የዦ ክረስፐ መጽሐፈ ሰማዕታት
የዦ ክረስፐ መጽሐፈ ሰማዕታት
በ1546 በሜዮ፣ ፈረንሳይ የሚኖሩ 14 ሰዎች በመናፍቅነት ተወንጅለው ከነሕይወታቸው እንዲቃጠሉ ተበየነባቸው። እነዚህ ሰዎች የፈጸሙት ወንጀል ምን ነበር? በግለሰቦች ቤት ይሰበሰቡ፣ ይጸልዩ፣ መዝሙራትን ይዘምሩ፣ የጌታን ራት ያከብሩ እንዲሁም “የጳጳሳቱን ጣዖታት” ፈጽሞ እንደማይቀበሉ ይናገሩ ነበር።
የሮም ካቶሊክ መምህር የነበሩት ፍራንስዋ ፒካር እነዚህ ሰዎች በሚገደሉበት ቀን፣ ስለ ጌታ ራት የነበራቸው እምነት ትክክል እንዳልሆነ ተከራክረዋቸው ነበር። የተፈረደባቸው ሰዎችም በምላሹ ምስጢረ ቁርባን ስለሚባለው የካቶሊክ ትምህርት ፒካርን ጠየቋቸው፤ በዚህ መሠረተ ትምህርት መሠረት ሥርዓተ ቁርባን በሚከናወንበት ጊዜ ቂጣውና ወይኑ በተአምራዊ ሁኔታ ወደ ኢየሱስ ሥጋና ደም እንደሚለወጥ ይታመናል። የተፈረደባቸው ሰዎች ‘ቂጣው የሥጋ ጣዕም አለው? ወይኑስ ደም ደም ይላል?’ ብለው ጠየቋቸው።
እነዚህ ሰዎች ለፒካር የሰጧቸው መልስ አፍ የሚያስይዝ ቢሆንም 14ቱም እንጨት ላይ ታስረው ከነሕይወታቸው መቃጠላቸው አልቀረም። ከመካከላቸው ምላሳቸው ያልተቆረጠባቸው ሰዎች መዝሙር ይዘምሩ ነበር። ግድያው በተከናወነበት ቦታ የነበሩት ቀሳውስት የእነዚህን ሰዎች ድምፅ ለመዋጥ ሲሉ ከእነሱ በላይ ጮክ ብለው ለመዘመር ሞከሩ። በማግሥቱ ፒካር 14ቱ ሰዎች በተገደሉበት ቦታ ላይ ቆመው እነዚህ ሰዎች ለዘላለም ወደሚሠቃዩበት ወደ ሲኦል እንደተወረወሩ ተናገሩ።
በ1500ዎቹ ዓመታት ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የማይስማሙበት ነገር እንዳለ ለሚገልጹ ሰዎች አውሮፓ በጣም አደገኛ ቦታ ነበረች። ተቀባይነት ባገኘው የቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርት ላይ ጥያቄ ያነሱ ብዙ ሰዎች በተቃዋሚዎቻቸው ይህ ነው የማይባል ግፍ ተፈጽሞባቸዋል። በዚያን ጊዜ ስለተፈጸመው ግፍ ከሚገልጹ የመረጃ ምንጮች አንዱ በ1554 በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ የታተመው ለ ሊቭረ ዴ ማርቲር (መጽሐፈ ሰማዕታት) የተባለው የዦ ክረስፐ መጽሐፍ ነው። ይህ መጽሐፍ ኢስትዋ ዴ ማርቲር በመባልም ይታወቃል። *
አንድ የሕግ ባለሙያ የተሃድሶውን እንቅስቃሴ ተቀላቀለ
በአሁኑ ጊዜ በሰሜን ፈረንሳይ በምትገኘው በአራ ከተማ በ1520 የተወለደው ክረስፐ በሉቨ፣ ቤልጅየም ሕግ አጠና። ክረስፐ የተሃድሶውን ንቅናቄ ለመጀመሪያ ጊዜ ያወቀው በቤልጅየም ሳይሆን አይቀርም። በ1541 ይህ ወጣት የአንድ እውቅ የሕግ ባለሙያ ፀሐፊ ሆኖ ለመሥራት ወደ ፓሪስ ሄደ። በዚሁ ጊዜ አካባቢ ክሎድ ለ ፔንክረ የተባለ ሰው መናፍቅ ነው በሚል ተወንጅሎ በፕላስ ሞቤር፣ ፓሪስ ሲቃጠል ተመለከተ። ክረስፐ፣ ወርቅ አንጥረኛ የሆነው የዚህ ወጣት እምነት ልቡን በእጅጉ ነካው፤ እንደ ክረስፐ አባባል ከሆነ ይህ ወጣት የተገደለው “ለወላጆቹና ለወዳጆቹ እውነትን በማሳወቁ ምክንያት” ነበር።
