በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የተሳካላቸው ቤተሰቦች—ክፍል ሁለት

የተሳካላቸው ቤተሰቦች—ክፍል ሁለት

የተሳካላቸው ቤተሰቦች—ክፍል ሁለት

“የተሳካላቸው ቤተሰቦች—ክፍል አንድ” ላይ እንደተገለጸው የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት አንድን ቤተሰብ በመከራ ወቅት እንደ ምሰሶ ደግፎ ሊያቆመው ይችላል። * ይሖዋ አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ለሚመሩ ሰዎች “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ” በማለት ቃል ገብቶላቸዋል።—መዝሙር 32:8

የኢኮኖሚን ችግር ተቋቁሞ መኖር። ብዙውን ጊዜ በጋብቻ ውስጥ ከባድ ውጥረት ከሚፈጥሩት ነገሮች አንዱ የገንዘብ ችግር ነው። ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች የቤተሰብ አባላት ያለባቸውን የገንዘብ ችግር በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ሊረዷቸው ይችላሉ። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “ስለ ነፍሳችሁ ምን እንበላለን፣ ምንስ እንጠጣለን ወይም ደግሞ ስለ ሰውነታችሁ ምን እንለብሳለን ብላችሁ መጨነቃችሁን ተዉ። . . . በሰማይ የሚኖረው አባታችሁ እነዚህ ሁሉ እንደሚያስፈልጓችሁ ያውቃል።”—ማቴዎስ 6:25, 32

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ኢስካርና ቤተሰቡ፣ ቤታቸው ካትሪና በተባለው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ ከወደመባቸው በኋላ የገጠማቸውን የገንዘብ ችግር እንዴት እንደተቋቋሙ የሚናገር ታሪክ በገጽ 23 ላይ ይገኛል።

አንድ የቤተሰብ አባል በከባድ በሽታ ሲያዝ። የማይታመም ሰው የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። በአብዛኛው ሕመሙ ጊዜያዊና ቶሎ የሚድን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ አንድ የቤተሰብ አባል ታሞ ለረጅም ጊዜ ቢተኛስ? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ታመው የተኙትን እንደሚደግፋቸው ይናገራል። (መዝሙር 41:1-3) የቤተሰብ አባላት ይሖዋ ለታማሚው ሰው እንክብካቤ የሚሰጥበት መሣሪያ ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉት እንዴት ነው?

በጃፓን የሚኖረው ሐጂሜ ባለቤቱ ኖሪኮ በጠና በታመመች ጊዜ እሱና ሴቶች ልጆቹ እሷን ለመንከባከብ ተባብረው የሠሩት እንዴት እንደሆነ የተናገረው ሐሳብ በገጽ 24 ላይ ይገኛል።

የልጅ ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም። የልጅ ሞት አንድ ቤተሰብ ከሚያጋጥሙት እጅግ አሳዛኝ መከራዎች አንዱ ነው። ይሖዋ የልጅ ሞት የሚያስከትለውን ከባድ ሐዘን እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል። (ራእይ 21:1-4) ይሖዋ አሁንም እንኳን ላዘኑት መጽናናትን ይሰጣል።—መዝሙር 147:3

በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት ፌርናንዶና ዲልማ፣ የሕፃን ልጃቸው ሞት ያስከተለባቸውን ሐዘን እንዲቋቋሙ መጽሐፍ ቅዱስ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ የተናገሩት ሐሳብ በገጽ 25 ላይ ይገኛል።

በሚቀጥሉት ገጾች ላይ ያሉት ታሪኮች በግልጽ እንደሚያሳዩት መጽሐፍ ቅዱስ መከራ የደረሰባቸውን ቤተሰቦች የሚረዳ አስተማማኝ መመሪያ ይዟል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 በዚህ መጽሔት ላይ ከገጽ 14-17ን ተመልከት።

