በኢንተርኔት የሚሰነዘር ጥቃት!
በኢንተርኔት የሚሰነዘር ጥቃት!
የኢንተርኔት ወንጀለኞችን ያቀፈ ሠራዊት በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር፤ የላቀ የኮምፒውተር ችሎታ ያላቸው እነዚህ ወንጀለኞች የጠለፏቸውን በርካታ ኮምፒውተሮች በኢንተርኔት አማካኝነት ለፈለጉት ዓላማ ይጠቀሙባቸዋል። ወንጀለኞቹ የጠለፏቸው ኮምፒውተሮች ቦትኔት (ሮቦት ኔትወርክ) በመባል የሚታወቁ ሲሆን እነዚህም የአንድን አገር ኮምፒውተሮች ከጥቅም ውጪ ሊያደርጉ የሚችሉ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን ያዥጎደጉዳሉ። በደቂቃዎች ውስጥ የዚህ አገር የውትድርና እንዲሁም ገንዘብ ነክና የንግድ ተቋማት የሚጠቀሙባቸው ድረ ገጾች አገልግሎት መስጠት ያቆማሉ። የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች (ኤ ቲ ኤም) እና ስልኮች ከአገልግሎት ውጭ ይሆናሉ። የአየር በረራዎች ይስተጓጎላሉ፤ እንዲሁም በኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙ ኮምፒውተሮችና አደጋ ለመከላከል የሚያገለግሉ መሣሪያዎች መሥራት ያቆማሉ። በዚህ ጊዜ የአገሪቱ ሕዝብ ምን ይሰማዋል? ምንስ ያደርጋል? አንተ ብትሆን ምን ታደርጋለህ?
ከላይ የተገለጸው ሁኔታ ፈጽሞ ሊሆን እንደማይችል ይሰማህ ይሆናል። ይሁን እንጂ የዩናይትድ ስቴትስ የደኅንነት፣ የመሠረተ ልማት ጥበቃና የፀረ ሽብርተኝነት ብሔራዊ አስተባባሪ የነበሩት ሪቻርድ ክላርክ እንደተናገሩት ይህን የመሰለ ሁኔታ ሊደርስ ይችላል። እንዲያውም ከአሁን ቀደም እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች ተከስተው ያውቃሉ። * ምናልባት አንተም የዚህ ጥቃት ሰለባ ሆነህ ሊሆን ይችላል።
አንድ ሰው በኢንተርኔት አማካኝነት ጥቃት የሚሰነዝረው ለምን ሊሆን ይችላል? እንዲህ ያሉት ጥቃቶች የሚፈጸሙት እንዴት ነው? እንዲሁም በግለሰቦች ላይ እንዲህ ዓይነት ጥቃት መሰንዘሩ የተለመደ በመሆኑ አንተ ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው?
የኢንተርኔት ጦርነት
ሰዎች በኢንተርኔት አማካኝነት ጥቃት የሚሰነዝሩባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሏቸው። ለምሳሌ አሸባሪዎች ወይም መንግሥታት ወደ ጠላቶቻቸው ኮምፒውተሮች ሰርገው በመግባት ሚስጥራቸውን ለመስረቅ ወይም ኮምፒውተሮቹ የሚቆጣጠሯቸውን የተለያዩ መሣሪያዎች ለማበላሸት ሊሞክሩ ይችላሉ። የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል የመከላከያ ሚኒስቴር የሆኑት ዊልያም ሊን በ2010 እንደተናገሩት የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች ሚስጥራዊ መረጃ በያዙ የመንግሥት ኮምፒውተሮች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት አድርሰዋል፤ እንዲሁም “የጦር መሣሪያ ንድፎችን፣ የውጊያ እቅዶችንና የስለላ መረጃዎችን የያዙ በሺህዎች የሚቆጠሩ ፋይሎችን” ሰርቀዋል።— “በቅርብ የተሰነዘሩ አንዳንድ ጥቃቶች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
