ትምህርቴን ማቋረጥ ይኖርብኛል?
የወጣቶች ጥያቄ
ትምህርቴን ማቋረጥ ይኖርብኛል?
እስከ ስንተኛ ክፍል ድረስ መማር የሚኖርብህ ይመስልሃል?
․․․․․
ወላጆችህ እስከ ስንተኛ ክፍል እንድትማር ይፈልጋሉ?
․․․․․
ለሁለቱም ጥያቄዎች የሰጠኸው መልስ ተመሳሳይ ነው? መልሶችህ ተመሳሳይ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ያም ሆኖ ትምህርት ቤት እየተመላለስክ ከሆነ ትምህርትህን የምታቋርጥበት ቀን ይናፍቅህ ይሆናል። ከዚህ በታች እንደቀረቡት ያሉ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ መጥተው ያውቃሉ?
● “አንዳንድ ጊዜ በጣም ውጥረት ስለሚበዛብኝ ከአልጋዬ መነሳት አልፈልግም ነበር። ‘ወደፊት ፈጽሞ የማልጠቀምባቸውን ነገሮች ለመማር ትምህርት ቤት መሄድ የሚያስፈልገኝ ለምንድን ነው?’ እያልኩ አስብ ነበር።”—ሪቼል
● “ብዙ ጊዜ ትምህርት ቤት መሄድ ስለሚሰለቸኝ ትምህርቴን አቋርጬ ሥራ መያዝ እፈልግ ነበር። ትምህርት ቤት መሄድ ምንም እንደማይሠራልኝ ከዚህ ይልቅ ጊዜዬን ገንዘብ ለማግኘት ብጠቀምበት እንደሚሻል ይሰማኝ ነበር።”—ጆን
● “በየቀኑ ማታ ማታ ለአራት ሰዓት ያህል የቤት ሥራ መሥራት ይጠበቅብኝ ነበር! የቤት ሥራዎች፣ ፕሮጀክቶችና ፈተናዎች በላይ በላዩ እየተደራረቡ በጣም ስለሚያጨናንቁኝ ትምህርቴን መቀጠል ከባድ እንደሆነና ማቋረጥ እንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር።”—ሲንዲ
● “በቦምብ ጥቃት እንደሚፈጸምብን ማስፈራሪያ ደርሶን ነበር። ሦስት ተማሪዎች ራሳቸውን ለማጥፋት ሞክረዋል፤ አንድ ተማሪ ደግሞ ራሱን አጥፍቷል። እንዲሁም ተማሪዎች በቡድን ተደራጅተው ይደባደቡ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎቹ ከአቅሜ በላይ እንደሆኑ ስለሚሰማኝ ከትምህርት ቤት መልቀቅ እፈልግ ነበር!”—ሮዝ
አንተም ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮች አጋጥመውሃል? ከሆነ ትምህርትህን ለማቋረጥ እንድታስብ ያደረገህ ሁኔታ የትኛው ነው?
․․․․․
ምናልባትም ትምህርትህን ለማቋረጥ ወስነህ ይሆናል። ይሁንና ትምህርትህን ለማቋረጥ የወሰንከው በቂ ትምህርት እንዳገኘህ ስለሚሰማህ ይሁን ወይም ትምህርት ስለሰለቸህ እንዴት ማወቅ ትችላለህ? በመጀመሪያ ትምህርት ማቋረጥ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት።
መልቀቅ ወይስ ማቋረጥ?
ከትምህርት ቤት በመልቀቅና ትምህርት በማቋረጥ መካከል ያለውን ልዩነት እንዴት ትገልጸዋለህ?
