በአምላክ ማመን ምክንያታዊ ነው?
በአምላክ ማመን ምክንያታዊ ነው?
ከአቶም ቅንጣቶች አንስቶ ግዙፍ እስከሆኑት ጋላክሲዎች ድረስ ያሉት ነገሮች ዝንፍ በማይል የሒሳብ ሕግ የሚመሩ መሆናቸው አስገርሞህ ያውቃል? ስለ ሕይወትስ አሰላስለህ ታውቃለህ? ማለትም ሕይወት ያላቸው ነገሮች ዓይነታቸው ስለ መለያየቱ፣ ውስብስብ ስለ መሆናቸውና በጣም አስደናቂ ንድፍ ያላቸው ስለ መሆኑ ቆም ብለህ አስበህ ታውቃለህ? ብዙ ሰዎች አጽናፈ ዓለም በአጋጣሚ እንደተገኘ፣ በውስጡ ያለው ሕይወት ደግሞ በዝግመተ ለውጥ እንደመጣ ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ባለው ፈጣሪ እንደተፈጠረ ይሰማቸዋል። ይበልጥ ምክንያታዊ የሆነው አመለካከት የትኛው ይመስልሃል?
እርግጥ ነው፣ ሁለቱም አመለካከቶች እምነት የሚጠይቁ ናቸው። በአምላክ ማመን እምነት ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው “በየትኛውም ጊዜ ቢሆን አምላክን ያየው አንድም ሰው የለም።” (ዮሐንስ 1:18) በተመሳሳይም አጽናፈ ዓለም እንዴት እንደተሠራ ወይም ሕይወት እንዴት እንደ ጀመረ ያየ ሰው የለም። እንዲሁም አንድ የሕይወት ዓይነት በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ተሻሽሎ ወይም ተለውጦ ሌላ ዓይነት ሕይወት ሲሆን ያየ ሰው የለም። በቅሪተ አካላት ላይ የሚደረገው ምርምር፣ ዋና ዋና የሚባሉት የእንስሳ ዓይነቶች በድንገት ሕያው እንደሆኑና እስካሁንም ምንም ሳይለወጡ እንደቆዩ ያሳያል። * ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ወሳኝ ጥያቄ ይነሳል፤ ይህ ጥያቄ ‘ጽኑ መሠረት ያለው በዝግመተ ለውጥ ማመን ነው ወይስ በፈጣሪ ማመን?’ የሚል ነው።
እምነትህ ተአማኒነት ባለው ማስረጃ ላይ የተመሠረተ ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ትክክለኛ “እምነት . . . እውነተኛዎቹ ነገሮች ባይታዩም እንኳ መኖራቸውን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው” ይላል። (ዕብራውያን 11:1) ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል ከላይ ያለውን ጥቅስ “እምነት . . . የማናያቸው እውነተኛ ነገሮች ስለመኖራቸው እርግጠኛ እንድንሆን ያደርገናል” በማለት ተርጉሞታል። ይህ ሲባል በጽኑ የምታምንባቸው በርካታ የማይታዩ እውነታዎች ወደ አእምሮህ እንደሚመጡ ምንም ጥርጥር የለውም።
ይህን ለመረዳት አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ የብዙዎችን አክብሮት ያተረፉ በርካታ ታሪክ ጸሐፊዎች ታላቁ እስክንድር፣ ጁሊየስ ቄሳርና ኢየሱስ ክርስቶስ በሕይወት የነበሩ ሰዎች እንደነበሩ ያምናሉ። እነዚህ ታሪክ ጸሐፊዎች እንዲህ ብለው ለማመን የሚያስችል ተጨባጭ ማስረጃ አላቸው? አዎን፣ ምክንያቱም ተአማኒነት ያላቸውን የታሪክ ማስረጃዎች መጥቀስ ይችላሉ።
