በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ​—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ፣ ክፍል 2

መጽሐፍ ቅዱስ​—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ፣ ክፍል 2

መጽሐፍ ቅዱስ​—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ፣ ክፍል 2

ከባቢሎን ውጡ!

ከዚህ እትም ጀምሮ በሚወጡ ስምንት ተከታታይ “የንቁ!” እትሞች ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ከሚያደርጉት ገጽታዎች መካከል አንዱ ስለሆነው ማለትም በውስጡ ስለያዘው ትንቢት እንመረምራለን። ይህ ተከታታይ ርዕስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ይረዳሃል፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ያሰፈሯቸው ግምታዊ ሐሳቦች ናቸው? ወይስ እነዚህ ትንቢቶች በአምላክ መንፈስ መሪነት መጻፋቸውን የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ? እስቲ ማስረጃዎቹን አብረን እንመርምር።

በዚህ ተከታታይ ርዕስ የመጀመሪያ ክፍል ላይ የአብርሃም ዘርን አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ ሦስት ትንቢቶችን መርምረናል። አምላክ በእነዚህ ትንቢቶች አማካኝነት የሰጣቸውን ተስፋዎች የአብርሃም ዘር በሆነው በጥንቱ የእስራኤል ብሔር አማካኝነት እንደፈጸማቸው ማስረጃዎቹ ያረጋግጣሉ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ፣ በተለይም በሰባተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ላይ ጉልህ ሚና የተጫወተችው ሌላዋ ብሔር የጥንቷ ባቢሎን ናት። እስቲ ይህችን ግዛት አስመልክቶ የተነገሩ ሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን እንመልከት፤ እንዲሁም እነዚህ ትንቢቶች በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ማስረጃዎቹን እንመርምር።

ነቢዩ ሙሴ የጥንቱን የእስራኤል ብሔር “አምላክህን እግዚአብሔርን ብትረሳና ሌሎችን አማልክት ብትከተል፣ ብታመልክና ለእነርሱ ብትሰግድላቸው በእርግጥ [ትጠፋለህ]” በማለት አስጠንቅቆ ነበር። (ዘዳግም 8:19፤ 11:8, 9) ያም ሆኖ እስራኤላውያን ጣዖታትን በማምለክ በተደጋጋሚ ጊዜያት በአምላክ ላይ ዓመፁ።​—1 ነገሥት 14:22-24

ከጊዜ በኋላ አምላክ፣ ትዕግሥቱ በማለቁ እሱን ለመታዘዝ አሻፈረኝ ያሉትን አገልጋዮቹን በባቢሎናውያን እጅ እንዲወድቁ አደረገ። በንጉሥ ናቡከደነፆር (ናቡከደረፆር ተብሎም ይጠራል) የሚመራው የባቢሎናውያን ሠራዊት በእስራኤል ላይ በመዝመት ኢየሩሳሌምን ከበባት። ለመሆኑ ይህ ከበባ ያን ያህል ትልቅ ቦታ ልንሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው? እስቲ ነቢዩ ኤርምያስ ይህ ከመሆኑ ከ20 ዓመታት ገደማ በፊት የጻፈውን ነገር እንመርምር።​—ኤርምያስ 25:1

ትንቢት 1፦ “[እናንተ እስራኤላውያን] ቃሌን ስላልሰማችሁ፣ . . . የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እጠራለሁ። . . . በዚህች ምድርና በነዋሪዎቿም ላይ፣ . . . [ባቢሎናውያንን] አመጣባቸዋለሁ፤ . . . አገሪቱ በሞላ ባድማና ጠፍ ትሆናለች፤ እነዚህም ሕዝቦች ለባቢሎን ንጉሥ ሰባ ዓመት ይገዛሉ።”​ኤርምያስ 25:8-11

ፍጻሜ፦ ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ለረጅም ጊዜ ከብቦ ከቆየ በኋላ በ607 ዓ.ዓ. አውድሟታል። በተጨማሪም ለኪሶንና ዓዜቃን ጨምሮ ሌሎች የይሁዳን ከተሞች ድል በማድረግ ተቆጣጥሯል። (ኤርምያስ 34:6, 7) ናቡከደነፆር፣ በሕይወት ከተረፉት ሰዎች መካከል አብዛኞቹን በምርኮ ወደ ባቢሎን ወስዷቸዋል፤ በዚያም ለ70 ዓመታት በግዞት ቆይተዋል።

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

● ኢየሩሳሌም በጠፋችበት ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ የነበረው ናቡከደነፆር እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። የአርኪኦሎጂ ማስረጃዎችም ቢሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ናቡከደነፆር የሚባል ንጉሥ ስለመኖሩ የሚናገረውን ሐሳብ ይደግፋሉ። በፍሎረንስ፣ ጣሊያን የናቡከደነፆር ምስል የተቀረጸበት የከበረ ድንጋይ ይገኛል። በዚህ ድንጋይ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ በከፊል “የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር በሕይወት ዘመኑ ለጌታው ለሜሮዳክ ክብር ብሎ ያሠራው” ይላል። ናቡከደነፆር የገዛው ከ624 እስከ 582 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ውስጥ ነው።

ዘ ባይብል ኤንድ አርኪኦሎጂ የተሰኘው መጽሐፍ በለኪሶ የተደረገው ቁፋሮና ጥናት የሚከተለውን እንዳረጋገጠ ይናገራል፦ “ጥፋቱ እጅግ አስከፊ ነበር፤ እንዲሁም ከተማዋን [ለኪሶን] ያጋያት እሳት በጣም ኃይለኛ ስለነበር ሕንፃዎቹ የተገነቡበት ድንጋይ አመድ ሆኗል።”

ትንቢት 2፦ “ሰባው ዓመት የባቢሎን ቈይታችሁ በተፈጸመ ጊዜ እጐበኛችኋለሁ፤ ወደዚህም ሥፍራ [ወደ ይሁዳ ምድር] ልመልሳችሁ የገባሁላችሁን መልካሚቱን ቃሌን እፈጽምላችኋለሁ።”​ኤርምያስ 29:10

ፍጻሜ፦ የአይሁድ ምርኮኞች ከ607 እስከ 537 ዓ.ዓ. ድረስ በግዞት ለ70 ዓመታት ከቆዩ በኋላ የፋርስ ንጉሥ የነበረው ቂሮስ ነፃ ለቀቃቸው፤ እንዲሁም ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው በኢየሩሳሌም የሚገኘውን ቤተ መቅደስ ዳግመኛ እንዲገነቡ ፈቀደላቸው።​—ዕዝራ 1:2-4

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

● በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትንቢት እንደተነገረው እስራኤላውያን በባቢሎን ለ70 ዓመታት በግዞት ቆይተው ነበር? ታዋቂ የእስራኤል የአርኪኦሎጂ ባለሙያ የሆኑት ኤፍሬም ስተርን የሰጡትን አስተያየት ልብ በል። እንዲህ ብለዋል፦ “ከ604 ዓ.ዓ. እስከ 538 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ውስጥ በእስራኤል ምድር ሰው ይኖር እንደነበረ የሚያሳይ ምንም ማስረጃ አልተገኘም። በዚህ ሁሉ ጊዜ፣ ባቢሎናውያን ካጠፏቸው ከተሞች መካከል በአንዱም እንኳ ሰዎች በድጋሚ አልሰፈሩበትም።” በጦርነት ድል በተደረጉት አካባቢዎች ሰዎች ይኖሩ እንደነበር ወይም በድጋሚ እንደሰፈሩ የሚጠቁም ማስረጃ አለመገኘቱ እስራኤላውያን ከ607 እስከ 537 ዓ.ዓ. ድረስ በግዞት በባቢሎን ስለመቆየታቸው ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር በእጅጉ ይስማማል።​—2 ዜና መዋዕል 36:20, 21

● በመላው ሜሶጶጣሚያ የነበሩት የጥንቶቹ ብሔራት በሸክላ ጽላቶች ላይ የመጻፍ ልማድ ነበራቸው። በመሆኑም የቂሮስ ሲሊንደር ተብሎ የሚጠራ ጠንካራ የሆነ የሸክላ ጽላት ተገኝቷል፤ ይህ ጽላት በ539 ዓ.ዓ. አካባቢ እንደተጻፈ የሚገመት ሲሆን ይህ ጊዜ ደግሞ የፋርሱ ንጉሥ ቂሮስ የባቢሎንን መንግሥት የገለበጠበት ዓመት ነው። በዚህ ሸክላ ላይ “እኔ . . . የባቢሎን ንጉሥ . . . ቂሮስ ነኝ” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾበታል። ይኸው ጽሑፍ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “የአምልኮ ስፍራዎቻቸው ከፈራረሱባቸው ረጅም ዘመናት ላስቆጠሩት በጤግሮስ ማዶ ለሚገኙ [ቀደም ሲል ለተጠቀሱት አንዳንድ] ቅዱስ ከተሞች በዚያ የነበሩትን ዕቃዎቻቸውን መልሼላቸዋለሁ። . . . (በተጨማሪም የቀድሞ) ነዋሪዎቻቸውን በሙሉ ሰብስቤ ወደ ትውልድ ስፍራቸው መልሻለሁ።”

ይህ ከዓለማዊ ምንጭ የተገኘ የታሪክ ዘገባ፣ የአይሁድ ምርኮኞች ወደ ትውልድ አገራቸው እንደሚመለሱ ከ200 ዓመታት አስቀድሞ ተጽፎ ከነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ጋር ይስማማል።

ትንቢት 3፦ “የመንግሥታት ዕንቍ፣ የከለዳውያን ትምክሕት፣ የሆነችውን ባቢሎንን፣ እግዚአብሔር እንደ ሰዶምና እንደ ገሞራ ይገለብጣታል። በዘመናት ሁሉ የሚቀመጥባት አይኖርም።”​ኢሳይያስ 13:19, 20

ፍጻሜ፦ የዓለም ኃያል መንግሥት የሆነችው ባቢሎንም በተራዋ በ539 ዓ.ዓ. በሜዶንና በፋርስ ጥምር ሠራዊት እጅ ባልተጠበቀ መንገድ ወደቀች። * ከዚያ በኋላ ከተማዋ ፈጽሞ ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ አልተመለሰችም። እንዲያውም ቀስ በቀስ እየተዳከመች ሄዳለች፤ በመጨረሻም ማንም ‘የማይኖርባት’ የፍርስራሽ ክምር ሆናለች።​—ኤርምያስ 51:37

ታሪክ ምን ያረጋግጣል?