የኮምፒውተር ወንጀለኞች ከትላልቅ ድርጅቶችም ሆነ ከግል ኮምፒውተሮች አእምሮአዊ ንብረቶችን ወይም ገንዘብ ነክ መረጃዎችን ለመስረቅ የሚጠቀሙባቸው ዘዴዎች ተመሳሳይ ናቸው። ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ወንጀለኞች በኢንተርኔት አማካኝነት በሚፈጸም ማጭበርበር በየዓመቱ በቢሊዮን የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር ያፍሳሉ።
አጭበርባሪዎች በቁጥጥራቸው ውስጥ ያዋሏቸውን እጅግ በጣም ብዙ ኮምፒውተሮች በኢንተርኔት አማካኝነት ወንጀል
ለመፈጸም ይጠቀሙባቸዋል። ለምሳሌ ኮምፒውተሮችን ከጥቃት የሚጠብቅ ድርጅት በ2009 አንድን የወንጀለኞች ቡድን አጋልጧል፤ ይህ ቡድን ከየትኛውም ቦታ ሆኖ በኢንተርኔት አማካኝነት ሁለት ሚሊዮን ኮምፒውተሮችን የሚቆጣጠር ሲሆን ከእነዚህ ኮምፒውተሮች አብዛኞቹ የግለሰቦች ንብረት ናቸው። የኢኮኖሚያዊ ትብብርና ልማት ድርጅት (ኦ ኢ ሲ ዲ) በቅርቡ ይፋ ያደረገው ግምታዊ መረጃ እንደሚጠቁመው ከኢንተርኔት ጋር ከሚገናኙ ሦስት ኮምፒውተሮች መካከል አንዱን ወንጀለኞች ከፈለጉበት ቦታ ሆነው ይቆጣጠሩታል። የአንተስ ኮምፒውተር? ሳታውቀው ሌላ ሰው እየተቆጣጠረው ይሆን?ድምፅ የለሽ አድቢዎች
የሚከተለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። አንድ ወንጀለኛ ኮምፒውተሮችን ሊጎዳ የሚችል ፕሮግራም በኢንተርኔት አማካኝነት ይልካል። ይህ ፕሮግራም የአንተን ኮምፒውተር ሲያገኝ አንተ ሳታውቀው የቫይረስ መከላከያ ፕሮግራሞችህን መመርመር ይጀምራል። በኮምፒውተርህ የቫይረስ መከላከያ ፕሮግራም ላይ ክፍተት ካገኘ ወደ ኮምፒውተርህ ሰርጎ ይገባና ጠቃሚ መረጃ ለማግኘት ማሰሱን ይያያዘዋል። * ከዚያም ይህ ጎጂ ፕሮግራም ኮምፒውተርህ ውስጥ የሚገኙ ፋይሎችን ይለውጣል ወይም ያጠፋል፣ ራሱን ወደ ሌሎች ኮምፒውተሮች በኢ-ሜይል ይልካል አሊያም የይለፍ ቃሎችን፣ ገንዘብ ነክ መረጃዎችን ወይም ሌሎች ሚስጥራዊ መረጃዎችን ወደ ወንጀለኛው መልሶ ይልካል።
የኮምፒውተር ወንጀለኞች አንተ ራስህ ኮምፒውተርህን የሚያበላሽ ነገር እንድትፈጽም ሊያደርጉህ ይችላሉ! እንዴት? ምንም ጉዳት የሌለው ከሚመስል ኢ-ሜይል ጋር አባሪ ሆኖ የተላከ ፋይል ወይም ወደ ሌላ ድረ ገጽ የሚመራ ሊንክ ከከፈትክ፣ ኢንተርኔት ላይ በነፃ የሚገኙ የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን ኮምፒውተርህ ላይ ከጫንክ፣ በቫይረስ የተበከሉ መረጃ ማስተላለፊያ መሣሪያዎችን (ለምሳሌ ፍላሽ ዲስክ) ኮምፒውተርህ ላይ ከሰካህ ወይም ደግሞ ተገቢ ያልሆኑ ድረ ገጾችን ከከፈትክ ኮምፒውተርህ እንዲበከል ልታደርግ ትችላለህ። ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዱን እንኳ ብታደርግ ጎጂ የሆነ ፕሮግራም ኮምፒውተርህ ላይ ሊጫንና ኮምፒውተርህን የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች እንዲቆጣጠሩት መንገድ ልትከፍት ትችላለህ።
ኮምፒውተርህ ተበክሎ እንደሆነ እንዴት ማወቅ ትችላለህ? ይህን ማወቅ በጣም አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ኮምፒውተርህ ወይም የኢንተርኔት መስመርህ በጣም አዝጋሚ ሊሆኑብህ አሊያም ፕሮግራሞችህ መሥራት ሊያቆሙ ይችላሉ፤ አንዳንድ ፕሮግራሞችን እንድትጭን የሚጠይቁ መልእክቶች ሊመጡብህ አሊያም ደግሞ ኮምፒውተርህ ያልተለመደ ባሕርይ ማሳየት ሊጀምር ይችላል። ከእነዚህ ምልክቶች አንዱን ካስተዋልክ ጥሩ ችሎታ ያለው ባለሙያ ኮምፒውተርህን እንዲያይልህ ማድረግ ይኖርብሃል።
‘እርምጃህን አስተውል’