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የኢኮኖሚን ችግር ተቋቁሞ መኖር

ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖረው ኢስካር ኒከልዝ እንደተናገረው

“ካትሪና የተባለው ዝናብ የቀላቀለ ኃይለኛ አውሎ ነፋስ የቤታችንን ጣሪያና ግድግዳ ሙሉ በሙሉ አወደመብን። የማስተምርበት ትምህርት ቤት ደግሞ ለአንድ ወር ተኩል በጎርፍ ተጥለቅልቆ ቆየ።”

በ2005 ነሐሴ ወር ውስጥ እኔና ባለቤቴ ሚሼል፣ ሲድኒ ከምትባለው የሁለት ዓመት ልጃችን ጋር በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሚሲሲፒ በሚገኘው ቤይ ሴንት ሉዊስ ከተማ እንኖር ነበር። እኔና ሚሼል የይሖዋ ምሥክሮች ስለሆንን በክርስቲያናዊው አገልግሎት የቻልነውን ያህል ሙሉ ተሳትፎ የማድረግ ግብ ነበረን። እኔ የሙያ አስተማሪ የነበርኩ ሲሆን የማስተምርበት ትምህርት ቤት የሚገኘው በአቅራቢያችን ባለችው ኒው ኦርሊየንስ፣ ሉዊዚያና ነበር። የምሠራው በሳምንት ውስጥ ሦስቱን ቀን ብቻ በመሆኑ ከሚቀረኝ ጊዜ ውስጥ አብዛኛውን ሌሎችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በማስተማር አሳልፍ ነበር። ይህ ፕሮግራም በጣም ተስማምቶን ነበር። ከዚያ በኋላ ካትሪና የተባለው ዝናብ የቀላቀለ አውሎ ነፋስ ከተማችንን ሊመታ መሆኑን የሚገልጽ ዜና ሰማን። እኛም በአፋጣኝ አካባቢውን ለቀን ለመውጣት ዝግጅት አደረግን።

አውሎ ነፋሱ ካለፈ በኋላ ስንመለስ በቤይ ሴንት ሉዊስ የሚገኘው ቤታችንም ሆነ በኒው ኦርሊየንስ የሚገኘው የማስተምርበት ትምህርት ቤት ወድመው አገኘናቸው። ከኢንሹራንስና ከመንግሥት ያገኘነው ገንዘብ ቤት ለማግኘት ያስቻለን ቢሆንም ቋሚ የገቢ ምንጭ ማግኘት ግን አዳጋች ሆነብኝ። በተጨማሪም ባለቤቴ በተበከለ ውኃ ምክንያት ታመመች። ከዚያም የሰውነቷ በሽታን የመከላከል አቅም ተዳክሞ ስለነበር በትንኝ በሚተላለፈው በዌስት ናይል ቫይረስ ተጠቃች። በዚህ ጊዜ የኢንሹራንስ ዋጋና የኑሮ ውድነት ጨምሮ ነበር።

ከአዲሱ ሁኔታ ጋር ለመላመድ ለሕይወት አስፈላጊ በሆኑ ነገሮችም ሳይቀር በገንዘብ አወጣጥ ረገድ ይበልጥ ቆጣቢ መሆን ጀመርን። እኔም ያገኘሁትን ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆን ነበረብኝ።

ንብረታችንን ሁሉ ማጣታችን ለእኛ ቀላል እንዳልነበረ አልክድም። ይሁን እንጂ በሕይወት በመኖራችን አመስጋኞች ነበርን። ደግሞም የደረሰው አደጋ ቁሳዊ ነገሮች ያላቸው ዋጋ ውስን መሆኑን አስገንዝቦናል። እንዲያውም “አንድ ሰው ሀብታም ቢሆንም እንኳ ሕይወቱ በንብረቱ ላይ የተመካ” እንዳልሆነ ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ እንድናስታውስ አድርጎናል።—ሉቃስ 12:15

