አስገራሚ የሆነው ተፈጥሮ!
አስገራሚ የሆነው ተፈጥሮ!
ሳይንሳዊ ምርምር፣ የሰው ልጅ ስለ ጽንፈ ዓለም ወይም ስለ ጠፈር አካላት አሠራር ሰፋ ያለ እውቀት እንዲኖረው አድርጓል። በአሁኑ ጊዜ እጅግ ጥቃቅን የሆኑትን የቁስ አካል መሠረታዊ ክፍሎችም ሆነ ግዙፍ የሆነውን ጽንፈ ዓለም በተሻለ ሁኔታ መረዳት ተችሏል። ይሁን እንጂ ሰዎች ገና ያላወቋቸው በርካታ ውስብስብ ነገሮች አሉ።
የምንኖርባት ምድር ሰፊ በሆነው ጽንፈ ዓለም ውስጥ የያዘችው ቦታ በጣም ኢምንት ነው። ያም ሆኖ በዚህች ፕላኔታችን ላይ የምናየው እጅግ ውስብስብና አስገራሚ ውበት ያለው ተፈጥሮ በጣም ያስደምመናል፤ ከእነዚህም መካከል የአበቦች ውበት፣ ቀልብ የሚሰርቅ መልክዓ ምድር፣ አስደናቂ የሆነው የአእዋፍ ላባ፣ በሕብረ ቀለማት ያሸበረቀው የቢራቢሮ ክንፍ፣ አመሻሹ ላይ ከአድማሱ በስተጀርባ ስታሽቆለቁል ፍም መስላ የምትታየው ጀምበር እንዲሁም የምንወደው ሰው ሣቅ ይገኙበታል።
ብዙ ሰዎች ግዑዙን ጽንፈ ዓለም ሲመለከቱ እነዚህን ነገሮች ወደ ሕልውና ያመጣ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል መኖሩን የሚያሳምኗቸው በቂ ማስረጃዎች እንዳሉ ይሰማቸዋል። የፊዚክስ ሕግጋት በምድር ላይ ሕይወት መኖር እንዲችል ለማድረግ ሲባል በጥንቃቄ ተስተካክለው የተቀመጡ እንደሚመስሉ ይናገራሉ። ጽንፈ ዓለም የተዋቀረው አሁን ካለበት በትንሹ እንኳ ለየት ባለ መልኩ ቢሆን ኖሮ ሕይወት ያለው ነገር በፍጹም ሊኖር አይችልም ነበር። ይሁን እንጂ ለቁጥር የሚያታክት ብዛት ያላቸው ሕያዋን ፍጥረታት በፕላኔታችን ላይ ይኖራሉ።
ፖል ዴቪስ የተባሉ የጠፈር ተመራማሪ እንደሚከተለው ሲሉ ጽፈዋል፦ “የጠፈር አካላት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በሚገባ የተቀናጀ ንድፍን የሚከተል ይመስላል። . . . ተፈጥሮ፣ በአጋጣሚ የተከናወኑ ክስተቶች ያስገኙት ነገር ሳይሆን በረቀቀ መንገድ የተቀነባበሩ የሂሣብ ሕግጋት ውጤት ነው።” በፖል ዴቪስ አባባል የሚስማሙ አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት አሉ። ሌሎች ደግሞ በዚህ አይስማሙም።
ለምሳሌ፣ የኖቤል ተሸላሚና የፊዚክስ ሊቅ የሆኑት ስቲቨን ዋይንበርግ “ጽንፈ ዓለሙን ይበልጥ እየተረዳን በሄድን መጠን ምንም ዓይነት ዓላማ የሌለው ይሆንብናል” ብለዋል። የሚገርመው ግን ዋይንበርግ ራሳቸው “አንዳንድ ጊዜ ተፈጥሮ ከሚያስፈልገው በላይ ውብ የሆነ ይመስላል። . . . ይህ ሁሉ ውበት ለእኛ ተብሎ የተዘጋጀ ነው ብሎ ማሰብ ይከብዳል” ብለዋል።
ታዲያ ሐቁ የትኛው ነው? የተፈጥሮ ሕግጋት በጥንቃቄ ተስተካክለው የተቀመጡ ከሆኑ ይህንን ያደረገ ዓላማ ያለው ንድፍ አውጪ ወይም ፈጣሪ መኖር አይገባውም? የእኛ ሕይወትም ሆነ ጽንፈ ዓለም ዓላማ ይኖረው ይሆን? ወይስ እዚህ የተገኘነው ምንም ዓይነት ዓላማም ሆነ መሪ በሌለው አንድ ክስተት የተነሳ ነው? የሚቀጥሉት ርዕሶች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ።