የተፈጥሮ ጋዝ—በቤት ውስጥ የምንጠቀምበት የኃይል ምንጭ
የተፈጥሮ ጋዝ—በቤት ውስጥ የምንጠቀምበት የኃይል ምንጭ
በዓለም ላይ ካለው ጠቅላላ የኃይል ፍላጎት ውስጥ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆነው የሚሸፈነው በተፈጥሮ ጋዝ ነው። የተፈጥሮ ጋዝ የሚገኘው ከየት ነው? የተፈጥሮ ጋዝ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ምን መደረግ አለበት? ከዚህ ጋዝ ውስጥ ገና ጥቅም ላይ ያልዋለው ምን ያህሉ ነው?
ብዙ የሳይንስ ሊቃውንት የተፈጥሮ ጋዝ፣ በባሕር ውስጥ የሚገኙ ጥቃቅን ዕፅዋትን ጨምሮ ከእንስሳት ቅሪተ አካላትና ከዕፅዋት ብስባሽ ከረጅም ዘመናት በፊት እንደተሠራ ያምናሉ። በዚህ ጽንሰ ሐሳብ መሠረት ከመሬት በላይ የተከማቸው ደለል የሚያሳድረው ግፊትና ጥልቅ ከሆነው የመሬት ክፍል የሚወጣው ሙቀት፣ ረቂቅ ተሕዋስያን ከሚያሳድሩት ተጽዕኖ ጋር ተዳምረው በረጅም ዘመናት ውስጥ ሕይወት የነበራቸውን ነገሮች ብስባሽ ከቅሪተ አካላት ወደሚገኙ ነዳጆች እንዲለወጥ አድርገውታል፤ ከቅሪተ አካላት ከሚገኙት ነዳጆች መካከል የድንጋይ ከሰል፣ ጋዝና ድፍድፍ ነዳጅ ይገኙበታል። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አብዛኛው ጋዝ በዓለቶች ስንጥቅ ውስጥ የሚገባ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ከፍተኛ የጋዝ ክምችት ይፈጥራል፤ ይህ የጋዝ ክምችት ምንም ነገር በማያሳልፉ ዓለቶች ሥር ይጠራቀማል። በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ብዙ ትሪሊዮን ሜትር ኩብ የሚሆን ጋዝ ተከማችቶ ይገኛል። ታዲያ የጋዝ ክምችቶች ያሉበትን ቦታ ማወቅ የሚቻለው እንዴት ነው?
የተፈጥሮ ጋዝ የሚገኝባቸው ቦታዎች የሚታወቁት እንዴት ነው?
ከርቀት ምስሎችን ለማየት የሚያስችሉ ሳተላይቶች፣ ግሎባል ፖዚሽኒንግ ሲስተም የሚባለው አቅጣጫ ጠቋሚ መሣሪያ፣ የርዕደ መሬት ማሚቶዎችና ኮምፒውተሮች ጋዝ የሚገኝበትን ስፍራ ይበልጥ ትክክለኛ በሆነ መንገድ ለመገመት ይረዳሉ። የርዕደ መሬት ማሚቶ፣ ድምፅ ከመሬት በታች ባሉት ዓለቶች ላይ እንደሚስተጋባ በሚገልጸው መሠረተ ሐሳብ ላይ የተመሠረተ ሲሆን በዚህ መንገድ የሚስተጋባው ድምፅ ከታች ስላለው ነገር ለሳይንስ ሊቃውንቱ ምልክት ይሰጣቸዋል። የሳይንስ ሊቃውንቱ አብዛኛውን ጊዜ ትንንሽ ፈንጂዎችን በማፈንዳት ወይም በልዩ የጭነት መኪኖች ላይ የተገጠሙ ንዝረት የሚፈጥሩ መሣሪያዎችን በመጠቀም ከፍተኛ ድምፅ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። በዚህ መንገድ የሚገኘው የድምፅ ሞገድ የምድር ላይኛው ክፍል ድረስ ዘልቆ ከገባ በኋላ ከታች ባሉት ዓለቶች ላይ ተስተጋብቶ ሲመለስ ተዘጋጅተው ለሚጠብቁት መሣሪያዎች ምልክት ይሰጣል፤ ይህም የሳይንስ ሊቃውንቱ የዓለቶቹን ወርድ፣ ቁመትና ጥልቀት የሚያሳዩ የኮምፒውተር ምስሎችን ለመፍጠር ይረዳቸዋል። እነዚህ ምስሎች ደግሞ የጋዝ ክምችት ያለባቸውን ቦታዎች ሊጠቁሙ ይችላሉ።
ከባሕር በታች ጋዝ የሚገኝበትን ቦታ ለማወቅ ደግሞ የሳይንስ ሊቃውንት የታመቀ አየር፣ እንፋሎት ወይም ውኃ በልዩ ዓይነት
ጠመንጃ ወደ ባሕሩ ውስጥ በመተኮስ የድምፅ ሞገዶችን ይፈጥራሉ። በዚህ መንገድ የሚፈጠረው ኃይለኛ የድምፅ ሞገድ የባሕሩን ወለል ሰንጥቆ ከገባ በኋላ ተስተጋብቶ ወደ ላይ በመመለስ ከመርከቡ ኋላ ከታሰረው ረጅም ገመድ ጋር ተያይዘው ለሚገኙት ሃይድሮፎኖች (ከውኃ በታች ያለውን የድምፅ ሞገድ ለማወቅ የሚረዱ መሣሪያዎች) ምልክት ይሰጣል። ተመራማሪዎቹ እነዚህን ምልክቶች በመጠቀም ከላይ እንደተገለጸው ለምርምር የሚረዱ የኮምፒውተር ምስሎችን ይፈጥራሉ።ጋዙን ለማውጣት የሚወሰነው፣ ያን ያህል ወጪ ሊወጣለት የሚገባ በቂ የጋዝ ክምችት መኖሩ ከተረጋገጠ ነው። በመሆኑም የሥነ ምድር ተመራማሪዎች ምን ያህል የጋዝ ክምችት እንዳለና የግፊቱን መጠን ማረጋገጥ አለባቸው። ግፊቱን በመለኪያ መሣሪያዎች በመጠቀም በትክክል ማወቅ ይቻላል። ምን ያህል የጋዝ ክምችት እንዳለ በትክክል ማወቅ ግን አስቸጋሪ ነው። ይህን ለማወቅ የሚሠራበት አንዱ ዘዴ፣ መጀመሪያ የግፊቱን መጠን መለካት ከዚያም የተወሰነ መጠን ያለው ጋዝ ካወጡ በኋላ እንደገና ግፊቱን መለካት ነው። ግፊቱ መጀመሪያ ከነበረው በትንሹ ብቻ ከወረደ ብዙ የጋዝ ክምችት መኖሩን የሚያመለክት ሲሆን ግፊቱ ከመጀመሪያው መጠን በጣም ከወረደ ደግሞ የጋዝ ክምችቱ አነስተኛ ነው ማለት ነው።
ጋዙን በጥቅም ላይ ለማዋል ማዘጋጀት
የተፈጥሮ ጋዝ ከመሬት ውስጥ ከወጣ በኋላ በቧንቧ ተደርጎ ወደ ነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ይላካል፤ እዚያም እንደ ካርቦን ዳይኦክሳይድ፣ ሃይድሮጂን ሰልፋይድና ሰልፈር ዳይኦክሳይድ ያሉ የማይፈለጉ ኬሚካሎች እንዲሁም ቧንቧዎችን የሚያዝገው የውኃ ትነት ከጋዙ እንዲወገዱ ይደረጋል። ቀጥሎም የተፈጥሮ ጋዙ ተቀጣጣይ ያልሆነው ናይትሮጂን እንዲወገድለትና ጠቃሚ የሆኑት ሂሊየም፣ ቢዩቴን፣ ኤቴንና ፕሮፔን እንዲለዩ ለማድረግ ሲባል በጣም በማቀዝቀዝ ይጣራል። የመጨረሻው ውጤት በዋነኝነት ሜቴን ሲሆን ይህም ቀለምም ሆነ ሽታ የሌለውና ከፍተኛ ተቀጣጣይነት ያለው ጋዝ ነው። ሜቴን ከተፈጥሮ የሚገኝ ስለሆነ የተፈጥሮ ጋዝ ተብሎም ይጠራል።
የተፈጥሮ ጋዝን ለቤት ውስጥ አገልግሎት ጉዳት በማያስከትል መንገድ ለማዘጋጀት አምራቾች ሰልፈር የተቀላቀለበት ኃይለኛ ሽታ ያለው ውሕድ በትንሹ ይጨምሩበታል፤ ይህም ጋዙ ሳይታወቅ እየተነነ ቢሆን ፍንዳታ ከማስከተሉ በፊት አሽትቶ ለማወቅና አደጋ እንዳይፈጠር ለመከላከል ያስችላል። ይሁን እንጂ የተፈጥሮ ጋዝ እንደ ከሰል ድንጋይና ነዳጅ ዘይት ካሉት ከቅሪተ አካላት የሚገኙ ሌሎች ነዳጆች ጋር ሲወዳደር በጣም ንጹሕ ነው።