የሳይንስ ሊቃውንትም ቢሆኑ በማይታዩ እውነታዎች ያምናሉ፤ ምክንያቱም እነዚህ እውነታዎች ለመኖራቸው “ተጨባጭ ማስረጃ” አላቸው። ለምሳሌ ያህል፣ በ19ኛው መቶ ዘመን የኖሩት ድሚትራይ ሚንደሌቭ የተባሉ ሩሲያዊ የኬሚስትሪ ሊቅ፣ ጽንፈ ዓለም የተሠራባቸው መሠረታዊ ንጥረ ነገሮች (elements) እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት ትኩረታቸውን ስቦት ነበር። ሚንደሌቭ እነዚህ ንጥረ ነገሮች የሚያመሳስሏቸው የጋራ ባሕርያት እንዳሏቸውና በአቶም ክብደታቸውና በኬሚካላዊ ባሕርያቸው መሠረት በቡድን ሊከፈሉ እንደሚችሉ ተገንዝበው ነበር። በእያንዳንዱ ቡድን ውስጥ በተካተቱት ንጥረ ነገሮች ቅደም ተከተል እምነት በማሳደራቸው ምክንያት ንጥረ ነገሮቹን በቡድን በቡድን ከፋፍለው ፔሬዲክ ቴብል የተባለ ሰንጠረዥ የሠሩ ከመሆኑም በላይ አንዳንድ ንጥረ ነገሮች በወቅቱ ባይታወቁም እንኳ በእርግጥ እንዳሉ በትክክል መተንበይ ችለው ነበር።
አርኪኦሎጂስቶች በጥንት ዘመን ስለነበሩት ሥልጣኔዎች አንድ መደምደሚያ ላይ የሚደርሱት ብዙውን ጊዜ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ተቀብረው በቆዩ ዕቃዎች ላይ ምርምር በማድረግ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ አርኪኦሎጂስት ሲቆፍር በጥንቃቄ ተስተካክለው የተቆረጡና ተመሳሳይ መጠን ያላቸው ብዙ ድንጋዮች አንዱ በአንዱ ላይ ተነባብሮ አገኘ እንበል። እንዲሁም ድንጋዮቹ አንዱ በአንዱ ላይ የተገነቡት ልዩ በሆነ ንድፍ ነው። ታዲያ አርኪኦሎጂስቱ ይህን ሲመለከት ምን መደምደሚያ ላይ ይደርሳል? ይህ ግኝት አጋጣሚ የፈጠረው ነገር እንደሆነ ይሰማዋል? እንደማይሰማው የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ ጥንት የነበሩ ሰዎች ያከናውኑ ለነበረው ተግባር
እንደ ማስረጃ አድርጎ ይመለከተዋል፤ ደግሞም ትክክለኛ የሆነው መደምደሚያ ይህ ነው።ከዚህ ጋር በሚስማማ መልኩ በተፈጥሮ ላይ የሚንጸባረቀውን ንድፍ ስንመለከት ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ መድረሳችን ምክንያታዊ አይሆንም? በብዙዎች ዘንድ አክብሮት ያተረፉ የሳይንስ ሊቃውንትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች እንዲህ ያለ አመለካከት አላቸው።
በአጋጣሚ የተገኘ ነው ወይስ ዓላማ ያለው ንድፍ አውጪ አለው?
የሒሳብና የፊዚክስ ሊቅ እንዲሁም የሥነ ፈለክ ተመራማሪ የነበሩት ብሪታንያዊው ሰር ጄምስ ጂንስ፣ እያደገ ከመጣው ሳይንሳዊ እውቀት አንፃር ስንመለከተው “አጽናፈ ዓለም” እኛ ባለን አእምሮ የሚንጸባረቅ ችሎታና ባሕርይ ባሉት ‘የረቀቀ የሒሳብ ሊቅ አማካኝነት የተሠራ ይመስላል’ በማለት ጽፈው ነበር።
ጂንስ ይህን ሐሳብ ከጻፉ ወዲህ ሌሎች የሳይንስ ሊቃውንትም ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። የፊዚክስ ሊቅ የሆኑት ፖል ዴቪስ “በዛሬው ጊዜ ላሉ በርካታ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች የአጽናፈ ዓለም አጠቃላይ አደረጃጀት የረቀቀ ንድፍ እንዳለው ይጠቁማቸዋል” በማለት ጽፈዋል። የምንጊዜም የሒሳብ ሊቅና ስመ ጥር የፊዚክስ ሊቅ የሆነው አልበርት አንስታይንም “[ተፈጥሮ] ሊታወቅ የሚችል መሆኑ ተአምር ነው” በማለት ጽፏል። በብዙ ሰዎች አስተያየት ይህ ተአምር ሕይወትን ማለትም ሕይወት ከተዋቀረባቸው ረቂቅ ሕዋሳት አንስቶ በጣም አስደናቂ እስከሆነው እስከ ሰው አንጎል ድረስ ያሉ ነገሮችን ይጨምራል።
ዲ ኤን ኤ እና የሰው አንጎል
ዲ ኤን ኤ ከሴሎች ለተሠሩ ሕያዋን ነገሮች በሙሉ ባሕርያቸውን የሚወስን እንዲሁም የዘር ባሕርይ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ የሚረዳ መሠረታዊ ሞለኪዩል ነው። * ዲ ኤን ኤ በኬሚካል መልክ የተዘጋጀ በጣም ብዙ ሚስጥራዊ መረጃዎችን አጭቆ ስለያዘና ሚስጥሩን ለመፍታት ብሎም ወደ ሥራ ለመለወጥ በሚያስችል ሞለኪዩላዊ ሁኔታ ውስጥ ስለተቀመጠ አንዳንዶች ይህን ውስብስብ አሲድ ከአንድ ንድፍ (blueprint) ወይም ከምግብ አዘገጃጀት መምሪያ ጋር ያነጻጽሩታል። በዲ ኤን ኤ ውስጥ ምን ያህል መረጃ ይገኛል? አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው ኑክሊዮታይድ ተብለው የሚጠሩት የዲ ኤን ኤ የመጨረሻ ክፍልፋዮች ወደ ፊደል ቢለወጡ “ከሚሊዮን የሚበልጡ ገጾች ያሉት አንድ መጽሐፍ ሊወጣቸው” ይችላል።
ዲ ኤን ኤ ሕይወት ባላቸው በአብዛኞቹ ነገሮች ውስጥ እርስ በርስ ተጠላልፎ ክር መሳይ ነገር የሚፈጥር ሲሆን ይህም ክሮሞሶም ተብሎ ይጠራል፤ እነዚህ ክሮሞሶሞች በእያንዳንዱ ሴል አስኳል ውስጥ በአስተማማኝ ሁኔታ ተቀምጠዋል። የሴሎቹ አስኳሎች በአማካይ ዲያሜትራቸው ሲለካ 5 ማይክሮ ሜትር * ያህል ነው። እስቲ አስበው፣ ልዩ የሆነውን አካልህን ያስገኘው ያ ሁሉ መረጃ የተቀመጠው በአጉሊ መነፅር ብቻ በሚታዩ በጣም ትንንሽ ጥቅልሎች ውስጥ ነው! አንድ የሳይንስ ሊቅ ሕይወት ያላቸው ነገሮች “መረጃን አጭቆ በመያዝና በተፈለገው ጊዜ መልሶ በመስጠት ረገድ ፈጽሞ ተወዳዳሪ” እንደሌላቸው መናገራቸው የተገባ ነው። ስለ ኮምፒውተር ቺፕሶች፣ ዲቪዲዎችና እነዚህን ስለመሳሰሉ ነገሮች ስናስብ ዲ ኤን ኤ ስላለው መረጃ የመያዝ አቅም በጣም መደነቃችን አይቀርም! የሚገርመው ደግሞ ስለ ዲ ኤን ኤ ገና ያልታወቁ ብዙ ነገሮች መኖራቸው ነው። “እያንዳንዱ ግኝት ሌላ ውስብስብ ነገር እንዳለ ይጠቁማል” በማለት ኒው ሳይንቲስት መጽሔት ይናገራል። *
ታዲያ እንዲህ ያለው የረቀቀ ንድፍና አደረጃጀት የተገኘው በአጋጣሚ ነው ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው? ረቀቅ ባለ ሁኔታ በጥንቃቄ የተጻፈ ባለ ሚሊዮን ገጽ ቴክኒክ ነክ መምሪያ መጽሐፍ በድንገት ብታገኝ ይህ መጽሐፍ ጸሐፊ ሳይኖረው በራሱ የተገኘ ነው ብለህ ታስባለህ? መጽሐፉ በጣም ትንሽ ከመሆኑ የተነሳ ያለ አጉሊ መነፅር ልታነበው የማትችል ቢሆንስ? በሌላ በኩል ደግሞ ይህ መጽሐፍ ያላንዳች መዛነፍ በትክክለኛው ሰዓትና በትክክለኛው መንገድ የሚገጣጠሙ በቢሊዮን የሚቆጠሩ ክፍሎች ያሉት ራሱን በራሱ የሚጠግን እንዲሁም አምሳያውን የሚተካ የማሰብ ችሎታ ያለው ማሽን ለመሥራት የሚያስችል ትክክለኛ መመሪያ የያዘ ቢሆንስ? ማንም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱ መጽሐፍ በአጋጣሚ የመጣ ነው ብሎ እንደማያስብ የተረጋገጠ ነው።
በአንድ ወቅት አምላክ የለሽነትን ወግነው ሲሟገቱ የነበሩት አንተኒ ፍሉ የተባሉ ብሪታንያዊ ፈላስፋ፣ በጊዜያችን ስለ ሴል ውስጣዊ አሠራር የሚደረገውን ጥናት ከመረመሩ በኋላ እንደሚከተለው ብለው ተናግረዋል፦ “(ሕይወትን) ለማስገኘት የሚያስፈልጉት ነገሮች ለማመን በሚያዳግት መልኩ ውስብስብ መሆናቸው የማሰብ ችሎታ እንደተንጸባረቀበት [ያሳያል]።” ፍሉ “ማስረጃው የሚያደርሰው የትም ይሁን የት ያንን መከተል” እንደሚፈልጉ ተናግረዋል። ደግሞም ማስረጃው ሙሉ በሙሉ አስተሳሰባቸው እንዲለወጥ ይኸውም በአምላክ መኖር እንዲያምኑ አድርጓቸዋል።
በርካታ የሳይንስ ሊቃውንትን በግርምት እንዲዋጡ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል የሰው አንጎል ይገኝበታል። የዲ ኤን ኤ ውጤት የሆነው አንጎል “በአጽናፈ ዓለም ውስጥ እጅግ ውስብስብ የሆነው ነገር” ተብሎ ተገልጿል። እጅግ ዘመናዊ የሚባለው ኮምፒውተር እንኳ ከነርቭ ሴሎችና ከሌሎች ነገሮች ከተዋቀረው፣ ሐምራዊ ግራጫ መልክ ካለውና 1.3 ኪሎ ግራም ገደማ ከሚመዝነው አንጎል ጋር ሲነጻጸር በጣም