በዚሁ ጊዜ አካባቢ ክረስፐ በአራ ከተማ በሕግ ሙያ ተሠማራ። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ በአዲሱ እምነቱ ምክንያት በመናፍቅነት ተወነጀለ። ለፍርድ ከመቅረቡ በፊት ወደ ስትራስቡርግ፣ ፈረንሳይ የሸሸ ሲሆን ቆየት ብሎም በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ መኖር ጀመረ። በዚያም ከተሃድሶው እንቅስቃሴ ደጋፊዎች ጋር ለመገናኘት ቻለ። ከጊዜ በኋላ ክረስፐ የሕግ ሙያውን ትቶ አታሚ ሆነ።
ክረስፐ እንደ ጆን ካልቪን፣ ማርቲን ሉተር፣ ጆን ኖክስ እና ቴኦዶር ቤዘ ያሉትን የተሃድሶ አራማጆች ሃይማኖታዊ ጽሑፎች አትሟል። በተለምዶ አዲስ ኪዳን የሚባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በግሪክኛ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን በሙሉ ወይም በከፊል በላቲን፣ በስፓንኛ፣ በእንግሊዝኛ፣ በጣሊያንኛና በፈረንሳይኛ አትሟል። ይሁንና ክረስፐ ዝነኛ የሆነው መጽሐፈ ሰማዕታት በተባለው መጽሐፉ ነው። በዚህ መጽሐፉ ውስጥ ከ1415 እስከ 1554 ባሉት ዓመታት ውስጥ በመናፍቅነት ተወንጅለው የተገደሉ በርካታ ሰዎችን ዘርዝሯል።
የሰማዕታትን ታሪክ መጻፍ ለምን አስፈለገ?
የተሃድሶ አራማጆች ከጻፏቸው ጽሑፎች ብዙዎቹ የካቶሊክ ባለሥልጣናትን የጭካኔ ድርጊት የሚያወግዙ ናቸው። እነዚህ ጽሑፎች፣ የፕሮቴስታንት ሰማዕታት “በጀግንነት” የተወጡት መከራ በአንደኛው መቶ ዘመን የኖሩትን ክርስቲያኖች ጨምሮ በጥንቶቹ የአምላክ አገልጋዮች ላይ ከደረሰው ግፍ የቀጠለ እንደሆነ አድርገው በማቅረብ ሕዝቡን ያበረታታሉ። ክረስፐ፣ ፕሮቴስታንት የሆኑ የእምነት ባልንጀሮቹ እንደ አርዓያ ሊመለከቷቸው የሚገቡ ግለሰቦችን መጥቀስ ስለፈለገ በእምነታቸው ምክንያት የተገደሉ ሰዎችን ስም ዝርዝር አዘጋጅቷል። *
የክረስፐ መጽሐፍ የፍርድ መዝገቦችን፣ የምርመራ ሂደቶችን፣ የዓይን ምሥክሮችን ቃል እንዲሁም ተከሳሾቹ በእስር ቤት ሳሉ የጻፏቸውን ሐሳቦች ያካተተ ነው። በተጨማሪም በእስር ላይ ያሉ ግለሰቦችን ለማበረታታት የተጻፉ ደብዳቤዎችን አካትቷል፤ ከእነዚህ ደብዳቤዎች አንዳንዶቹ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን የያዙ ናቸው። ክረስፐ፣ የጸሐፊዎቹ እምነት “ለዝንተ ዓለም ሊታወስ የሚገባው” እንደሆነ ያምን ነበር።
