ተጨማሪ ጊዜ እንዲኖርህ ትፈልጋለህ?
ተጨማሪ ጊዜ እንዲኖርህ ትፈልጋለህ?
በስተ ቀኝ ለተዘረዘሩት ጥያቄዎች ከቀረቡት ምርጫዎች መካከል በአብዛኛው በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ላይ ምልክት ካደረግክ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልግህ ይሆናል። እርግጥ እንዲህ የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። በሁሉም ቦታ የሚኖሩ ሰዎች ማለት ይቻላል የግድ መሠራት ያለበትን ነገር ለመሥራት በሚያደርጉት ጥረት ጊዜያቸው የተጣበበ ነው፤ ይህ ሥራ እነሱ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ ከሚሰማቸው ነገር ጋር ምንም ግንኙነት ላይኖረው ይችላል። አብዛኛው ጊዜያቸው የሚያልፈው መኪና በማስጠገን፣ የአለቃቸውን ፈቃድ በመፈጸም፣ ያልተጠበቁ ሁኔታዎችን በማስተናገድና እንደነዚህ ያሉ አፋጣኝ ትኩረት የሚያሻቸውን ነገሮች በማከናወን ሊሆን ይችላል። አንተም ተደራራቢ ሁኔታዎችን በማስተናገድ ስለምትወጠር ጊዜህን እንዴት እንደምትጠቀምበት መወሰን እንዳልቻልክ ሊሰማህ ይችላል። አልፎ ተርፎም ሕይወትን ሳታጣጥመው እያለፈብህ እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል።
እርግጥ ነው፣ ይህ የሚሆነው ለጊዜው ነው ብለህ ታስብ ይሆናል። ውሎ አድሮ የተረጋጋ ሕይወት እንደሚኖርህና ይበልጥ አስፈላጊ በሆኑ ነገሮች ማለትም ለአንተም ሆነ ለቤተሰብህ ብሎም ለሌሎች እርካታ በሚያመጡ ነገሮች ላይ ትኩረት ለማድረግ የሚያስችልህን ጊዜ እንደምታገኝ ታስባለህ። ይሁንና ይህ የሚሆነው መቼ ነው? በዛሬዋ ዕለት በፕሮግራምህ ውስጥ ክፍት ጊዜ የምታገኝ ይመስልሃል? በዚህ ሳምንትስ? በሚቀጥለው ወርስ?
በዓለም ውስጥ የሚታየው ሩጫ የተረጋጋ ይሆናል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ይሁንና የሚያስፈልግህን ጊዜ ለማግኘት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በጣም አስፈላጊ ለምትላቸው ነገሮች ጊዜ የምትመድበው መቼ መቼ ነው?
○ በየቀኑ
○ ቅዳሜና እሁድ
○ ከስንት አንዴ
በዕለታዊ ሕይወትህ
○ ለማድረግ ያቀድከውን ታከናውናለህ?
○ ከዕቅድህ ውጭ ሌላ ሥራ ለማከናወን ትገደዳለህ?
○ የሚያጋጥምህን ማንኛውንም ነገር ያለማንገራገር ታከናውናለህ?
በዕለታዊ ሕይወትህ
○ ጊዜህን በምትፈልገው መንገድ እንደምታሳልፍ ይሰማሃል?
○ ምክንያታዊ ያልሆኑ ነገሮችን ለማስተናገድ ስለምትገደድ ጫና እንደበዛብህ ይሰማሃል?
○ ሕይወትህ ከቁጥጥርህ ውጭ እንደሆነና ተደራራቢ ሁኔታዎች ፋታ እንዳሳጡህ ይሰማሃል?
በቀኑ መገባደጃ ላይ
○ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች እንዳከናወንክ ይሰማሃል?
○ አስፈላጊ የሆኑ ሥራዎችን ጥሩ አድርገህ እንዳልሠራህ ይሰማሃል?
○ ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑት ነገሮች ጊዜ አጥተህ እንደነበር ይሰማሃል?
ብዙ ጊዜ በቀኑ መገባደጃ ላይ ምን ይሰማሃል?
○ እርካታና ደስታ
○ ባዶነት፣ ድካምና ውጥረት
○ ብስጭት