አንዳንድ ጊዜ የተፈጥሮ ጋዝን ለማጓጓዝ እንዲያመች ሲባል በጣም ቀዝቅዞ ወደ ፈሳሽነት እንዲለወጥ ይደረጋል። ቢዩቴንና ፕሮፔን አብዛኛውን ጊዜ በፈሳሽ መልክ (ኤል ፒ ጂ) የሚዘጋጁ ሲሆን በአንዳንድ አገሮች ለምግብ ማብሰያነት ያገለግላሉ። ኤል ፒ ጂ ብዙውን ጊዜ ለአውቶቡሶች፣ ለእርሻ መኪኖች፣ ለጭነት መኪኖችና ለሌሎች ተሽከርካሪዎች ነዳጅ ሆኖም ያገለግላል። በኬሚካላዊ ምርቶች መስክ ደግሞ ቢዩቴንና ፕሮፔን ፕላስቲኮችን፣ ማሟሚያዎችን፣ ሰው ሠራሽ ክሮችንና ሌሎች የተፈጥሮ ምርቶችንም ለመሥራት ይውላሉ።
አላቂ የኃይል አቅርቦት
እንደ ማንኛውም ከቅሪተ አካላት የሚገኝ ነዳጅ ሁሉ የተፈጥሮ ጋዝም አላቂ ነው። ግምቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ በዓለም ላይ ካለው ሊወጣ የሚችል ጋዝ ውስጥ እስከ አሁን ጥቅም ላይ ያልዋለው 45 በመቶ የሚሆነው ነው። ይህ አኃዝ ትክክል ከሆነ ጥቅም ላይ ያልዋለው የተፈጥሮ ጋዝ አሁን በምንጠቀምበት መጠን ለ60 ዓመታት ያህል ሊቆይ ይችላል። ይሁን እንጂ በብዙ አገሮች የኃይል ፍጆታ እያሻቀበ በመሆኑ ይህ ትንበያ ትክክል ላይሆን ይችላል።
በአንዳንድ አገሮች የሚታየው በርካታ ኢንዱስትሪዎችን የማቋቋም አባዜ የምድር የተፈጥሮ ሀብቶች የማያልቁ እንዲመስለን ሊያደርግ ይችላል። እርግጥ ነው፣ ከኑክሌር የሚገኘው ኃይል እንዲሁም ከፀሐይና ከነፋስ እንደሚገኘው ያሉ ታዳሽ የኃይል ምንጮችም አሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ የኃይል ምንጮች እያደገ የሚሄደውን የኃይል ፍላጎት ማሟላት ይችላሉ? ደግሞስ አካባቢን የማይበክሉና ጉዳት የማያስከትሉ ናቸው? ጊዜ የሚያሳየን ነገር ይሆናል።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የተፈጥሮ ጋዝ ከመሬት ውስጥ ከወጣ በኋላ በቧንቧ ተደርጎ ወደ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ይላካል፤ እዚያም ከተጣራ በኋላ ወደ መኖሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ይላካል
[ሥዕላዊ መግለጫ]
የጋዝ ጉድጓድ
ማጣሪያ
ጋዝ አምራች ኩባንያ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንዝረት የሚፈጥሩ ለየት ያሉ መሣሪያዎች የድምፅ ሞገድ እንዲፈጠር የሚያደርጉ ሲሆን ይህ ሞገድ ተስተጋብቶ ሲመለስ ተዘጋጅተው ለሚጠብቁት መሣሪያዎች ምልክት ይሰጣል
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሥነ ምድር ተመራማሪዎች ከድምፅ ሞገዶች ባገኙት መረጃ በመጠቀም የዓለቶቹን ወርድ፣ ቁመትና ጥልቀት የሚያሳዩ የኮምፒውተር ምስሎችን ያዘጋጃሉ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Top: © Lloyd Sutton/Alamy; bottom: © Chris Pearsall/Alamy