ኋላ ቀር ነው። አንድ የነርቭ ሳይንቲስት እንደተናገሩት የሳይንስ ሊቃውንት ስለ አንጎልና ስለ አስተሳሰብ ባወቁ መጠን “ይበልጥ ዕፁብ ድንቅ ብሎም ከመረዳት ችሎታ በላይ እየሆነባቸው ይሄዳል።”እስቲ አስበው፦ አንጎል እንድንተነፍስ፣ እንድንስቅ፣ እንድናለቅስ፣ እንቆቅልሾችን እንድንፈታ፣ ኮምፒውተሮችን እንድንሠራ፣ ብስክሌት እንድንነዳ፣ ግጥም እንድንጽፍና የሌሊቱን ሰማይ ስንመለከት በአድናቆትና በአክብሮት ስሜት እንድንዋጥ ያስችለናል። ታዲያ እነዚህን ችሎታዎችና ተሰጥኦዎች ያገኘነው የማሰብ ችሎታ በማይንጸባረቅበት ዝግመተ ለውጥ ነው ብሎ ማመን ምክንያታዊ ነው?
በማስረጃ ላይ የተመሠረተ እምነት
የሰውን ዘር በሚመለከት አንዳንድ ጥያቄዎች ሲፈጠሩብን የዝግመተ ለውጥ አራማጆች እንደሚያደርጉት ከሰው በሚያንሱት ጦጣዎችና ሌሎች እንስሳት ላይ ምርምር ማድረግ ይኖርብናል? ወይስ ትክክለኛ መልስ ለማግኘት ከእኛ በላይ ወደሆነው አምላክ መመልከት ይኖርብናል? እርግጥ ነው፣ ከእንስሳት ጋር የሚያመሳስሉን አንዳንድ ነገሮች አሉ። እኛም እንደ እንስሳት መብላት፣ መጠጣትና መተኛት ይኖርብናል፤ እንዲሁም ዘር የመተካት ችሎታ አለን። ያም ሆኖ ከእንስሳት በብዙ መንገዶች እንለያለን። ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ከእንስሳት ልዩ የሚያደርጉንን ባሕርያት ያገኘነው ከእኛ በላይ ከሆነ አካል ይኸውም ከአምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ የሰውን ዘር ከሥነ ምግባርና ከመንፈሳዊ አንጻር “በራሱ መልክ” እንደፈጠረው በመግለጽ ይህን ሐሳብ ቅልብጭ ባለ አነጋገር ያስቀምጠዋል። (ዘፍጥረት 1:27) ታዲያ ስለ አምላክ ባሕርያት ለምን አታሰላስልም? አንዳንዶቹ የአምላክ ባሕርያት በዘዳግም 32:4፣ በያዕቆብ 3:17, 18 እንዲሁም በ1 ዮሐንስ 4:7, 8 ላይ ተመዝግበው ይገኛሉ።
ፈጣሪያችን በዙሪያችን ያለውን ዓለም ለመመርመርና ለጥያቄዎቻችን አጥጋቢ መልስ ለማግኘት የሚያስችለንን “የማስተዋል ችሎታ” ሰጥቶናል። (1 ዮሐንስ 5:20) የፊዚክስ ሊቅና የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ዊሊያም ፊሊፕስ ይህን በሚመለከት እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል፦ “አጽናፈ ዓለም በሥርዓት የተደራጀ፣ ሊታወቅ የሚችልና ውብ መሆኑን ስመረምር የማየውን ነገር የሠራው ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ ያለው ንድፍ አውጪ ነው ወደሚል መደምደሚያ እደርሳለሁ። ያደረግኩት ሳይንሳዊ ጥናት፣ ቁስ አካልና ኃይል እርስ በርስ ዝንፍ የማይል ትስስር ያላቸው እንዲሁም በቀላሉ ሊታወቁ የሚችሉ መሆናቸውን መገንዘቤ በአምላክ ላይ ያለኝን እምነት ያጠናክረዋል።”
ከሁለት ሺህ ዓመታት ገደማ በፊት ተፈጥሮን ልብ ብሎ የተመለከተ አንድ አስተዋይ ሰው “የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል” በማለት ጽፏል። (ሮም 1:20) ይህን የጻፈው ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ ሲሆን ስለ ሙሴ ሕግ ጠንቅቆ የተማረ ነበር። በማስረጃ ላይ የተመሠረተው እምነቱ አምላክ እውን እንዲሆንለት ያደረገ ሲሆን የፍትሕ ስሜቱ ደግሞ አምላክን ስለ ፍጥረት ሥራዎቹ የሚገባውን ምስጋናና ክብር እንዲሰጠው ገፋፍቶታል።