በክረስፐ መጽሐፍ ውስጥ ከሰፈሩት ከመሠረተ ትምህርት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች አብዛኞቹ ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች በሚወዛገቡባቸው የተለመዱ ርዕሶች ላይ ያተኮሩ ናቸው። ከእነዚህም መካከል ምስሎችን ለአምልኮ መጠቀም፣ መንጽሔ፣ ፍታት እንዲሁም በካቶሊክ ሥርዓተ ቅዳሴ ላይ የኢየሱስ መሥዋዕት የሚደገም መሆን አለመሆኑና ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የአምላክ ወኪል የመሆናቸው ጉዳይ ይገኙበታል።
መጽሐፈ ሰማዕታት በጥላቻና በጭካኔ በተሞላው በዚያ ዘመን ለነበረው ግጭትና አለመቻቻል ምሥክር ነው። ክረስፐ ያተኮረው ካቶሊኮች በፕሮቴስታንቶች ላይ ያደርሱ በነበረው ስደት ላይ ቢሆንም ፕሮቴስታንቶቹም ከካቶሊኮቹ ባላነሰ ጭካኔ ካቶሊኮችን ያሳደዱባቸው ጊዜያት እንደነበሩ መዘንጋት የለበትም።
በታሪክ ዘመናት በሙሉ የሐሰት ሃይማኖት ‘በነቢያት፣ በቅዱሳንና በምድር ላይ በታረዱ ሰዎች ሁሉ ደም’ ተጨማልቃለች። አምላክ ለእሱ ታማኝ የሆኑ ሰማዕታት እንደሆኑ አድርጎ የሚቆጥራቸው ግለሰቦች ደም፣ የበቀል እርምጃ እንዲወሰድ እንደሚጮኽ ጥርጥር የለውም። (ራእይ 6:9, 10፤ 18:24) በዦ ክረስፐ ዘመን ለእምነታቸው ሲሉ የመከራና የሞት ጽዋ ከተጎነጩት ሰዎች አንዳንዶቹ ሃይማኖታዊ እውነትን ለማግኘት ከልባቸው ይጥሩ የነበረ ይመስላል።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.5 የክረስፐ መጽሐፍ ሲተረጎም ከተሰጡት ርዕሶች መካከል አንዱ መጽሐፈ ሰማዕታት ማለትም ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተገደሉ በርካታ ሰማዕታት ስብስብ፣ ከያን ሁስ እስከዚህ ዓመት፣ 1554 የሚል ነው። የተለያየ ርዕስና ይዘት ያላቸው የታረሙና የተጨመረባቸው ሌሎች በርካታ እትሞች ክረስፐ በሕይወት በኖረበት ዘመንና ከሞተ በኋላ ታትመዋል።
^ አን.11 ክረስፐ መጽሐፈ ሰማዕታትን ባተመበት ዓመት ይኸውም በ1554 የሰማዕታትን ታሪክ የሚዘግቡ ሌሎች ሁለት መጻሕፍት የታተሙ ሲሆን እነዚህም ሉትቪክ ራቡስ በጀርመንኛ እንዲሁም ጆን ፎክስ በላቲን ቋንቋ ያሳተሟቸው መጻሕፍት ናቸው።
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የክረስፐ “መጽሐፈ ሰማዕታት” የፊት ገጽ (የ1564 እትም)
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፕሮቴስታንቶች በፈረንሳዊው ንጉሥ ዳግማዊ ሄንሪና በችሎቱ ፊት ሲገደሉ
[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Images, both pages: © Société de l’Histoire du Protestantisme Français, Paris