ፈረንሳዊ ዲፕሎማት ይገኝበታል። ቪኜረ ቀደም ሲል የተፈለሰፈውን ሳይፈር የተባለ ዘዴ በመጠቀም፣ በርካታ ፊደሎችን እያፈራረቁ ውስብስብ በሆነ መንገድ ሚስጥራዊ መልእክቶችን መጻፍ እንደሚቻል ሐሳብ አቀረበ። ይህ ዘዴው ሊደረስበት የማይቻል ተብሎ ይታሰብ ስለነበረ “ፈጽሞ ሊፈታ የማይችለው ሚስጥራዊ አጻጻፍ” (ለ ሺፍር ኢንደሺፍረበል) የሚል ስም ተሰጥቶት ነበር። ይሁን እንጂ ጽሑፎችን ሚስጥራዊ የማድረጉ ዘዴ በተራቀቀ መጠን ሚስጥሮቹን የመፍታት ዘዴዎችም ይበልጥ እየተራቀቁ መጡ። *
ለምሳሌ ያህል፣ የእስልምና ምሁራን በአረብኛ የተጻፈውን ቁርዓን በሚመረምሩበት ጊዜ አንዳንድ ፊደሎች ከሌሎቹ በበለጠ በብዛት እንደሚገኙ አስተዋሉ። እንዲህ ያለው ሁኔታ በሌሎች ቋንቋዎችም ይታያል። ይህን ማስተዋላቸው በአንድ ሚስጥራዊ ጽሑፍ ውስጥ የተወሰኑ ፊደሎች ወይም ሐረጎች ምን ያህል እንደተደጋገሙ በመቁጠር ፊደሎቹ ወይም ሐረጎቹ ምን ትርጉም እንዳላቸው ለማወቅ የሚያስችል ፍሪክዌንሲ አናሊስስ የተባለ ሚስጥር መፍቻ ዘዴ እንዲያገኙ አስቻላቸው።
በ15ኛው መቶ ዘመን ክሪፕቶግራፊ የአውሮፓ ዲፕሎማቶች ዕለት ተዕለት የሚጠቀሙበት ዘዴ እስከ መሆን ደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ ሚስጥርን ሙሉ በሙሉ ለመጠበቅ የሚያስችል አስተማማኝ ዘዴ ሊሆን አልቻለም። ለምሳሌ ያህል፣ ፍራንስዋ ቪየት የተባለ ፈረንሳዊ በስፔን ቤተ መንግሥት ውስጥ ሚስጥር ይለዋወጡበት የነበረውን ኮድ መፍታት ችሎ ነበር። እንዲያውም ቪየት በዚህ ረገድ በጣም የተሳካለት በመሆኑ የስፔኑ ንጉሥ ዳግማዊ ፊሊፕ ተስፋ ቆርጦ ቪየት ከዲያብሎስ ጋር
ስለተሻረከ በካቶሊክ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት እስከ ማለት ደርሶ ነበር!ቴክኖሎጂ ወደ መድረክ ብቅ አለ
በ20ኛው መቶ ዘመን በተለይ በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ወቅት እጅግ የተራቀቁ መሣሪያዎችን መጠቀም ስለተቻለ ክሪፕቶግራፊ እጅግ ተራቅቆ ነበር፤ ከእነዚህ መሣሪያዎች መካከል ከታይፕ መጻፊያ ጋር ብዙ ተመሳሳይነት ያለው የጀርመኑ ኢኒግማ ይገኝበታል። ፀሐፊው ሐሳቡን ሲጽፍ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚንቀሳቀሱ የሚሽከረከሩ ነገሮች መልእክቱ ሚስጥራዊ እንዲሆን የሚያደርጉ ኮዶችን ያስገባሉ። ከዚያም ጽሑፉ ሞርስ ኮድ በተባለ ሚስጥራዊ መልእክት የማስተላለፊያ ዘዴ ይላክና ተቀባዩ ተመሳሳይ በሆነ በሌላ መሣሪያ አማካኝነት ይፈታዋል። ይሁን እንጂ በሥራ የተሰላቹ ሠራተኞች የሚሠሩት ስህተት ሚስጥር ለመፍታት የሚሞክሩ ሰዎች የሚስጥሩን ቁልፍ ለማግኘት የሚያስችል ፍንጭ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
በዛሬው ጊዜ የባንክ ሥራ የሚከናወነው እንዲሁም ገንዘብ ከቦታ ቦታ የሚዘዋወረውና ክፍያ የሚፈጸመው አልፎ ተርፎም የሕክምና ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶችና መንግሥታት መረጃዎቻቸውን የሚያስቀምጡት ውስብስብ በሆኑ የኢንክሪፕሽን ዘዴዎች አማካኝነት ነው። የኮድ መፍቻ ቁልፍ ያላቸው ባለሙያዎች በሚስጥራዊ የአጻጻፍ ዘዴ የተላከውን መልእክት ወደ ቀድሞው ይዘቱ ይመልሱትና መረጃውን ያነቡታል።
ከብረት የተሠራ ቁልፍ ብዙውን ጊዜ አንድን ነገር ለመክፈት የሚያስችሉ ጥርሶችና ክርክሮች አሉት፤ ዲጂታል ቁልፍ ደግሞ እርስ በርስ ተሰበጣጥረው የሚገኙ ዜሮና አንድ ቁጥሮች ይኖሩታል። ረዘም ያሉ ቁልፎች ብዙ የዜሮና የአንድ ቁጥሮች ስብጥር ስለሚኖራቸው ሚስጥሩን ለመፍታት የሚደረገውን ጥረት ይበልጥ አስቸጋሪ ያደርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ስምንት ዲጂት ያለው ቁልፍ 256 የአንድና የዜሮ ስብጥሮች ያሉት ሲሆን 56 ዲጂት ያለው ቁልፍ ደግሞ ከ72 ኳድሪሊየን የሚበልጥ ስብጥር ይኖረዋል። በአሁኑ ጊዜ ሚስጥራዊ የሆኑ ድረ ገጾች ውስጥ ለመግባት አብዛኛውን ጊዜ የሚጠየቀው 128 ዲጂት ያለው ቁልፍ ነው፤ ይህ ሲባል 56 ዲጂት ካለው ቁልፍ 4.7 ሴክስቲሊየን ጊዜ የሚበልጥ ስብጥር ይኖረዋል ማለት ነው! *
እንዲህም ሆኖ ሚስጥራዊ መረጃዎች የሚሰረቁበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ በ2008 በዩናይትድ ስቴትስ፣ የፌዴራሉ አቃቤ ሕጎች እስከ ዛሬ ታይቶ የማይታወቅ በተባለለት የግለሰቦች ማንነት ስርቆት 11 ሰዎችን ከሷል። እነዚህ ሰዎች በላፕቶፕ ኮምፒውተሮች፣ በሽቦ አልባ ቴክኖሎጂና ልዩ በሆኑ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች በመጠቀም ሰዎች በገንዘብ መክፈያ ቦታዎች የተጠቀሙባቸውን የክሬዲትና ዴቢት ካርድ ቁጥሮች እንደወሰዱ ተገልጿል።
መረጃዎችህን በሚስጥር ለመያዝ የምትጠቀምበት ዘዴ ምን ያህል አስተማማኝ ነው?