እርግጥ ነው፣ ስለደረሰብን ኪሳራ በጣም አዝነናል፤ ሆኖም ከእኛ የበለጠ ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ሰዎች ነበሩ። እንዲያውም አንዳንዶች ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከአደጋው በኋላ ጉዳት የደረሰባቸውን መልሶ ለማቋቋምና ያዘኑትን ለማጽናናት በሚደረገው ጥረት ወዲያውኑ መካፈል የጀመርኩት ለዚህ ነው።

በዚህ የመከራ ወቅት በተለይ በመዝሙር 102:17 (NW) ላይ የሚገኘው ሐሳብ አጽናንቶናል። ጥቅሱ ይሖዋ አምላክ “የችግረኞችን [ወይም ባዶ እጃቸውን የቀሩ ሰዎችን] ጸሎት በእርግጥ ይሰማል፣ ጸሎታቸውንም አይንቅም” ይላል። እኛም በቤተሰብ ደረጃ የእሱ ድጋፍ እንዳልተለየን ይሰማናል!

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ካትሪናና ሪታ የተባሉት ኃይለኛ ዝናብ የቀላቀሉ አውሎ ነፋሶች በ2005 የዩናይትድ ስቴትስን ባሕረ ሰላጤ ከመቱ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች በአፋጣኝ 13 የእርዳታ ማከፋፈያ ጣቢያዎችን፣ ዘጠኝ መጋዘኖችንና አራት የነዳጅ ማከማቻዎችን አቋቋሙ። እርዳታ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን እገዛ ለማድረግ ከዩናይትድ ስቴትስና ከሌሎች 13 አገሮች ወደ 17,000 የሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች ጎረፉ። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች በሺህ የሚቆጠሩ ቤቶችን አድሰዋል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

አንድ የቤተሰብ አባል በከባድ በሽታ ሲያዝ

ጃፓን የሚኖረው ሐጂሜ ኢቶ እንደተናገረው

“ኖሪኮ እስከታመመችበት ጊዜ ድረስ ምግብ ማብሰል የሚያስደስተን ነገር ነበር። አሁን ግን በአፏ መብላትም ሆነ መጠጣት ወይም መናገር አትችልም። ያለ ተሽከርካሪ ወንበር መንቀሳቀስ የማትችል ከመሆኑም ሌላ የምትተነፍሰው በሰው ሠራሽ የመተንፈሻ መሣሪያ አማካኝነት ነው።”

በግንቦት 2006 አካባቢ ባለቤቴ ኖሪኮ መናገር ትቸገር ጀመር። በቀጣዮቹ ወራት መብላትና መጠጣትም አስቸጋሪ እየሆነባት መጣ። መስከረም ላይ የአንጎልንና የአከርካሪን የነርቭ ሴሎች የሚያጠቃ አሚዮትሮፊክ ላተራል ስክለሮሲስ (ALS) የሚባል እያደር እየተባባሰ የሚሄድ በሽታ እንደያዛት በምርመራ ተረጋገጠ። በአራት ወራት ውስጥ ሕይወታችን ሙሉ በሙሉ ተለወጠ። የኖሪኮ ችግር ግን ገና መጀመሩ ነበር።

ውሎ አድሮ ምላሷ መሥራት አቆመ፤ ቀኝ እጇም ሽባ ሆነ። ለመመገብ የሚያስችላት የፕላስቲክ ቱቦ በቀዶ ሕክምና አማካኝነት ጨጓራዋ ውስጥ ገባላት፤ መተንፈስ እንድትችል ደግሞ በአንገቷ በኩል መተንፈሻ ቱቦ ተደረገላት። ይህ ደግሞ መናገር እንዳትችል አድርጓታል። ኖሪኮ ሁልጊዜ ንቁና ቀልጣፋ ስለነበረች ይህ በሽታ ምን ያህል ከባድ እንደሚሆንባት መገመት ይከብደኛል። የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን ኖሪኮና ሁለቱም ሴት ልጆቼ ሙሉ ጊዜያቸውን ለክርስቲያናዊው አገልግሎት ያውሉ ነበር። አሁን ኖሪኮ መተንፈስ የምትችለው በሰው ሠራሽ የመተንፈሻ መሣሪያ ሲሆን የአልጋ ቁራኛም ሆናለች።

