በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በአንደበት አጠቃቀም ረገድ ጥበብ ማሳየት

በአንደበት አጠቃቀም ረገድ ጥበብ ማሳየት

በአንደበት አጠቃቀም ረገድ ጥበብ ማሳየት

‘ምነው ምላሴን በቆረጠው!’ ብለህ ታውቃለህ? ምላስን ወይም አንደበትን መቆጣጠር ለሁላችንም ቢሆን ቀላል እንዳልሆነ የታወቀ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው የሰው ልጆች ከሞላ ጎደል ሁሉንም ዓይነት እንስሳት መግራት ይችላሉ፤ “ምላስን ግን ሊገራ የሚችል አንድም ሰው የለም።” (ያዕቆብ 3:7, 8) ታዲያ አንደበታችንን ለመቆጣጠር ምንም ጥረት ማድረግ የለብንም ማለት ነው? በፍጹም! ይህን ትንሽ ሆኖም ኃይለኛ የሰውነት ክፍል በመቆጣጠር ረገድ ይበልጥ እንዲሳካልን የሚረዱንን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች እንመልከት።

“ከቃላት ብዛት ኀጢአት አይታጣም፤ አንደበቱን የሚገታ ግን ጠቢብ ነው።” (ምሳሌ 10:19) ብዙ በተናገርን ቁጥር ሞኝነት የሚንጸባረቅበት አልፎ ተርፎም ጎጂ የሆነ ነገር የመናገር አጋጣሚያችን ይጨምራል። በእርግጥም ያልተገታ ምላስ እንደ እሳት በመሆን ሐሜትንና ስም ማጥፋትን በፍጥነት ሊያዛምት ይችላል። (ያዕቆብ 3:5, 6) ይሁን እንጂ ‘አንደበታችንን የምንገታ’ በሌላ አባባል ከመናገራችን በፊት የምናስብ ከሆነ የምንናገረው ነገር ምን ውጤት እንደሚያስከትል እናመዛዝናለን። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በአስተዋይነታችን የምንታወቅ ከመሆኑም በላይ የሌሎችን አክብሮትና አመኔታ እናተርፋለን።

“ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየና ለቁጣ የዘገየ መሆን አለበት።” (ያዕቆብ 1:19) ሰዎች በሚናገሩበት ጊዜ በትኩረት ስናዳምጣቸው ደስ ይላቸዋል፤ ምክንያቱም እንዲህ ማድረጋችን እንደምናስብላቸው ብቻ ሳይሆን እንደምናከብራቸውም ጭምር ያሳያል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው የሚያስቀይም ወይም የሚያስቆጣ ነገር ቢናገርስ? ተመሳሳይ ምላሽ ባለመስጠት ‘ለቁጣ የዘገየን’ ለመሆን ጥረት ማድረግ አለብን። ደግሞስ ማን ያውቃል፤ ግለሰቡ በሌላ ነገር ተበሳጭቶ ሊሆንና ደግነት ለጎደለው ንግግሩ ይቅርታ ሊጠይቀን ይችላል። ይሁንና “ለቁጣ የዘገየ መሆን” ከባድ ሆኖብሃል? እንግዲያው ራስህን መግዛት እንድትችል አምላክ እንዲረዳህ ጸልይ። አምላክ እንዲህ ያሉትን ልባዊ ጸሎቶች ችላ አይልም።—ሉቃስ 11:13

“ለስላሳ አንደበትም ዐጥንት ይሰብራል።” (ምሳሌ 25:15) ብዙዎች እንደሚያስቡት ለስላሳ ወይም ገራም መሆን የድክመት ምልክት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ሰው እንደ አጥንት ከባድና ደረቅ የሆነ ተቃውሞ ቢሰነዝርብን በለሰለሰ አንደበት መልስ መስጠታችን ተቃውሞውን ሊያበርደው ይችላል፤ ምናልባትም ግለሰቡ ይህን ያደረገው በቁጣ ወይም በጭፍን ጥላቻ ተነሳስቶ ሊሆን ይችላል። በተለይ በተጋጋለ ሁኔታ ውስጥ ስንሆን ገርነት ማሳየት ተፈታታኝ ሊሆንብን እንደሚችል አሌ የማይባል ሐቅ ነው። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር መፈጸም ያሉትን ጥቅሞች፣ አለመፈጸም ደግሞ የሚያስከትላቸውን መዘዞች አስብ።

በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ‘ከላይ ከሆነው ጥበብ’ የሚካተቱ ናቸው። (ያዕቆብ 3:17) ይህን ጥበብ በአንደበት አጠቃቀማችን ረገድ በተግባር ማዋላችን፣ በተገቢው ጊዜ እንድንናገር ስለሚያደርገን ንግግራችን “በብር መደብ ላይ እንደ ተቀረጸ የወርቅ እንኮይ” ውብ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ያስከብረናል፣ ያስወድደናል እንዲሁም ሌሎችን የሚያንጽ ይሆናል።—ምሳሌ 25:11