አስደናቂ የወረቀት ከተማ
አስደናቂ የወረቀት ከተማ
‘የወረቀት ከተማ?’ አዎ፣ በወረቀት የተሠራ ከተማ አለ። ይሁንና እውነተኛ ከተማ ሳይሆን የከተማ ሞዴል ነው። ሞዴሉ የቼክ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ የሆነው የፕራግ ሲሆን የሚገኘውም በፕራግ የማዘጋጃ ቤት ቤተ መዘክር ውስጥ ነው። ሞዴሉን የሠራው ሰው አንቶኒን ላንግቫይል ይባላል፤ ይህን ሞዴል ለመሥራት ከ1826 ጀምሮ እስከሞተበት ዓመት ይኸውም እስከ 1837 ድረስ 11 ዓመት ፈጅቶበታል። ላንግቫይል እንዲህ ያለውን አስቸጋሪ ሥራ እንዲጀምር ያነሳሳው ምን ነበር?
ላንግቫይል የተወለደው በአሁኑ ጊዜ ቼክ ሪፑብሊክ በምትባለው አገር ውስጥ ባለች ፖስቶሎፕርቲ በተባለች ከተማ በ1791 ነበር። በቪየና፣ ኦስትሪያ በሚገኘው የቪየና የሥነ ጥበብ ተቋም የኅትመት ሙያ ከተማረ በኋላ በፕራግ የመጀመሪያውን ማተሚያ ቤት ከፈተ። ይሁን እንጂ ላንግቫይል በንግዱ ዓለም ያን ያህል ውጤታማ ስላልነበረ ድርጅቱ ከስሮ ተዘጋ። ላንግቫይል በ1826 በፕራግ አንድ ኤግዚቢሽን ሲጎበኝ የፈረንሣይ ከተማ የሆነችውን የፓሪስን ሞዴል ተመለከተ፤ ሞዴሉ በጀሶ የተሠራ ነበር። የተመለከተው ነገር በካርቶንና በትናንሽ እንጨቶች በመጠቀም የፕራግን ሞዴል ለመሥራት አነሳሳው።
በመጀመሪያ ግን ላንግቫይል የፕራግን ከተማ ዝርዝር ገጽታ በጥንቃቄ ሲመዘግብ በርካታ ዓመታት አሳለፈ። በእያንዳንዱ ጎዳና በእግሩ እየተዘዋወረ ሕንፃዎች፣ የመናፈሻ መቀመጫዎች፣ የዕቃ ማስቀመጫ ቤቶች፣ ሐውልቶችና ዛፎች ያሉበትን ቦታ በወረቀት ላይ አሰፈረ። የተሰበሩ መስኮቶችን፣ ግድግዳ ላይ የተደገፈ መሰላልን፣ የእንጨት ክምርንና መሬት ላይ ያያቸውን በርሜሎች ሳይቀር በንድፉ ውስጥ አካትቷል። ከዚያም 1:480 በሆነ ስኬል ሞዴሉን መሥራት ጀመረ። ኑሮው ከእጅ ወዳፍ ስለነበር ተጨማሪ
ገቢ ለማግኘት የመኳንንቶችን ቤቶች ሞዴልም ይሠራ ነበር።ላንግቫይል በ1837 በሳንባ ነቀርሳ በሽታ ታመመ፤ በዚያው ዓመት በሰኔ ወር ሚስቱንና አምስት ሴት ልጆቹን ትቶ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። ከሦስት ዓመት በኋላም እሱ የሠራው ሞዴል በአሁኑ ጊዜ ብሔራዊ ቤተ መዘክር እየተባለ በሚጠራው የአርበኞች ቤተ መዘክር ውስጥ ተቀመጠ። እንዴት እዚያ ሊገባ ቻለ? በ1840 የላንግቫይል ሚስት ሞዴሉን እንዲገዟት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ፈርድናንድን ጠየቀቻቸው፤ እሳቸውም ሞዴሉን ከገዙ በኋላ አሁን የቼክ ሪፑብሊክ ብሔራዊ ቤተ መዘክር ለሆነው ተቋም በስጦታ አበረከቱት። ሞዴሉ የተጓጓዘው በዘጠኝ ሣጥኖች ተጭኖ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ሞዴሉ የሚገኝበት የፕራግ ከተማ ቤተ መዘክር ቃል አቀባይ እንዲህ ብለዋል፦ “የላንግቫይል ሞዴል በ19ኛው መቶ ዘመን ለእይታ ይቀርብ የነበረው አልፎ አልፎ ብቻ ነበር። በ1891 በብሔራዊው የኢዩቤልዩ ኤግዚቢሽን ላይ ቀርቦ ነበር። ሞዴሉን በዚህ ኤግዚቢሽን ላይ ለማቅረብ ከፍተኛ ወጪ የጠየቀ ጥገና ተደረገለት። . . . ከ1905 ወዲህ ይህ ሞዴል በብሔራዊው ቤተ መዘክር ውስጥ ቋሚ መቀመጫ አግኝቷል።”
ለታሪክ ምሁራን መስህብ