․․․․․
በአንዳንድ አገሮች አንድ ልጅ ከአምስት እስከ ስምንት ለሚሆኑ ዓመታት ተምሮ ሊመረቅ እንደሚችል ታውቃለህ? በሌሎች አገሮች ደግሞ ተማሪዎች ከአሥር እስከ አሥራ ሁለት ዓመት በትምህርት ቤት እንዲቆዩ ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህ አንድ ወጣት እስከ ስንት ዓመቱ ወይም እስከ ስንተኛ
ክፍል መማር እንዳለበት የሚወስን ዓለም አቀፋዊ መሥፈርት ማውጣት አይቻልም።በተጨማሪም አንዳንድ አገሮች ወይም ክፍላተ አገራት አንድ ተማሪ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት ሳይሄድ አንዳንዶቹን ወይም ሁሉንም የትምህርት ዓይነቶች በቤቱ ሆኖ እንዲማር ይፈቅዱለታል። በወላጆቻቸው ፈቃድና ትብብር በቤታቸው ሆነው የሚማሩ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አቋርጠዋል ሊባል አይችልም።
ይሁን እንጂ በመደበኛ ትምህርት ቤትም ይሁን በቤትህ የምትከታተለውን ትምህርት ከመጨረስህ በፊት ለማቋረጥ እያሰብክ ከሆነ ቀጥሎ የቀረቡትን ጥያቄዎች ልታስብባቸው ይገባል፦
ሕጉ የሚጠይቀው ምንድን ነው? ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው፣ አንድ ተማሪ እስከ ስንተኛ ክፍል መማር እንዳለበት የሚወስኑት ሕጎች ከአገር አገር ይለያያሉ። ታዲያ በአካባቢህ ባለው ሕግ መሠረት ቢያንስ እስከ ስንተኛ ክፍል እንድትማር ይጠበቅብሃል? አንተስ እዚያ ደረጃ ድረስ ተምረሃል? ‘ለበላይ ባለሥልጣናት ተገዙ’ የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ችላ ብለህ ሕጉ የሚጠብቅብህ ክፍል ላይ ሳትደርስ መማር ብታቆም ትምህርትህን አቋርጠሃል ማለት ነው።—ሮም 13:1
በትምህርት የማሳካቸው ግቦች ላይ ደርሻለሁ? በትምህርት ልታሳካቸው የምትፈልጋቸው ግቦች ምንድን ናቸው? እርግጠኛ አይደለህም? ግብህን ማወቅ አለብህ! አለበለዚያ የት መሄድ እንደሚፈልግ ሳያውቅ ባቡር ላይ እንደተሳፈረ መንገደኛ ነህ ማለት ነው። ስለዚህ ከወላጆችህ ጋር ቁጭ በልና ገጽ 28 ላይ የሚገኘውን “በትምህርት የማሳካቸው ግቦች” የሚለውን የመልመጃ ሣጥን ሙላ። እንዲህ ማድረግህ በግቦችህ ላይ እንድታነጣጥር የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ አንተም ሆንክ ወላጆችህ እስከ ስንተኛ ክፍል መማር እንዳለብህ እንድትወስኑ ያስችላችኋል።—ምሳሌ 21:5
አስተማሪዎችህና ሌሎች ሰዎች እስከ ስንተኛ ክፍል ብትማር ጥሩ እንደሚሆን ምክር እንደሚሰጡህ ጥርጥር የለውም። ይሁንና የመጨረሻውን ውሳኔ የማድረግ ሥልጣን ያላቸው ወላጆችህ ናቸው። (ምሳሌ 1:8፤ ቆላስይስ 3:20) አንተም ሆንክ ወላጆችህ በትምህርትህ እንድታሳካ በወሰናችሁት ግብ ላይ ሳትደርስ መማር ብታቆም ትምህርትህን አቋረጥክ ማለት ነው።