አንተም በአምላክ ማመን ፍጹም ምክንያታዊ መሆኑን እንደምታስተውል ከልብ ተስፋ እናደርጋለን። አምላክ መኖሩን በማመን ብቻ ሳትወሰን ልክ እንደ ጳውሎስ ከዚያ ያለፈ ነገር እንደምታደርግ እንተማመናለን። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዳደረጉት ሁሉ አንተም ይሖዋ በሰው ልብ ውስጥ የሚያስተጋቡና ወደ እሱ እንድንቀርብ የሚገፋፉ ተወዳጅ ባሕርያት ያሉት መንፈሳዊ አካል እንደሆነ ይበልጥ እንድትገነዘብ ምኞታችን ነው።—መዝሙር 83:18 NW፤ ዮሐንስ 6:44፤ ያዕቆብ 4:8
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 በመስከረም 2006 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳብ ተጨባጭ ሐቅ ነው?” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
^ አን.14 ዲ ኤን ኤ የሚለው ምህጻረ ቃል ዲኦክሲራይቦኑክሊክ አሲድ የሚለውን ቃል የሚያመለክት ነው።
^ አን.15 ማይክሮሜትር የአንድ ሜትር አንድ ሚሊዮንኛ ነው።
^ አን.15 ቻርልስ ዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሐሳቡን በቀመረበት ወቅት አንድ ሕያው ሴል ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ቅንጣት ታክል እውቀት አልነበረውም።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በሃይማኖት ስም የሚፈጸመው ክፋት በአምላክ ላለማመን ሰበብ ይሆናል?
በርካታ ሰዎች በፈጣሪ የማያምኑት የብዙ ሃይማኖቶች ታሪክ በግፍና በምግባረ ብልሹነት እጅግ የጎደፈ በመሆኑ ነው። ይሁን እንጂ ይህ በፈጣሪ ላለማመን ምክንያት ሊሆን ይችላል? በፍጹም። ሮይ አብርሃም ቨርጊዝ አምላክ አለ የሚል ርዕስ ባለው የአንተኒ ፍሉ መጽሐፍ መቅድም ላይ ሲጽፉ “የኑክሌር ስጋት E=mc2 * ከሚለው ፎርሙላ ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ ሁሉ የሃይማኖቶች መብዛትና የሚፈጽሙት ግፍም ከአምላክ ሕልውና ጋር ምንም ግንኙነት የለውም” ብለዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.32 ኃይል እኩል ይሆናል ክብደት ሲባዛ የብርሃንን ፍጥነት በሁለት ኃይል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በቁፋሮ የተገኘ አንድ ጥንታዊ የግንባታ ሥራ ስንመለከት በሰዎች ተሠርቷል የሚል መደምደሚያ ላይ እንደርሳለን፤ ታዲያ በተፈጥሮ ላይ የሚታየውን ንድፍ ስንመለከት ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አልበርት አንስታይን
[በገጽ 24, 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ዲ ኤን ኤ የማሰብ ችሎታ ላላቸው ሕያዋን ነገሮች ዝንፍ የማይሉ መመሪያዎችን የያዘ በአጉሊ መነፅር እንደሚታይ መጽሐፍ ነው
[በገጽ 25 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የሰው አንጎል “በአጽናፈ ዓለም ውስጥ እጅግ ውስብስብ የሆነው ነገር” ተብሎ ተገልጿል
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
© The Print Collector/age fotostock