‘ጠቢባኑን’ ወደ ኢየሱስ የመራቸው ምን ዓይነት ኮከብ ነው?
‘ጠቢባኑን’ ወደ ኢየሱስ የመራቸው ምን ዓይነት ኮከብ ነው?
በገና ሰሞን የሚነገሩ ታዋቂ የሆኑ ታሪኮች ኮከቡን ከሰማይ እንደታየ ጥሩ ምልክት አድርገው ይገልጹታል። ይህ እውነት ነው?
▪ ኮከቡ ለየት ያለ መሆኑ በምሥራቅ ይኖሩ የነበሩትን “ጠቢባን” ትኩረት እንደሳበውና ይህን ኮከብ ተከትለው ሲሄዱ ሕፃኑ ኢየሱስ ወዳለበት ቦታ እንደደረሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ማቴዎስ ዘግቧል። (ማቴዎስ 2:1-12 አ.መ.ት.) በገና ወቅት የሚነገሩ ታዋቂ የሆኑ ታሪኮች ይህን ኮከብ ከሰማይ እንደታየ ጥሩ ምልክት አድርገው ይገልጹታል። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህ ኮከብ “አምላክ ሕፃኑን ኢየሱስን . . . ለማክበርና በአባቱ የሚወደድ ልጅ መሆኑን ለማሳወቅ አስቀድሞ ካዘጋጃቸው” ምልክቶች አንዱ እንደሆነ ይገልጻል። የገና መዝሙሮችም እንኳ ሳይቀሩ ኮከቡን ያወድሱታል። ይህ ኮከብ ምን ነበር?
አንዳንዶች ኮከቡ በሕዋ ላይ የተከናወነ ተፈጥሯዊ ክስተት ነበር የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። በርካታ ምሑራን ኮከቡ፣ ፕላኔቶች ሲተላለፉ የሚፈጠረው ብርሃን ሊሆን እንደሚችል ሐሳብ አቅርበዋል። ይሁን እንጂ ዘ ኒው ባይብል ዲክሽነሪ “እንዲህ ዓይነቱ ክስተት እንደ ‘ኮከብ’ ተደርጎ ሊጠቀስ እንደማይችል” ይጠቁማል። ብዙ ፕላኔቶች ተጠጋግተው ሲተላለፉ የተከሰተ ክንውን ነው ብለን ብናስብ እንኳ እያንዳንዳቸው የሚፈነጥቁት ብርሃን ለየብቻ ይታያል እንጂ ፕላኔቶቹ አንድ ኮከብ መስለው አይታዩም። አንዳንዶች ደግሞ ጅራታም ኮከብ (comet) ወይም አንድ ኮከብ በመፈንዳቱ የተከሰተ ብርሃን (supernova) ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ከእነዚህ ክስተቶች አንዳቸውም ቢሆኑ ሰዎቹን ወደ አንድ ከተማ በመምራትና አንድ ቤት ጋ ሲደርሱ በመቆም ሕፃኑ ያለበትን ቦታ ሊጠቁሟቸው አይችሉም።
ታዲያ ኮከቡ አንድ ዓይነት ተፈጥሯዊ ክስተት ነበር? ወይስ ኮከቡ እንዲታይ ያደረገው አምላክ ነው? እስቲ አንዳንድ ነጥቦችን እንመልከት፦ “ጠቢባን” የተባሉት ዛሬ ምሑራን እንደምንላቸው ዓይነት ሰዎች ወይም ደግሞ ነገሥታት አይደሉም። “ጠቢባን” የተባሉት ሰዎች በአንዳንድ የአማርኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ እንደተገለጸው “ሰብአ ሰገል” ወይም “ኮከብ ቆጣሪዎች” ናቸው። እነዚህ ሰዎች በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ በተወገዘ ተግባር የሚካፈሉ ነበሩ። (ዘዳግም 18:10-12) ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው ነጥብ ደግሞ ኮከቡን ‘እንዳዩት’ የተገለጹት እነዚህ ኮከብ ቆጣሪዎች ብቻ መሆናቸው ነው። ኮከቡ እውነተኛ ኮከብ ቢሆን ኖሮ ፍንትው ብሎ ለሁሉም ሰው ይታይ ነበር። ንጉሥ ሄሮድስም እንኳ ኮከቡ ስለታየበት ዘመን ዝርዝር ጉዳዮችን ከእነሱ ጠይቆ መረዳት አስፈልጎታል። ይህ ኮከብ፣ ኮከብ ቆጣሪዎቹን መጀመሪያ የመራቸው ሄሮድስ ወደሚኖርባት ወደ ኢየሩሳሌም ሲሆን ሄሮድስ ደግሞ የወደፊቱ መሲሕ ክፉ ጠላት ነበር። በዚህ ጊዜ ሄሮድስ ሕፃኑን ኢየሱስን ለመግደል አልሞ ተነሳ። ከዚያም ኮከቡ አቅጣጫውን ወደ ደቡብ በመለወጥ ኢየሱስ ወዳለበት ወደ ቤተልሔም መራቸው፤ በዚህ መንገድ የሕፃኑን ሕይወት አደጋ ላይ ጣለው።
እነዚህ ነጥቦች ኮከቡ የተላከው ክፉ ከሆነ ምንጭ፣ ምናልባትም ከሰይጣን ዲያብሎስ ሊሆን እንደሚችል ያመለክታሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ዲያብሎስ “በሐሰተኛ ምልክቶችና ድንቅ ነገሮች” እንደሚጠቀም ይገልጻል። (2 ተሰሎንቄ 2:9) በመሆኑም ሰይጣን ለኮከብ ቆጣሪዎቹ ብቻ ኮከብ የሚመስል ነገር እንዲታያቸውና ይህ “ኮከብ” እሱ ሊያጠፋው ወደሚፈልገው የአምላክ ልጅ እንዲመራቸው ማድረግ መቻሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችን ሊያስገርማቸው አይገባም። እርግጥ ነው፣ ነገሮችን በብልሃት በማቀነባበር የይሖዋ አምላክ ዓላማ እንዳይሳካ ማድረግ የሚችል ማንም የለም። በመሆኑም ዲያብሎስ፣ ኢየሱስ ያለጊዜው እንዲሞት ለማድረግ የተጠቀመበት ዘዴ መክሸፉ ምንም አያስደንቅም።
በሌላ በኩል ግን አምላክ የኢየሱስን መወለድ በተአምራዊ መንገድ ለሰዎች አሳውቋል። ኢየሱስ በተወለደበት ሌሊት አንድ መልአክ ለተወሰኑ እረኞች ተገልጦ “አዳኝ” መወለዱን አብስሯቸዋል። በተጨማሪም እረኞቹ ኢየሱስን ሄደው ማየት እንዲችሉ መልአኩ አቅጣጫ አመላክቷቸዋል። ከዚያም የመላእክት ሠራዊት ተገልጠው አምላክን አወደሱ። (ሉቃስ 2:8-14) አምላክ ስለ ኢየሱስ መወለድ ለሰዎች ለመናገር የተጠቀመው በእነዚህ መላእክት እንጂ በዚያ ኮከብ አልነበረም።