ለማቋረጥ ያነሳሳኝ ምንድን ነው? ራስህን እንዳታሞኝ ተጠንቀቅ። (ኤርምያስ 17:9) ሰዎች ስንባል ተገቢ ያልሆነ እርምጃ ለመውሰድ ሰበብ ማቅረብ ይቀናናል።—ያዕቆብ 1:22
ትምህርትህን ከመጨረስህ በፊት ለማቋረጥ በቂ ናቸው የምትላቸውን ምክንያቶች ጻፍ።
․․․․․
አሁን ደግሞ ሰበብ ሊሆኑ የሚችሉ ምክንያቶችን ጻፍ።
․․․․․
በቂ ናቸው ያልካቸው ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው? እየሠራህ ወላጆችህን በገንዘብ ለመደገፍ ወይም በፈቃደኝነት አገልግሎት ለመሳተፍ አስበህ ይሆን? ሰበቦቹ ደግሞ ፈተናዎችን መሸሽ ወይም የቤት ሥራ ከመሥራት መገላገል ሊሆኑ ይችላሉ። አሁን ተፈታታኙ ጉዳይ ‘ትምህርትህን ለማቋረጥ በዋነኝነት ያነሳሳህ ነገር በእርግጥ በቂ ምክንያት ሊሆን ይችላል ወይስ ሰበብ ነው’ የሚለውን ለይቶ ማወቁ ነው።
አሁን እንደገና የጻፍካቸውን ነገሮች ተመልከትና ትምህርት ለማቋረጥ የምትፈልግባቸውን ምክንያቶች በሐቀኝነት ከ1 እስከ 5 ቁጥር ስጣቸው። (እምብዛም አስፈላጊ
ላልሆነው 1 በጣም አስፈላጊ ለሆነው ደግሞ 5 ስጥ።) ከችግሮች ለመሸሽ ብለህ ትምህርት ብታቋርጥ ወደፊት ለእፍረት ሊዳርግህ ይቻላል።ማቋረጥ ምን ችግር አለው?
ትምህርት ማቋረጥ፣ ያሰብክበት ቦታ ከመድረስህ በፊት ከባቡር ላይ ዘለህ እንደመውረድ ሊቆጠር ይችላል። ባቡሩም ሆነ ተሳፋሪዎቹ ላይመቹህ ይችላሉ። ያም ሆኖ ከባቡሩ ላይ ዘለህ ብትወርድ ያሰብክበት ቦታ ሳትደርስ የምትቀር ከመሆኑም ሌላ ከባድ ጉዳት ሊደርስብህ ይችላል። በተመሳሳይም ትምህርትህን ብታቋርጥ በትምህርት ልታሳካቸው ባሰብካቸው ግቦች ላይ የማትደርስ ከመሆኑም በላይ አሁንም ሆነ ለዘለቄታው በራስህ ላይ ችግር ልታመጣ ትችላለህ፤ ከእነዚህም ጥቂቶቹ ከዚህ በታች ሰፍረዋል፦
አሁን የሚያጋጥሙ ችግሮች፦ መጀመሪያውኑም ሥራ ማግኘት ከባድ ሊሆንብህ ይችላል፤ ሥራ ብታገኝ እንኳ ደሞዝህ ትምህርትህን ብትጨርስ ኖሮ ልታገኘው ከምትችለው ክፍያ ያነሰ የመሆን አጋጣሚው ሰፊ ነው። መሠረታዊ ፍላጎቶችህን ለማሟላት በምትጥርበት ጊዜ ደግሞ ተማሪ እያለህ ከነበርክበት በከፋ ሁኔታ ለረጅም ሰዓት መሥራት ይጠበቅብህ ይሆናል።
ዘላቂ ችግሮች፦ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ትምህርት አቋርጠው የወጡ ሰዎች ጤና የማጣት፣ በለጋ ዕድሜ ልጅ የመውለድና እስር ቤት የመግባት አጋጣሚያቸው ሰፊ ከመሆኑም ሌላ ያለ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ድጋፍ መኖር ሊያቅታቸው ይችላል።
ትምህርት ማጠናቀቅ ከእነዚህ ችግሮች ለመዳን ዋስትና እንደማይሆን ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ትምህርትህን በማቋረጥ ራስህን ለምን ጣጣ ውስጥ ትከታለህ?
