ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
▪ በቅርብ የተደረገ አንድ ጥናት “ከ10 ብሪታንያውያን መካከል ስድስቱ፣ ሃይማኖት ሰዎች እንዲከፋፈሉ ምክንያት ሆኗል ብለው እንደሚያስቡ አመልክቷል።”—ዘ ካቶሊክ ሄራልድ፣ ብሪታንያ
▪ በዓለም ትልቁ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ የተተከለው በፖርቹጋል ነው። የፀሐይ ኃይል ማመንጫዎቹ የተተከሉት 250 ሄክታር በሚሸፍን ቦታ ላይ ሲሆን ለ30,000 ቤቶች የሚበቃ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ይችላሉ።—ኤል ፓይስ፣ ስፔን
▪ በመላው ዓለም በየዓመቱ 900,000 የሚሆኑ ወጣቶች ያለ ዕድሜያቸው ይቀጫሉ፤ ይህም ሲባል በየቀኑ ከ2,000 በላይ የሚሆኑ ወጣቶች ይሞታሉ ማለት ነው። ለዚህ ዋነኞቹ መንስኤዎች የትራፊክ አደጋ፣ ውኃ ውስጥ መስጠምና የእሳት አደጋ ናቸው።—ዲ ቬልት፣ ጀርመን
▪ “ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የደን ጭፍጨፋ በአማካይ ሲታይ የቀነሰ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜም በዓለም ላይ በየቀኑ 200 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ደን ይጨፈጨፋል።”—የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት፣ ጣሊያን
▪ በጥር 2009 የባሕር ላይ ወንበዴዎች አንድን የሳውዲ አረቢያ ነዳጅ ጫኝ መርከብ ጠልፈው 3,000,000 የአሜሪካ ዶላር ካሳ ከተቀበሉ በኋላ አምስቱ ውኃ ውስጥ ሰጥመው ሞተዋል። ከአምስቱ ጠላፊዎች መካከል የአንዱ አስከሬን በውኃው ሞገድ ተገፍቶ በባሕር ዳርቻ የተገኘ ሲሆን በኪሱ ውስጥ በላስቲክ የተቋጠረ 153,000 የአሜሪካን ዶላር ተገኝቷል።—አሶሺዬትድ ፕሬስ፣ ሶማሊያ
ወጣቶች እኩዮቻቸው እንደሚሞላቀቁ ይሰማቸዋል
ዴ ፎልክስክረንት የተሰኘው ጋዜጣ እንደዘገበው ከሆነ በኔዘርላንድ የሚኖሩ ወጣቶች “እኩዮቻቸው እየተሞላቀቁ እንደሆኑ ይሰማቸዋል።” ጋዜጣው እነዚህ ሞልቃቃ ልጆች “ስለራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲኖራቸው ብዙ ማበረታቻ የሚሰጣቸው መሆኑ ለሌሎች አሳቢነት የሌላቸው እንዲሆኑ አድርጓቸዋል” በማለት አትቷል። ጋዜጣው እንደዘገበው ከ16 እስከ 24 ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ወጣቶች መካከል “ከሦስቱ ሁለቱ . . . የወጣቶች መብትና ግዴታ ሊመጣጠን እንዳልቻለ ይሰማቸዋል።” የብዙኃኑ አስተያየት እንደሚያመለክተው “ወጣቶች ብዙ ነገር እንዲደረግላቸው ይጠይቃሉ፤ . . . ሆኖም ለኅብረተሰቡ ምን ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ራሳቸውን አይጠይቁም።”
ልጆች ምሳቸውን ያዘጋጃሉ
ጃፓን ውስጥ የአንድ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ወላጆችና ልጆች አብረው የበለጠ ጊዜ ማሳለፍ የሚችሉበትን መንገድ ሲፈልግ ከቆየ በኋላ ተማሪዎች በወር አንድ ጊዜ ትምህርት ቤት ይዘው የሚመጡትን ምሳ ራሳቸው እንዲያዘጋጁ ሐሳብ አቀረበ፤ ትምህርት ቤቱም ርዕሰ መምህሩ ያቀረበውን ሐሳብ ተቀብሎ አጸደቀው። በአሁኑ ጊዜ በመቶ የሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ ነገር እያደረጉ ነው። አይ ኤች ቲ አሳሂ ሺምቡን የተባለው በጃፓን የሚታተም ጋዜጣ እንዲህ ሲል ዘግቧል፦ “ልጆች ሁሉንም ነገር ራሳቸው እንዲሠሩ ይጠበቅባቸዋል ማለት አይደለም። በተለያየ የክፍል ደረጃ የሚገኙ ልጆች የሚጠበቅባቸው ነገር የተለያየ ነው። በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ዝቅተኛ ክፍሎች ውስጥ የሚማሩ ልጆች የሚሠሩትን የምግብ ዓይነት በመምረጥና የሚያስፈልጉትን ነገሮች በመግዛት ረገድ የወላጅ እገዛ ይደረግላቸዋል። . . . ከዚያ ከፍ ባሉት ክፍሎች የሚገኙ ተማሪዎች ደግሞ የሚሠሩትን የምግብ ዓይነት እንዲመርጡ ይጠበቅባቸዋል።” ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? “ትምህርት ቤቶች ልጆች ምግብ የማዘጋጀት ችሎታቸው እንደተሻሻለ፣ የሚደፋ ምግብ እንደቀነሰና ቤተሰቦች የሚነጋገሩበት አንድ አዲስ ርዕሰ ጉዳይ እንዳገኙ ሪፖርት አድርገዋል” በማለት ጋዜጣው ዘግቧል። በተጨማሪም ልጆች “ወላጆቻቸው የሚያደርጉላቸውን ነገር ማድነቅ እንደጀመሩ” ተናግረዋል።
በደቡብ ዋልታ የተካሄደ የጽዳት ዘመቻ
ባለፈው ዓመት ከሥነ ምሕዳር ጋር በተያያዘ በተካሄደ አንድ ልዩ ፕሮግራም ላይ የተካፈሉ የሩሲያ የዋልታ ምሑራን በአንታርክቲካ ባደረጉት አጠቃላይ የጽዳት ዘመቻ 360 ቶን የሚመዝን ቆሻሻ አስወግደዋል። በደቡብ ዋልታ በሚገኙ የምርምር ጣቢያዎች አካባቢ ከተጣለው ቆሻሻ ውስጥ ጥቅም ላይ ያልዋሉ የግንባታ ቁሳቁሶች፣ የተበላሹ ማሽኖችና ባዶ የነዳጅ በርሜሎች ይገኙበታል። “ለምድር የደቡብ ዋልታ ጫፍ ጥበቃ ለማድረግ በተደረገው ስምምነት መሠረት እያንዳንዱ አገር የራሱን ቆሻሻ የማስወገድ ግዴታ አለበት” በማለት ኢቶጊ የተባለው የሩሲያ መጽሔት ዘግቧል። “ግዴታቸውን በመወጣት ረገድ ከፍተኛ ትጋት ያሳዩት ጃፓናውያን ናቸው።”