ይህም ቢሆን የምትፈልጋቸውን ነገሮች ከማድረግ ኖሪኮን አላገዳትም! ለምሳሌ ያህል፣ በተሽከርካሪ ወንበር ላይ ሆና የመተንፈሻ መሣሪያው እንደተያያዘላት በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ትገኛለች። የመስማት ችሎታዋ በጣም ስለደከመ ከስብሰባው መጠቀም እንድትችል አንዷ ልጄ የሚነገረውን ነገር በማስታወሻ ደብተር ላይ በትልልቁ ትጽፍላታለች። ምንም እንኳ ኖሪኮ የሙሉ ጊዜ አገልግሎቷን ለማቋረጥ ብትገደድም የመጽሐፍ ቅዱስን ተስፋ ያዘለ መልእክት ለሰዎች ለማስተማር በኮምፒውተራችን ላይ በተገጠመ ልዩ መሣሪያ አማካኝነት ደብዳቤ እየጻፈች አሁንም ትመሠክራለች።—2 ጴጥሮስ 3:13፤ ራእይ 21:1-4

ኖሪኮን ለመርዳት በቤተሰብ ደረጃ ተባብረን እንሠራለን። ሁለቱም ሴቶች ልጆቼ በቤት ውስጥ እናታቸውን ይበልጥ መርዳት እንዲችሉ ሥራ ቀይረዋል። ሦስታችንም ኖሪኮ ታከናውናቸው የነበሩትን በርካታ ዕለታዊ ተግባሮች እንሠራለን።

አንዳንድ ጊዜ ጠዋት ላይ ኖሪኮን ሳያት የደከማት ትመስላለች። በውስጤ ‘ዛሬ ደክሞሻል፤ ብታርፊ ጥሩ ነው’ ልላት አስባለሁ። ይሁን እንጂ ኖሪኮ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች ማካፈል ትፈልጋለች። ኮምፒውተሩን ማዘጋጀት ስጀምር የኖሪኮ ዓይኖች በደስታ ይበራሉ! ደብዳቤ ስትጽፍ ይበልጥ እየተነቃቃች ትሄዳለች። የኖሪኮ ሁኔታ ‘ሁልጊዜ የጌታ ሥራ የበዛልን መሆናችን’ ያለውን ጥቅም እንድገነዘብ አስችሎኛል።—1 ቆሮንቶስ 15:58

በጥር 2006 የንቁ! መጽሔት እትም ላይ የወጣውና ተመሳሳይ ሕመም ስለነበረበት ስለ ጄሰን ስቱዋርት የሚናገረው ተሞክሮ ኖሪኮ በትካዜ እንዳትዋጥ በእጅጉ ረድቷታል። እንዲያውም የሆስፒታል ሠራተኞች እንዲህ ዓይነት አዎንታዊ አመለካከት ሊኖራት የቻለው ለምን እንደሆነ በመገረም ሲጠይቁ ኖሪኮ ስለ ጄሰን ስቱዋርት የወጣውን ርዕስ አሳየቻቸው፤ እኛም መጽሔቱን ለበርካታ ሠራተኞች ሰጠናቸው። ባለቤቴ ለሌሎች ስለ እምነቷ መናገሯ ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ሆኖላታል።

ኖሪኮን ካገባሁ 30 ዓመት ሆኖኛል። ይሁን እንጂ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ የተከሰቱት ሁኔታዎች ቀደም ሲል ብዙም ያላደነቅኩላትን ነገሮች እንዳደንቅ አድርገውኛል። እሷን በማግባቴ በጣም ደስተኛ ነኝ!