ትምህርት አለማቋረጥ ያሉት ጥቅሞች
እርግጥ ነው፣ ፈተና ወድቀህ ከሆነ ወይም በትምህርት ቤት አስቸጋሪ ሁኔታ ካጋጠመህ ትምህርትህን ለማቋረጥ ትነሳሳ ይሆናል፤ አሁን ባለህበት ሁኔታ ከመማረርህ የተነሳ ወደፊት ሊያጋጥሙህ የሚችሉ ችግሮች ላይታዩህ ይችላሉ። ይሁን እንጂ “ቀላል ነው” ያልከውን አማራጭ ከመከተልህ በፊት ቀደም ሲል የተጠቀሱት ተማሪዎች ትምህርታቸውን አለማቋረጣቸው እንዴት እንደጠቀማቸው ቀጥሎ የተናገሩትን ሐሳብ ተመልከት።
● “ጽናት ተምሬበታለሁ፤ አስተሳሰቤም ጎልብቷል። በተጨማሪም በማደርገው ነገር ደስታ ማግኘት አለማግኘቴ የተመካው በራሴ ላይ እንደሆነ ተምሬበታለሁ። በትምህርት ቤት መቆየቴ ከተመረቅሁ በኋላ ልጠቀምበት የምችለውን የሥነ ጥበብ ሙያ እንዳሻሽል ረድቶኛል።”—ሪቼል
● “ጠንክሬ ከሠራሁ ግቦቼ ላይ መድረስ እንደምችል አሁን ተረድቻለሁ። በምማርበት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ወደፊት ልሠማራበት ለምፈልገው የኅትመት ማሽን ጥገና ሥራ የሚያዘጋጀኝን የቴክኒክ ሙያ ሥልጠና እየወሰድኩ ነው።”—ጆን
● “ትምህርት ቤት፣ በክፍል ውስጥም ሆነ በሌላ ቦታ የሚያጋጥሙኝን ችግሮች እንዴት መፍታት እንደምችል አስተምሮኛል። ከትምህርት፣ ከማኅበራዊ ሕይወትና ከሌሎች ነገሮች ጋር የተያያዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙኝ እንዴት መፍታት እንደምችል ትምህርት ማግኘቴ በእርግጥም ብስለት እንዳገኝ ረድቶኛል።”—ሲንዲ
● “ትምህርት ቤት በሥራ ቦታ ለሚያጋጥሙኝ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድዘጋጅ ረድቶኛል። በተጨማሪም በትምህርት ቤት የይሖዋ ምሥክር የሆንኩበትን ምክንያት እንድመረምር የሚያነሳሱኝ በርካታ ሁኔታዎች ገጥመውኝ ስለነበር በዚያ የነበረኝ ቆይታ እምነቴን አጠናክሮልኛል።”—ሮዝ
ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን “የአንድ ነገር ፍጻሜ ከጅማሬው ይሻላል፤ ትዕግሥተኛም ከትዕቢተኛ ይሻላል” በማለት ጽፏል። (መክብብ 7:8) በመሆኑም ትምህርትህን ከምታቋርጥ ይልቅ በዚያ የሚያጋጥሙህን ችግሮች በትዕግሥት ለመጋፈጥ ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግህ ፍጻሜህ ያማረ ይሆናል።
www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚለው አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
● በትምህርት ልታሳካቸው የምትችላቸው የአጭር ጊዜ ግቦችን ማውጣትህ በዚያ የምታሳልፈውን ጊዜ በሚገባ እንድትጠቀምበት ሊረዳህ የሚችለው እንዴት ነው?
● ትምህርትህን ከጨረስክ በኋላ ምን ዓይነት ሥራ መሥራት እንደምትፈልግ አስቀድመህ ማሰብህ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
እኩዮችህ ምን ይላሉ?
“የማንበብ ፍቅር እንዲኖረኝ ያደረገኝ ትምህርት ቤት ነው። በንባብ አማካኝነት የሌላን ሰው ሐሳብና ስሜት መረዳት መቻል የሚያስደስት ነገር ነው።”
“በጊዜ አጠቃቀም ረገድ ችግር አለብኝ። ትምህርት ቤት የማልሄድ ቢሆን ኖሮ ይብስብኝ ነበር! ትምህርት ቤት የዕለት ተዕለት ልማዴን ጠብቄ እንድኖር፣ በፕሮግራም የምመራ ሰው እንድሆንና አስፈላጊ ነገሮችን የማከናወን ልማድ እንዲኖረኝ ይረዳኛል።”
[ሥዕሎች]
ኤስሜ
ክሪስቶፈር
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በትምህርት የማሳካቸው ግቦች
የትምህርት ዋና ዓላማ ራስህንም ሆነ ወደፊት የምትመሠርተውን ቤተሰብ ለማስተዳደር የሚያስችልህን ሥራ እንድታገኝ አንተን ማሠልጠን ነው። (2 ተሰሎንቄ 3:10, 12) መሥራት የምትፈልገውን የሥራ ዓይነት ወስነሃል? ታዲያ በትምህርት ቤት የምታሳልፈው ጊዜ ለሥራው ሊያዘጋጅህ የሚችለው እንዴት እንደሆነ አስበሃል? እየተከታተልክ ያለኸው ትምህርት ወደምትፈልገው ግብ እየመራህ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ፦
ምን ተሰጥኦ አለኝ? (ለምሳሌ ያህል፣ ከሰዎች ጋር የመግባባት ችሎታ አለህ? እንደ ፈጠራ ወይም ጥገና ያለ የእጅ ሙያ ማከናወን ያስደስትሃል? አንድን ችግር ተረድቶ መፍትሔ በማግኘት ረገድ ጎበዝ ነህ?)
․․․․․
ካሉኝ ችሎታዎች ጋር አብረው ሊሄዱ የሚችሉት ሥራዎች የትኞቹ ናቸው?
․․․․․
በምኖርበት አካባቢ ክፍት የሆኑት የሥራ ዕድሎች የትኞቹ ናቸው?
․․․․․
ወደፊት ሥራ ሊያስገኝልኝ የሚችል ምን ትምህርት እየተከታተልኩ ነው?
․․․․․
ግቦቼ ላይ በተሳካ ሁኔታ ለመድረስ የሚረዱኝና አሁን ልከታተላቸው የምችላቸው ምን አማራጭ ትምህርቶች አሉ?
․․․․․
ግብህ ወደፊት በሥራ ዓለም ሊጠቅምህ የሚችል ትምህርት ተከታትሎ መመረቅ እንደሆነ አስታውስ። በመሆኑም “ከባቡሩ” መውረድ እንደማይፈልግ ተሳፋሪ አንተም ትልቅ ሰው መሆን ከሚያስከትለው ኃላፊነት ለመሸሽ ስትል ወደሌላው ጽንፍ በመሄድ ዘላለም ተማሪ እንዳትሆን ተጠንቀቅ።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለወላጆች የቀረበ ሐሳብ
“አስተማሪዎቼ አሰልቺዎች ናቸው!” “የቤት ሥራ በጣም ይበዛብኛል!” “የማለፊያ ውጤት ማግኘት እንኳ አስቸጋሪ ሆኖብኛል፤ ታዲያ ምን አደከመኝ?” አንዳንድ ወጣቶች እንደነዚህ ያሉ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች ሲያጋጥሟቸው መተዳደሪያ ለማግኘት የሚያበቃቸውን ችሎታ ከማዳበራቸው በፊት ትምህርታቸውን ለማቋረጥ ይገፋፋሉ። ልጆቻችሁ ትምህርት ማቋረጥ ቢፈልጉ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
