በእርሳስ እንዳትመረዙ ተጠንቀቁ!
በእርሳስ እንዳትመረዙ ተጠንቀቁ!
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግሥታት እንደ አሻንጉሊቶችና ጌጣጌጦች ያሉ ምርቶች ወደ አምራቾቹ እንዲመለሱ የሚያዝዝ መመሪያ እያወጡ ነው። ለምን? ከእነዚህ ምርቶች መካከል በአንዳንዶቹ ውስጥ የተገኘው የእርሳስ * መጠን አደገኛ በመሆኑ ነው፤ ትንንሽ ልጆች ደግሞ ብዙውን ጊዜ እነዚህን ዕቃዎች ወደ አፋቸው አስገብተው የመምጠጥ ወይም የማኘክ ልማድ አላቸው። በተለይ ዕድሜያቸው ከስድስት ዓመት በታች የሆነ ልጆች ማዕከላዊ የነርቭ ሥርዓታቸው ገና በማደግ ላይ ስለሆነ በእርሳስ መመረዝ የበለጠ አደገኛ ሊሆንባቸው ይችላል።
የጆንስ ሆፕኪንስ ብሉምበርግ የሕዝብ ጤና ትምህርት ቤት ባካሄደው ጥናት መሠረት እርሳስ፣ ለአእምሮ እድገትና ለማሰብ ችሎታ መዳበር አስፈላጊ የሆነው ፕሮቲን ሥራውን በአግባቡ እንዳያከናውን እንቅፋት ይፈጥራል። ልጆች ወደ ሰውነታቸው ከገባው እርሳስ ውስጥ እስከ 50 በመቶ የሚሆነው ሰውነታቸው ውስጥ የሚቀር ሲሆን ትልልቅ ሰዎች ግን ወደ ሰውነታቸው ከገባው እርሳስ ውስጥ በሰውነታቸው ውስጥ የሚቀረው ከ10 እስከ 15 በመቶ የሚሆነው ብቻ እንደሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ።
በቅርቡ የተደረገ ጥናት እንደጠቆመው አንዳንድ መንግሥታት መርዛማ እንደሆነ ከሚገልጹት ደረጃ ያነሰ መጠን ያለው እርሳስም እንኳ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ናሽናል ሴፍቲ ካውንስል የተባለው ድርጅት እንደገለጸው ከሆነ በእርሳስ መመረዝ በልጆች ላይ ከሚያስከትላቸው ችግሮች መካከል “ትምህርት የመቀበልና ትኩረት የመሰብሰብ ችግር፣ የባሕርይ ችግር፣ የእድገት መቀጨጭ፣ የመስማት ችሎታ መዳከምና የኩላሊት ሕመም” ይገኙበታል። ሊያረግዙ በሚችሉበት ዕድሜ ላይ ያሉ ሴቶች በእርሳስ እንዳይመረዙ ልዩ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርባቸዋል፤ ምክንያቱም እርሳስ ፅንሱን ሊጎዳው ይችላል። *
በአንዳንድ የእስያና የላቲን አሜሪካ አገራት በብዛት ጥቅም ላይ በሚውሉት እርሳስ የተቀቡ ሸክላዎች የሚዘጋጅ ምግብና መጠጥም ሊመረዝ ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የሚጠጣ ውኃ እንዲቀዘቅዝ በሸክላ ዕቃ ውስጥ የሚቀመጥ ሲሆን ትኩስ ነገሮች ደግሞ እርሳስ በተቀቡ ኩባያዎች ይቀርባሉ። በሜክሲኮ ሲቲ ከአምስት ዓመት በታች ባሉ ልጆች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው ዕድሜያቸው ከዓመት ከስድስት ወር በላይ ከሆኑት ሕፃናት መካከል ግማሽ የሚያህሉት በደማቸው ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው እርሳስ ተገኝቷል። ለዚህም በምክንያትነት የተጠቀሰው እርሳስ በተቀቡ የሸክላ ዕቃዎች የተዘጋጀ ምግብ መመገባቸው ነው። እርሳስ ከሸክላ የተሠሩ ዕቃዎች ልስላሴ እንዲኖራቸውና እንደ መስታወት እንዲያብረቀርቁ የሚያደርግ ቢሆንም በተለይ እነዚህ ዕቃዎች ሲግሉ ወይም አንዳንድ የፍራፍሬ ዓይነቶችና አትክልቶች ሲቀመጡባቸው እርሳሱ ይለቃል።
በእርሳስ ለመመረዝ የሚያጋልጡ ሌሎች ነገሮች
አብዛኞቹ የበለጸጉ አገሮች ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የእርሳስ ማዕድን ያለበት ነዳጅ መጠቀማቸውን
ቀስ በቀስ ቢያቆሙም አሁንም በዓለም ዙሪያ ወደ 100 የሚጠጉ አገሮች እርሳስ የተደባለቀበት ነዳጅ እንደሚጠቀሙ የዓለም ጤና ድርጅት ይናገራል። እርሳስ የማይበሰብስ ወይም የማይቃጠል ነገር ነው። በመሆኑም ከተሽከርካሪዎች ጭስ የወጡ ጥቃቅን የእርሳስ ብናኞች በአውራ ጎዳናዎች አካባቢ ያለውን አፈር ይበክሉታል። ከዚያም እነዚህ ብናኞች ሰዎች ሲተነፍሱ ወደ ሳንባቸው ውስጥ ሊገቡ ወይም ጫማቸው ላይ ተለጥፎ ወደ ቤት ሊገቡ ይችላል።በእርሳስ ለመመረዝ ከሚያጋልጡት ዋነኛ መንስኤዎች ሌላው ደግሞ ቤቶች እርሳስ የተቀላቀለበት ቀለም እንዳይቀቡ የሚከለክል ሕግ ከመውጣቱ በፊት ጥቅም ላይ ይውል የነበረው ቀለም ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ በግምት 38 ሚሊዮን ቤቶች ማለትም ከጠቅላላው የቤቶች ቁጥር 40 በመቶ የሚሆኑት ከእርሳስ ጋር የተቀላቀለ ቀለም የተቀቡ ናቸው። በተለይ ቀለሙ ሲላላጥ ወይም ቤቶቹ ሲታደሱ የሚኖረው የእርሳስ ብናኝ አደጋ ሊያስከትል ይችላል።