● “ከአሥራ ስድስተኛው እስከ አሥራ ስምንተኛው መቶ ዘመን ድረስ ባሉት ጊዜያት የነበሩት ምዕራባውያን ታሪክ ጸሐፊዎችና አሳሾች” ከተማዋ ወሳኝ ስፍራ እንደነበረች ቢያውቁም “ትክክለኛ ቦታዋ” የት እንደሆነ መለየት ግን እንደተቸገሩ ቶም ቦይ የተባሉ አንድ ምሁር ተናግረዋል፤ ይህም ባቢሎን ሙሉ በሙሉ እንደጠፋች ያሳያል።

● በ1919 ደግሞ በብሪቲሽ ሙዚየም የግብፅና የአሦር ቅርሶችን በኃላፊነት የሚቆጣጠሩት ሄንሪ ረጅናል ሆል የሚባሉ ሰው ባቢሎንን “በአሸዋ የተዋጠች፣ የተደረመሱ ግንቦች . . . ክምር ናት” በማለት ገልጸዋታል።

የእነዚህን ትንቢቶች ፍጻሜ መመርመራችን ምን መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ያደርገናል? መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ትንቢቶችን የያዘ መጽሐፍ መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት እንደተረጋገጠ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁዳንና ባቢሎንን አስመልክቶ የተነገሩት ትንቢታዊ መልእክቶች አስቀድሞ በተገለጸው መሠረት ዝንፍ ሳይሉ ተፈጽመዋል!

የእስራኤል ሕዝብ ከዓመፅ ጎዳናቸው እንዲመለሱ አምላክ የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ለመቀበል አሻፈረኝ በማለታቸው ኢየሩሳሌም ለጥፋት ተዳርጋለች። እስራኤላውያን በትንቢት በተነገረው መሠረት በባቢሎን ለ70 ዓመታት በግዞት ካሳለፉ በኋላ የትውልድ አገራቸው ወደሆነችው ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ ተደርገዋል። የጥንቷ የባቢሎን ከተማም በትንቢት በተገለጸው መንገድ የጠፋች ሲሆን እስከ ዛሬ ድረስ ሰው የማይኖርባት ባድማ ናት። ይሁን እንጂ እስካሁን ያየነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት በርካታ ትንቢቶች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ናቸው።

በሚቀጥለው እትማችን ላይ ከረጅም ጊዜ በፊት በትንቢት የተነገሩ ነገሮች በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንዴት እንደተፈጸሙ እንመለከታለን። እነዚህ ትንቢቶችም ቢሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ ስለመሆኑ ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.20 ሜዶናውያን ባቢሎንን ድል በማድረግ ረገድ ግንባር ቀደም ሚና እንደሚጫወቱ ኢሳይያስ ከ200 ዓመታት አስቀድሞ ትንቢት ተናግሮ ነበር።​—ኢሳይያስ 13:17-19ን እና 21:2ን ተመልከት።

[በገጽ 12 እና 13 ላይ የሚገኝ ሠንጠረዥ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ከባቢሎን ጋር የተያያዙ ዓመታት

732 ዓ.ዓ. ገደማኢሳይያስ ስለ ባቢሎን ውድቀት ትንቢት ተናገረ

(ዓ.ዓ.)

647 ኤርምያስ ነቢይ ሆኖ ተሾመ

632 ባቢሎን አሦርን ድል አደረገች

625 ናቡከደነፆር መግዛት ጀመረ

617 ዳንኤልና ሕዝቅኤል ወደ ባቢሎን ተወሰዱ

607 ናቡከደነፆር ኢየሩሳሌምን ደመሰሰ

582 የናቡከደነፆር አገዛዝ አበቃ

539 ባቢሎን፣ በሜዶንና በፋርስ እጅ ወደቀች

537 አይሁዳውያን ምርኮኞች ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለሱ ተፈቀደላቸው

አይሁዳውያን ባቢሎን ውስጥ በግዞት 70 ዓመት ቆዩ

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የለኪሶ ደብዳቤዎች፣ ባቢሎናውያን ይሁዳን ድል እንደሚያደርጉ ኤርምያስ የተናገረውን ትንቢት ይደግፋሉ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የቂሮስ ሲሊንደር፣ ቂሮስ ምርኮኞችን ወደ ትውልድ አገራቸው የመመለስ ፖሊሲ እንደነበረው ይናገራል

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Page 12, Lachish Letter: Photograph taken by courtesy of the British Museum; page 13, Cyrus Cylinder: © The Trustees of the British Museum