አገራትም ሆኑ ግለሰቦች በኮምፒውተር የሚጠቀሙበት መጠን እየጨመረ በሄደ ቁጥር በኢንተርኔት የሚሰነዘር ጥቃትም እየተባባሰ መሄዱ አይቀርም። በመሆኑም ብዙ ብሔራት እንዲህ ያለውን ጥቃት ለመከላከል የሚያስችሏቸውን መንገዶች ለማጠናከር አፋጣኝ እርምጃ እየወሰዱ ሲሆን አንዳንዶቹ ደግሞ ኮምፒውተሮቻቸው ጥቃት የመቋቋም አቅማቸው ምን ያህል እንደሆነ ለመፈተን መጠነ ሰፊ ሙከራ እያካሄዱ ነው። እንዲያም ሆኖ በዩናይትድ ስቴትስ የፌዴራል የወንጀል ምርመራ ቢሮ የኮምፒውተር ደኅንነት ባለሙያ የሆኑት ስቲቨን ቻቢንስኪ እንደተናገሩት “ታጥቆ የተነሳ ጠላት፣ በቂ ጊዜና ገንዘብ እስካገኘና ምክንያት እስካለው ድረስ መቼም ቢሆን ዒላማ ወዳደረጋቸው ኮምፒውተሮች ሰርጎ መግባቱ አይቀርም።”
ታዲያ በኢንተርኔት አማካኝነት ከሚፈጸም ጥቃት ራስህን መጠበቅ የምትችለው እንዴት ነው? ኢንተርኔት ስትጠቀም ኮምፒውተርህ በምንም ዓይነት የማይደፈር መከላከያ እንዲኖረው ማድረግ የማይቻል ቢሆንም ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች አሉ። (“ራስህን ጠብቅ!” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።) መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ . . . ርምጃውን ያስተውላል” ይላል። (ምሳሌ 14:15) ይህ ሐሳብ ኢንተርኔት በምትጠቀምበት ጊዜ ልትሠራበት የሚገባ ጠቃሚ ምክር እንደሆነ ጥርጥር የለውም!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.3 በኢንተርኔት የሚሰነዘር ጥቃት (ሳይበርአታክ) ሲባል የኢንተርኔት አገልግሎት ያላቸው ኮምፒውተሮችን ወይም በውስጣቸው የሚገኘውን አሊያም የሚያሰራጩትን መረጃ ወይም ፕሮግራም ለመለወጥ፣ ለማበላሸት አሊያም ለማጥፋት ሆን ተብሎ የሚደረግ ሙከራ ማለት ነው።—የዩናይትድ ስቴትስ ብሔራዊ የምርምር ተቋም
^ አን.10 የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች፣ ኮምፒውተሮች ላይ የሚታዩ ከ45,000 በላይ የሚሆኑ የሚታወቁ ክፍተቶችን እንደሚጠቀሙ በ2011 ሪፖርት ተደርጓል። በእነዚህ ክፍተቶች በመጠቀም በግለሰቦች ኮምፒውተሮች ላይ ባለቤቶቹ ሳያውቁት ጎጂ ሶፍትዌር (ማልዌር) ለመጫን ሙከራ ያደርጋሉ።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የኢንተርኔት አጭበርባሪዎች በቁጥጥራቸው ውስጥ ያዋሏቸውን እጅግ በጣም ብዙ ኮምፒውተሮች ወንጀል ለመፈጸም ይጠቀሙባቸዋል
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ኦ ኢ ሲ ዲ እንደገለጸው ከኢንተርኔት ጋር ከሚገናኙ ሦስት ኮምፒውተሮች መካከል አንዱን ወንጀለኞች ከፈለጉበት ቦታ ሆነው ይቆጣጠሩታል
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በቅርብ የተሰነዘሩ አንዳንድ ጥቃቶች
2003፦ ስላመር የተባለው የኮምፒውተር ዎርም በኢንተርኔት አማካኝነት በከፍተኛ ፍጥነት በመሰራጨት በአሥር ደቂቃ ውስጥ 75,000 ገደማ የሚሆኑ ኮምፒውተሮችን በክሏል። * በዚህ ምክንያት መደበኛ የኢንተርኔት አገልግሎት በጣም አዝጋሚ ሆነ፤ ድረ ገጾች አገልግሎት መስጠት አቆሙ፤ የገንዘብ መክፈያ ማሽኖች (ኤ ቲ ኤም) ከአገልግሎት ውጭ ሆኑ፤ የአየር በረራዎች ተስተጓጎሉ እንዲሁም በአንድ የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ ኮምፒውተሮችና አደጋ ለመከላከል የሚያገለግሉ መሣሪያዎች መሥራት አቆሙ።