ብዙ ያረጁ ከተሞችና ቤቶች ውኃ የሚመጣላቸው በእርሳስ ማዕድን በተሠሩ ቧንቧዎች ወይም በእርሳስ በተበየዱ የመዳብ ቧንቧዎች ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ ማዮ ክሊኒክ የሚባል አንድ የታወቀ የሕክምና ማዕከል ከእነዚህ ቧንቧዎች የሚወርደውን ቀዝቃዛ ውኃ ቀድቶ ከመጠጣት በፊት ከ30 እስከ 60 ሴኮንድ ለሚያህል ጊዜ እንዲፈስ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይመክራል። ከእነዚህ ቧንቧዎች የተቀዳ ትኩስ ውኃ ለመጠጥና ለምግብ ማብሰያ በተለይ ደግሞ ለሕፃናት ወተት መበጥበጫ ፈጽሞ መዋል የለበትም።
ለእርሳስ የሚያጋልጠው መንስኤ ሲወገድ በደም ውስጥ ያለው የእርሳስ መጠንም በእጅጉ ይቀንሳል። በደማቸው ውስጥ ያለው የእርሳስ መጠን የሚያሳስባቸው ሰዎች ደማቸውን ማስመርመር ይፈልጉ ይሆናል። ጉዳት የሚያስከትል መጠን ያለው እርሳስ በደማቸው ውስጥ መኖሩ ከታወቀ የሕክምና እርዳታ ማግኘት ያስፈልጋቸዋል።
የሕዝቡን ንቃተ ሕሊና የማሳደግ አስፈላጊነት
ረዘም ላለ ጊዜ በሰውነት ውስጥ እርሳስ መከማቸቱ በእርሳስ መመረዝን ሊያስከትል ይችላል። ይሁን እንጂ ከፍተኛ መጠን ያለው እርሳስ አንድ ጊዜም እንኳ ወደ ሰውነት መግባቱ ሊገድል ይችላል። የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል እንደገለጸው በ2006 ዕድሜው ለትምህርት ያልደረሰ አንድ ልጅ ከፍተኛ መጠን ያለው እርሳስ ያለበት ከብረት የተሠራ ጌጥ መዋጡ ባስከተለበት መዘዝ የተነሳ ሕይወቱ አልፏል።
አንድ የሕክምና ኢንሳይክሎፒዲያ እንደገለጸው በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ካሉት ዕድሜያቸው ለትምህርት ያልደረሰ 20 ሕፃናት መካከል አንዱ በደሙ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው እርሳስ ይገኛል፤ ይህም የሕዝቡን ንቃተ ሕሊና ማሳደግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያጎላል። በእርሳስ አጠቃቀም ረገድ ቁጥጥር በሚደረግበት አገር ሁኔታው እንዲህ ከሆነ እንዲህ ዓይነት ቁጥጥር በሌለባቸው አገሮች ሁኔታው ምን ይመስል ይሆን? በእርግጥም ሁሉም ሰው መጠንቀቅ አለበት!
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.2 በዚህ ርዕስ ውስጥ ‘እርሳስ’ የሚለው ቃል የተሠራበት ለመጻፊያነት የሚያገለግለውን መሣሪያ ሳይሆን በእንግሊዝኛ ሌድ የሚባለውን የማዕድን ዓይነት ለማመልከት ነው።
^ አን.4 ትልልቅ ሰዎችም ቢሆኑ በእርሳስ ሊመረዙ የሚችሉ ሲሆን ይህም የነርቭ መቃወስ፣ የጡንቻና መገጣጠሚያ ሕመም ወይም ከማስታወስ ችሎታና ሐሳብን ከመሰብሰብ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ሊያስከትልባቸው ይችላል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ልጆች በእርሳስ እንደተመረዙ የሚጠቁሙ አንዳንድ ምልክቶች
የሆድ ሕመም፣ ቁጡ መሆን፣ የደም ማነስ፣ ትኩረትን የመሰብሰብ ችግር፣ የሆድ ድርቀት፣ ድካም፣ ራስ ምታት፣ መነጫነጭ፣ ከእድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችሎታዎችን ማጣት፣ የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ ኃይል ማጣትና አዝጋሚ እድገት።—ሜድላይን ፕላስ ሜዲካል ኢንሳይክሎፒዲያ