የባንክ ሒሳብህንና በኢንተርኔት አማካኝነት የምታደርገውን የገንዘብ ልውውጥ ከዘረፋ ለመጠበቅ የሚያስችለው ሚስጥራዊ ኮድ በቀላሉ ሌሎች እጅ ውስጥ የሚገባ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ከአንተም ብዙ የሚጠበቅ ነገር አለ። መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰው አደጋ ሲያይ መጠጊያ ይሻል፤ ብስለት የጐደለው ግን በዚያው ይቀጥላል፤ መከራም ያገኘዋል” ይላል። (ምሳሌ 22:3) ስለዚህ አንተም አስተዋይ መሆንና ራስህን ከአታላዮችና ከሌቦች ለመጠበቅ ቢያንስ የሚከተሉትን ነገሮች ማድረግ ይገባሃል፦
▪ በኮምፒውተርህ ላይ ፀረ ቫይረስ ፕሮግራም ተጠቀም።
▪ የግል መረጃዎችህን አሳልፎ የሚሰጥ ስፓይዌር የተባለ ፕሮግራም መኖሩን የሚከታተል ፕሮግራም ይኑርህ።
▪ ሌሎች ሰዎች መረጃዎችህን ለመመልከት ወደ ኮምፒውተርህ መግባት እንዳይችሉ የሚያግድ ፋየርዎል የተባለው ፕሮግራም ይኑርህ።
▪ ከላይ የተዘረዘሩትን ፕሮግራሞች ስትጠቀም ማሻሻያ የተደረገባቸውን ፕሮግራሞች ተጠቀም፤ ወቅታዊ የሆኑትንም ፕሮግራሞች ተከታትለህ አስገባ።
▪ ከኢሜይል ወይም ከፈጣን መልእክቶች ጋር ተያይዘው የሚመጡልህ ፋይሎች ካሉ በተለይ ደግሞ መልእክቶቹ ከማታውቃቸው ግለሰቦች ከመጡ እንዲሁም የግል መረጃህን እንድትሰጥ ወይም ፓስወርድህ ትክክል መሆን አለመሆኑን እንድታረጋግጥ የሚጠይቁ ከሆነ ጥንቃቄ አድርግ።
▪ የክሬዲት ካርድ ቁጥሮችንና የመሳሰሉትን ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸውን መረጃዎች በምትሞላበት ጊዜ መረጃዎችህን ወደ ሚስጥራዊ ኮዶች የሚለውጡ ድረ ገጾችን ተጠቀም፤ እንደጨረስክም ድረ ገጹን ዘግተህ ውጣ። *
▪ ለመገመት የሚያስቸግሩ ፓስወርዶችን ተጠቀም፤ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች እንዳያውቁብህ ጥንቃቄ አድርግ።
▪ ከማይታወቅ ምንጭ የተገኘ ፕሮግራም አትገልብጥ ወይም አትጠቀም።
▪ ፋይሎችህን በየጊዜው በሌሎች መሣሪያዎች ላይ ገልብጠህ በጥንቃቄ አስቀምጣቸው።
ቅድመ ጥንቃቄ እንድታደርግ የሚረዱህን እነዚህ መሠረታዊ መመሪያዎች ከተከተልክና ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ጊዜ ያስፈልጋሉ የሚባሉ እርምጃዎችን ከወሰድክ የግል ሚስጥሮችህንና መረጃዎችህን ለመጠበቅ በሚደረገው ትግል በአሸናፊነት የመወጣት አጋጣሚህ ከፍተኛ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.13 ሳይፈር በመሠረቱ ከኮድ የተለየ ዘዴ ነው። የሳይፈርን ዘዴ የሚጠቀም ሰው እያንዳንዱን ፊደል በሌላ ፊደል ወይም ቁጥር የሚተካ ሲሆን ኮድ የሚጠቀም ሰው ግን ፊደሎችን፣ ሐረጎችን ወይም ቁጥሮችን በሌላ ፊደል፣ ሐረግ ወይም ቁጥር ይተካል። ይሁን እንጂ ሁለቱም ተመሳሳይ የሚሆኑባቸው ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላል።
^ አን.19 ኳድሪሊየን የሚባለው ከ1 በኋላ 15 ዜሮዎች ያሉት ቁጥር ነው። ሴክስቲሊየን ደግሞ ከ1 በኋላ 21 ዜሮዎች አሉት።
^ አን.28 ሚስጥራዊ የሆኑ ድረ ገጾች አስተማማኝ መሆናቸውን የሚያሳይ የቁልፍ ምልክት ወይም በአድራሻ መጻፊያ ቦታ ላይ “https://” የሚል ምልክት አላቸው። “s” የሚለው ፊደል የድረ ገጹ ሚስጥራዊነት አስተማማኝ መሆኑን የሚያሳይ ነው።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጥንት ስፓርታውያን ስኪታሊ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሃያኛው መቶ ዘመን የጀርመኖች ኢኒግማ ማሽን
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ ውስብስብ የሆኑ ሚስጥራዊ ኮዶች የግል መረጃዎችን ለመጠበቅ ይረዳሉ