የላንግቫይል የወረቀት ሞዴል ከፍተኛ ተወዳጅነት አትርፏል። ሞዴሉ 5.76 ሜትር በ3.24 ሜትር ሲሆን በመስታወት ሣጥን ውስጥ ተቀምጧል፤ በሣጥኑ ውስጥ የተንጠለጠሉት በርካታ ትናንሽ መብራቶች ለሞዴሉ ውበት ሰጥተውታል። ይህ ሞዴል እውነተኛ ከተማ ስለሚመስል ሞዴል እየጎበኘህ እንዳለህ እንኳ ልትዘነጋ ትችላለህ! በእርግጥም ላንግቫይል ሞዴሉ ላይ ያሉትን ከሁለት ሺህ የሚበልጡ ትናንሽ ሕንፃዎች የሠራቸው እጅግ ተጨንቆና ተጠብቦ በመሆኑ ከእውነተኛው ከተማ ጋር በጣም ይመሳሰላሉ።
ለምሳሌ ላንግቫይል ለሕንፃዎቹ ቁጥር ሰጥቷቸው ነበር። የመንገድ መብራቶችን፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችንና የመንገዶቹን የድንጋይ ንጣፍ በሞዴሉ ውስጥ አካትቷል። የተለያዩ ቀለማት ባሏቸው መስታወቶች የተሠሩ የአብያተ ክርስቲያናት መስኮቶችን ሌላው ቀርቶ መስታወት የሌላቸውንና መስታወታቸው የተሰበረውን እንኳ ሳያስቀር በትክክል ሠርቷል። ልስናቸው የረገፈ ቤቶችን ከውስጥ ያለው ሸክላ እንዲታይ አድርጎ ሠርቷቸዋል። በተጨማሪም የፕራግን ከተማ አቋርጦ የሚያልፈውን የቨላታቫን ወንዝ በሞዴሉ ላይ አካትቷል።
ዛሬ የላንግቫይል የወረቀት ሞዴል የሰዎችን ትኩረት የሚስብ የቤተ መዘክር ቅርስ ከመሆን አልፎ ፕራግ በጊዜ ሂደት ምን ያህል እንደተለወጠች ማየት የሚፈልጉ የሥነ ጥበብ አፍቃሪዎችንና የታሪክ ምሁራንን ቀልብ የሚስብ ሆኗል። እርግጥ፣ ብዙ አዳዲስ ሕንፃዎች በመሠራታቸውና የድሮዎቹም ተሻሽለው በመታደሳቸው አንዳንዶቹ የከተማይቱ ክፍሎች ሞዴሉን አይመስሉም፤ የአይሁድ ሰፈርና አሮጌው ከተማ ተብሎ የሚጠራው የፕራግ ክፍል ለዚህ ምሳሌ ይሆናሉ። ዕድሜ ለዘመናዊ ቴክኖሎጂ የላንግቫይልን ሞዴል ዛሬ በኮምፒውተር አማካኝነት መመልከት ተችሏል፤ ጎብኚዎች ፕራግ በ1837 ምን ትመስል እንደነበር ለማወቅ ሞዴሉን እንደፈለጉ እያዘዋወሩ በኮምፒውተር መመልከት ይችላሉ።
ላንግቫይል በ1837 በሚያዝያ ወር ታምሞ እያለ ሞዴሉ በጊዜው የአርበኞች ቤተ መዘክር ይባል በነበረው ተቋም ውስጥ እንዲቀመጥለት ጠይቆ ነበር፤ ቤተ መዘክሩ ግን ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። ላንግቫይል እንዲህ ዓይነት ምላሽ ማግኘቱ ምን ያህል አሳዝኖት ይሆን! ዛሬ በሕይወት ቢኖርና በቤተ መዘክር ውስጥ የሚገኘውን የድሮዋን ፕራግ ሞዴል ቢጎበኝ አሊያም ሞዴሉን በኮምፒውተር መስኮት “እየተዘዋወረ” ቢቃኝ ምን ሊሰማው እንደሚችል ገምት። ያ ሁሉ ድካሙና ልፋቱ ከንቱ እንዳልቀረ እንደሚገነዘብ ጥርጥር የለውም።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንቶኒን ላንግቫይል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ላንግቫይል የሠራው የፕራግ ከተማ የወረቀት ሞዴል
[በገጽ 10 እና 11 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የላንግቫይል የወረቀት ሞዴል ከቅርብ ሲታይ
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Page 10, Langweil: S laskavým svolením Národního muzea v Praze; pages 10 and 11, model photos: S laskavým svolením Muzea hlavního mesta Prahy