ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ ጀርመን ውስጥ በሚኖሩ 2,000 ሰዎች ላይ በተደረገ ጥናት መሠረት ከ14 እስከ 19 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል 40 በመቶ የሚያህሉት ከተቃራኒ ፆታ ጋር የጀመሩትን ጓደኝነት ማቋረጣቸውን ለመግለጽ በሞባይል የጽሑፍ መልእክት ወይም ኢ-ሜይል መላክ ምንም ችግር የለውም የሚል አመለካከት አላቸው። ዕድሜያቸው 50ና ከዚያ በላይ ከሆኑ ሰዎች ውስጥ ከ80 በመቶ የሚበልጡት ግን እንዲህ ያለው ድርጊት ፈጽሞ ትክክል እንዳልሆነ ይሰማቸዋል።—ፍራንክፉርተር ኖይ ፕሬስ፣ ጀርመን
▪ በ2008 በዓለም ዙሪያ 2.3 ትሪሊዮን የጽሑፍ መልእክቶች በሞባይል እንደተላኩ ተገምቷል። —ሂቱ ኒውስ፣ ታሂቲ
▪ “ሲጋራ ማጨስ የአንድን ሰው ዕድሜ ምን ያህል ሊያሳጥረው ይችላል? በአማካይ ከአምስት እስከ አሥር ዓመት ሊያሳጥረው ይችላል።”—ዩኒቨርሲቲ ኦቭ ካሊፎርኒያ በርክሌይ ዌልነስ ሌተር፣ ዩናይትድ ስቴትስ
▪ በዩናይትድ ስቴትስ ቢሮዎች ውስጥ ከሚሠራባቸው ኮምፒውተሮች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ሌሊቱን ሳይዘጉ እንደሚያድሩ ተገምቷል። በዚህ ምክንያት በየዓመቱ 14.4 ሚሊዮን ቶን የሚሆን ካርቦን ዳይኦክሳይድ ሳያስፈልግ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ተለቆ ወደ ከባቢ አየር ይገባል።—ዎርልድ ዎች፣ ዩናይትድ ስቴትስ
አውቶቡሶች አምላክ የለሽነትን ያስፋፋሉ
“ምናልባት አምላክ ላይኖር ይችላል። መጨነቁን ትታችሁ ሕይወትን አጣጥሙ።” ዘ ጋርዲያን የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው ይህ መፈክር ለንደን፣ እንግሊዝ ውስጥ በሚገኙ 200 አውቶቡሶችና በመላ አገሪቱ ባሉ ሌሎች 600 አውቶቡሶች እንዲሁም ለንደን ኦክስፎርድ ጎዳና ላይ በተተከሉ ሁለት ትልልቅ ስክሪኖች አማካኝነት ለሕዝብ እንዲታይ ተደርጓል። መፈክሩን ያዘጋጁ ሰዎች፣ ይህን ዘመቻ ለማድረግ የተነሳሱት በገሃነመ እሳት የማያምኑ ሰዎችን የሚያወግዘውን ሃይማኖታዊ ማስታወቂያ ለመቃወም እንደሆነ ገልጸዋል። “ምናልባት” የሚለውን ቃል የተጠቀሙት በብሪታንያ የማስታወቂያ ደረጃ መዳቢ ባለሥልጣን ተጠያቂ እንዳይሆኑ ብለው ነው፤ ምክንያቱም አምላክ እንደሌለ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም። የዘመቻው አንዱ ዓላማ አምላክ የለሽ የሆኑ ሌሎች ሰዎች “አደባባይ ወጥተው” ሐሳባቸውን እንዲገልጡ ማበረታታት ነው።
ሕፃናት ያለጊዜያቸው መወለዳቸው የሚያስከትለው አደጋ
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በተለያዩ ዘዴዎች ለምሳሌ ያህል፣ ምጥ አስቀድሞ እንዲመጣ በማድረግና በቀዶ ሕክምና አማካኝነት ያለጊዜያቸው እንዲወለዱ የሚደረጉ ሕፃናት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው። ይሁን እንጂ ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል እንደዘገበው “የመጨረሻዎቹ የእርግዝና ሳምንታት ከዚህ በፊት ከሚታሰበው በላይ በጣም አስፈላጊ ናቸው።” አዲስ በተወለዱ 15,000 የሚያህሉ ሕፃናት ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው አንድ ሕፃን ከ32 እስከ 39 ባሉት ሳምንታት ውስጥ በእናቱ ማህፀን ውስጥ አንድ ሳምንት በቆየ መጠን በሰውነት መንዘፍዘፍ፣ በጆንዲስ፣ በመተንፈሻ አካላት መቆጣትና በአንጎል ውስጥ ደም የመፍሰስ ችግር የመያዝ አጋጣሚው 23 በመቶ ይቀንሳል። በተጨማሪም ከ32 እስከ 36 ባሉት ሳምንታት ውስጥ የተወለዱ ሕፃናት ሊያጋጥማቸው የሚችለው የባሕርይና ነገሮችን የመረዳት ችግር ከሌሎቹ ከፍ ያለ ነው። በመሆኑም ጋዜጣው እንደዘገበው በአሜሪካ የሚገኘው የማዋለድና የማህፀን ሕክምና ኮሌጅ፣ ሕፃናት “ከጤና ጋር የተያያዘ ችግር ካልተከሰተ በስተቀር ከ39 ሳምንታት በፊት” መወለድ እንደሌለባቸው ይመክራል።
ደረጃ መውጣት ጤንነትን ያሻሽላል
ዘ ላንሴት የተሰኘው የብሪታንያ የሕክምና መጽሔት “አዘውትሮ ደረጃ መውጣት ጤንነትን ለማሻሻል የሚረዳ ቀላልና ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ዘዴ ነው” በማለት ገልጿል። ተመራማሪዎች 69 የቢሮ ሠራተኞችን በመሥሪያ ቤታቸው ያለውን ሊፍት ከመጠቀም ይልቅ ሁልጊዜ ደረጃውን እንዲወጡ ጠይቀዋቸው ነበር። ከ12 ሳምንታት በኋላ እነዚህ ሠራተኞች ሰውነታቸው በኦክሲጅን የመጠቀም አቅሙ 8.6 በመቶ ጨመረ፤ ይህ ደግሞ “በማንኛውም ምክንያት የመሞት አጋጣሚያቸውን 15 በመቶ ቀንሶላቸዋል።” በተጨማሪም ሠራተኞቹ “በደም ግፊታቸው፣ በኮሌስትሮል መጠናቸው፣ በክብደታቸው፣ በሰውነታቸው የስብ ክምችትና በቦርጫቸው መጠን” ላይ ጉልህ መሻሻል ተመልክተዋል።