እናንተ ራሳችሁ ለትምህርት ያላችሁን አመለካከት መርምሩ። በትምህርት ቤት ያሳለፋችሁት ጊዜ እንደባከነ ይሰማችኋል? የምትፈልጉት ግብ ላይ እስክትደርሱ ድረስ የግድ ልታልፉት እንደሚገባ ‘የእስራት ዘመን’ አድርጋችሁ ትመለከቱት ነበር? ከሆነ እናንተ ለትምህርት ያላችሁ አመለካከት ወደ ልጆቻችሁም ሊጋባ ይችላል። እውነታው ግን ይህ ነው፦ ልጆቻችሁ ሁለገብ የሆነ ትምህርት ማግኘታቸው ወደፊት ትልቅ ሰው ሲሆኑ ስኬታማ ለመሆን የሚያስፈልጓቸውን ባሕርያት ማለትም “ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን” እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል።—ምሳሌ 3:21 NW
የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አቅርቡ። የተሻለ ውጤት ማምጣት የሚችሉ አንዳንድ ልጆች፣ እንዴት እንደሚጠና ስለማያውቁ ወይም ደግሞ ለማጥናት የሚረዳ ምቹ ቦታ ስለማያገኙ ብቻ ውጤታቸው ዝቅተኛ ይሆናል። የማጥኛው ጠረጴዛ ያልተዝረከረከ ከሆነ በክፍሉ ውስጥ በቂ ብርሃን ካለ እንዲሁም ለምርምር የሚረዱ መሣሪያዎች ከተሟሉ ቦታው ለማጥናት ምቹ ይሆናል። ልጆቻችሁ አዳዲስ በሆኑ አስተሳሰቦችና ሐሳቦች ላይ እንዲያሰላስሉ የሚያስችላቸው ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግና ምቹ ቦታ በማዘጋጀት በቀለምም ሆነ በመንፈሳዊ ትምህርታቸው እድገት እንዲያደርጉ መርዳት ትችላላችሁ።—1 ጢሞቴዎስ 4:15
በማሠልጠኑ ሂደት ተካፈሉ። አስተማሪዎችንና የትምህርት ቤት አማካሪዎችን እንደ ጠላት ሳይሆን አንደ አጋሮቻችሁ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው። ሄዳችሁ አነጋግሯቸው። ስማቸውን እወቁ። ልጆቻችሁ ስላሏቸው ግቦችና ስለሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለአስተማሪዎቻቸው አጫውቷቸው። ልጆቻችሁ ዝቅተኛ ውጤት የሚያመጡ ከሆነ የችግሩ መንስኤ ምን እንደሆነ ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ለምሳሌ ያህል፣ ልጆቻችሁ በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ቢያመጡ የጉልበተኞች የጥቃት ዒላማ እንደሚሆኑ ይሰማቸዋል? ከአስተማሪያቸው ጋር አይስማሙም? ወይስ ትምህርቱን አይወዱትም? ሥርዓተ ትምህርቱ እየከበደ የሚሄደው የልጆቻችሁን ችሎታ ለማሻሻል እንጂ ከልክ በላይ እንዲጨነቁ አይደለም። አሊያም ደግሞ ልጆቻችሁ የዓይን ሕመም ወይም ትምህርት የመቀበል ችግር የመሰለ ያልታወቀ አካላዊ ችግር ይኖርባቸው ይሆን?
ልጆቻችሁን በማሠልጠኑ ሂደት ይበልጥ በተካፈላችሁ መጠን በቀለምም ሆነ በመንፈሳዊ ትምህርታቸው ስኬታማ የመሆናቸው አጋጣሚ እየሰፋ ይሄዳል።—ምሳሌ 22:6
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትምህርት ማቋረጥ፣ ያሰብክበት ቦታ ከመድረስህ በፊት ከባቡር ላይ ዘለህ እንደመውረድ ሊቆጠር ይችላል