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

የልጅ ሞት የሚያስከትለውን ሐዘን መቋቋም

ዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩት ፌርናንዶ እና ዲልማ ፍሬተስ እንደተናገሩት

“የልጅ ሞት የሚያስከትለውን የስሜት ቀውስ በቃላት መግለጽ ያዳግታል። ከዚህ የሚበልጥ አሳዛኝ ነገር ሊኖር አይችልም።”

ፕሬሸስ ብለን ስም ያወጣንላት ሴት ልጃችን የሞተችው ሚያዝያ 16, 2006 ሲሆን ገና የአሥር ቀን ሕፃን ነበረች። ልጃችን የሦስት ወር ገደማ ፅንስ ሳለች ከባድ የልብ ችግር እንዳለባት ታውቆ ነበር። የምትወለድበት ጊዜ ሲቃረብ ከማህፀን በሕይወት መውጣት ብትችል እንኳ ብዙም ሳትቆይ እንደምትሞት ግልጽ ሆነ። ይህን መቀበል በጣም ከብዶን ነበር። ከእሷ በፊት ሦስት ጤነኛ ልጆች ወልደናል። አሁን የምትወለደው ልጃችን ትሞታለች ብለን ማመን ከበደን።

ፕሬሸስ ከተወለደች በኋላ ክሮሞዞም ስለሚባሉት የሴል ክፍሎች መዛባት ያጠኑ ጥሩ ልምድ ያላቸው አንድ ስፔሻሊስት ከ5,000 ሕፃናት ውስጥ አንዱን ብቻ የሚያጠቃ ትሪሶሚ 18 ተብሎ የሚጠራ የጤና ችግር እንዳለባት በምርመራ አረጋገጡ። በሕይወት ብዙ እንደማትቆይ ግልጽ ነበር። ምንም ማድረግ እንደማንችል ስናውቅ በጣም አዘንን። ልናደርግ የምንችለው አንድ ነገር ቢኖር በዚያች አጭር ዕድሜዋ አብረናት መሆን ነበር። ያደረግነውም ይህንኑ ነበር።

ከፕሬሸስ ጋር ያሳለፍናቸው አሥር ቀናት እጅግ አስደሳች ነበሩ። በእነዚያ ቀናት እኛና ሦስቱ ሴቶች ልጆቻችን ከፕሬሸስ ጋር በጣም ተቀራረብን። እናቅፋት፣ እናወራላት፣ እንስማት፣ እንዲሁም የቻልነውን ያህል ብዙ ፎቶግራፍ እናነሳት ነበር። ይበልጥ ማንን እንደምትመስል ጭምር እንጠያየቅ ነበር። የፕሬሸስን የጤና ችግር ያገኙላት ስፔሻሊስት በየቀኑ ሆስፒታል እየመጡ ይጠይቁን ነበር። አንድ ቀን አብረውን ካለቀሱ በኋላ በጣም እንዳዘኑ ነገሩን። እንዲሁም ከእኛ ጋር እየተነጋገሩ ለማስታወሻ እንዲሆናቸው ፕሬሸስን ሳሏት። ለእኛም አንድ ቅጂ ሰጡን። 

የይሖዋ ምሥክሮች በመሆናችን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው አምላክ ምድራችንን እንደገና ገነት እንደሚያደርጋትና እንደ ፕሬሸስ ያሉ ሕፃናትን ጨምሮ የሞቱ ሰዎችን በምድር ላይ እንዲኖሩ ለማስነሳት እንደሚናፍቅ ሙሉ እምነት አለን። (ኢዮብ 14:14, 15፤ ዮሐንስ 5:28, 29) ፕሬሸስን እንደገና የምናቅፍበትን ቀን በናፍቆት እንጠባበቃለን። “ገነት” የሚለውን ቃል በሰማን ቁጥር ይህን ተስፋ ስለምናስብ ልባችን በደስታ ይሞላል! እስከዚያው ድረስ ግን አምላክ ፕሬሸስን እንደሚያስታውሳት እንዲሁም አሁን እየተሠቃየች እንዳልሆነ ማወቃችን ያጽናናናል።—መክብብ 9:5, 10