ፍቅር የማሳየት አስፈላጊነት
ፍቅር የማሳየት አስፈላጊነት
“ብዙ ጊዜ እቀፊያቸው!” የመጀመሪያ መንታ ልጆቿን ለወለደች አንዲት እናት ይህን የተናገሩት የሕፃናት ሥነ ልቦና ምሑር የሆኑ አንድ ፕሮፌሰር ነበሩ። ይህን የተናገሩት ይህች እናት ልጆቿን ጥሩ አድርጋ ለማሳደግ ምን ማድረግ እንዳለባት ምክር በጠየቀቻቸው ጊዜ ነበር። አክለው እንዲህ ብለዋታል፦ “ፍቅር በተለያዩ መንገዶች ለምሳሌ በማቀፍና በመሳም፣ ወዳጃዊ በመሆን፣ የልጆችን ስሜት በመረዳት፣ ደስተኛና ለጋስ እንዲሁም ይቅር ባይ በመሆን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ደግሞ ተገቢ ቅጣት በመስጠት ሊገለጽ ይችላል። ልጆቻችን እንደምንወዳቸው ያውቃሉ ብለን ፍቅራችንን ከመግለጽ ወደኋላ ማለት የለብንም።”
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በማያሚ፣ ፍሎሪዳ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው መደባበስን አስመልክቶ ጥናት የሚያካሂድ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ቲፋኒ ፊልድ ከላይ በተገለጸው ሐሳብ የሚስማሙ ይመስላል። እኚህ ሴት እንደተናገሩት “እንደ ምግብና አካላዊ እንቅስቃሴ ሁሉ ሕፃናትን መደባበስ ለእድገታቸውና ለጤንነታቸው ወሳኝ ነገር ነው።”
እንደ መዳበስ ያሉ የፍቅር መግለጫዎች ለትልልቅ ሰዎችስ ያስፈልጓቸዋል? እንዴታ! የሥነ ልቦና ሐኪም የሆኑት ክሎድ ስታይነር ካካሄዱት ምርምር በመነሳት በየትኛውም ዕድሜ ላይ እንገኝ፣ በቃልም ሆነ በአካል የሚገለጹ ማበረታቻዎች ለስሜታዊ ጤንነታችን አስፈላጊ እንደሆኑ ተናግረዋል። በአንድ ተቋም ውስጥ የሚኖሩ በርካታ አረጋውያንን የምትንከባከብ ሎረ የተባለች ነርስ እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “በተለያዩ መንገዶች ለአረጋውያን ፍቅር ማሳየት ትልቅ ለውጥ እንደሚያመጣ አስተውያለሁ። በደግነት የምትይዟቸውና የምትደባብሷቸው ከሆነ አመኔታቸውን ታተርፋላችሁ፤ አልፎ ተርፎም የምትሰጧቸውን መመሪያዎች ለመከተል ፈቃደኛ ይሆናሉ። ከዚህም በላይ እንዲህ ባለ መንገድ ፍቅራችንን መግለጻችን ክብራቸውን እንደጠበቅንላቸው ያሳያል።”
በተጨማሪም ፍቅርን መግለጽ ለሚቀበለው ብቻ ሳይሆን ለሰጪውም ይጠቅማል። ኢየሱስ ክርስቶስ በአንድ ወቅት እንደተናገረው “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።” (የሐዋርያት ሥራ 20:35) በተለይ ደግሞ ለተጨነቁ፣ ተስፋ ለቆረጡ ወይም ስጋት ላደረባቸው ሰዎች ፍቅር ማሳየት መልሶ የሚክስ ነው። እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠማቸው ሰዎች በዚህ መንገድ እንዴት እርዳታ እንዳገኙ የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናገኛለን።
‘መላ ሰውነቱን የሥጋ ደዌ ወርሶት’ የነበረ አንድ ሰው ከማኅበረሰቡ ተገልሎ ስለሚኖር ማንም ሰው ነክቶት አያውቅም ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ይህን ሰው በርኅራኄ ተነሳስቶ በዳበሰው ጊዜ ምን ያህል ተጽናንቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም!—ሉቃስ 5:12, 13፤ ማቴዎስ 8:1-3
አረጋዊ የነበረው ነቢዩ ዳንኤል አንድ መልአክ ሞቅ ያለ ማበረታቻ ሲሰጠውና ሦስት ጊዜ ሲዳብሰው ምን ያህል ብርታት እንዳገኘ መገመት ትችላለህ። ዳንኤል የደከመ አካሉንና የዛለ አእምሮውን ለማደስ ያስፈልገው የነበረው ነገር የሚያንጹ ቃላትን መስማትና መዳሰስ ብቻ ነበር።—ዳንኤል 10:9-11, 15, 16, 18, 19
በአንድ ወቅት የሐዋርያው ጳውሎስ ወዳጆች እሱን ለማግኘት 50 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዘው ከኤፌሶን ወደ ሚሊጢን መጥተው ነበር። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ በድጋሚ ላያዩት እንደሚችሉ ነገራቸው። እነዚህ ታማኝ ወዳጆቹ ‘አንገቱን እቅፍ አድርገው ሲስሙት’ ጳውሎስ በጣም ተበረታቶ መሆን አለበት!—የሐዋርያት ሥራ 20:36, 37
መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ በዘመናችን የተደረጉ ጥናቶች አንዳችን ለሌላው ፍቅር እንድናሳይ ያበረታቱናል። ይህን መሠረታዊ ፍላጎት ማሟላት አካላዊና ስሜታዊ ጥቅም ያስገኛል። ከዚህ በግልጽ መመልከት እንደሚቻለው ተገቢ የሆነና ከልብ የመነጨ የፍቅር መግለጫ የሚያስፈልጋቸው ልጆች ብቻ አይደሉም።