2007፦ በኢስቶኒያ የተሰነዘሩት ተከታታይ የኢንተርኔት ጥቃቶች በመንግሥት ተቋማት፣ በመገናኛ ብዙኃንና በባንኮች ላይ ጉዳት አድርሰዋል። አብዛኞቹ ጥቃቶች የተሰነዘሩት በአጭበርባሪዎች ከተጠለፉ ኮምፒውተሮች (ቦትኔት) ነው፤ እነዚህ በ75 አገሮች የሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ኮምፒውተሮች፣ በኢስቶኒያ በሚገኙት ኮምፒውተሮች ላይ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የውሸት መልእክቶችን አዥጎድጉደውባቸዋል።
2010፦ እጅግ ውስብስብ የሆነው ስተክስኔት የተባለ የኮምፒውተር ዎርም በኢራን በሚገኝ የኑክሌር ጣቢያ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.25 የኮምፒውተር ዎርም የሚባሉት ራሳቸውን እያባዙ በኢንተርኔት አማካኝነት ከአንድ ኮምፒውተር ወደ ሌላ ኮምፒውተር የሚዛመቱ ጎጂ ፕሮግራሞች ናቸው። እንደ ሌሎች ጎጂ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ሁሉ የኮምፒውተር ዎርሞችም የራሳቸው ስም (ለምሳሌ ስላመር) ይሰጣቸዋል።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ራስህን ጠብቅ!
1. ኮምፒውተርህ ላይ የቫይረስ መከላከያ ፕሮግራም (አንቲቫይረስ)፣ የግል መረጃህን አሳልፈው የሚሰጡ ፕሮግራሞች መከላከያ (ስፓይዌር ዲቴክሽን) እንዲሁም የኮምፒውተር መከላከያ (ፋየርዎል) ጫን። እነዚህ ፕሮግራሞችም ሆነ ኮምፒውተርህን የሚያሠራው ፕሮግራም ጊዜ ያለፈባቸው አለመሆናቸውን አዘውትረህ አረጋግጥ።
2. ከምታውቃቸው ግለሰቦች የተላኩ ቢሆኑም እንኳ ከኢ-ሜይሎች ጋር አባሪ ሆነው የሚመጡ ፋይሎችን ወይም አጭር መልእክቶችን እንዲሁም ሊንኮችን ከመክፈትህ በፊት ቆም ብለህ አስብ። በተለይ ደግሞ መልእክቶቹ ከማታውቀው ምንጭ የተላኩና የግል መረጃዎችህን እንዲሁም የይለፍ ቃልህን የሚጠይቁ ከሆኑ ተጠንቀቅ።
3. ካልታወቀ ምንጭ የተገኘ ፕሮግራም ኮምፒውተርህ ላይ ኮፒ አታድርግ ወይም አትጫን።
4. ቁጥሮችንና ሥርዓተ ነጥቦችን ያካተተና ቢያንስ ስምንት ፊደላት የያዘ የይለፍ ቃል ተጠቀም፤ እንዲሁም የይለፍ ቃልህን በየጊዜው ለውጥ። ለተለያየ አካውንት የተለያየ የይለፍ ቃል ተጠቀም።
5. በኢንተርኔት አማካኝነት ከገንዘብ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን የምታከናውን ከሆነ አስተማማኝ ድረ ገጽ እንደሚጠቀሙ ከሚታወቁ ኩባንያዎች ጋር ብቻ ተገናኝ። *
6. ለማንም ሰው ክፍት በሆኑ ገመድ አልባ መገናኛዎች (ዋይ-ፋይ) በምትጠቀምበት ጊዜ ስለ ራስህም ሆነ ስለ አካውንትህ ሚስጥራዊ መረጃዎችን አትላላክ።
7. ኮምፒውተርህን በማትጠቀምበት ጊዜ አጥፋው።
8. በኮምፒውተርህ ላይ የሚገኙ ፋይሎችህን በየጊዜው እየገለበጥክ አስተማማኝ ቦታ አስቀምጣቸው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.36 አንድ ድረ ገጽ አስተማማኝ የሚባለው በአድራሻ መጻፊያው ላይ የቁልፍ ምልክት እና “https://” የሚል ጽሑፍ የሚታይ ከሆነ ነው። “s” የሚለው ሆሄ መስመሩ አስተማማኝ (secure) እንደሆነ የሚጠቁም ነው።
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በኢንተርኔት አማካኝነት ጥቃት እንዳይሰነዘርብህ የምትችለውን ሁሉ አድርግ