መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ፣ ክፍል 4
መጽሐፍ ቅዱስ—ትክክለኛ ትንቢት የያዘ መጽሐፍ፣ ክፍል 4
ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ተናግሯል
በእነዚህ ስምንት ተከታታይ “የንቁ!” እትሞች ላይ መጽሐፍ ቅዱስን ልዩ ከሚያደርጉት ገጽታዎች መካከል አንዱ ስለሆነው ማለትም በውስጡ ስለያዘው ትንቢት እንመረምራለን። ይህ ተከታታይ ርዕስ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ እንድታገኝ ይረዳሃል፦ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጥሩ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ያሰፈሯቸው ግምታዊ ሐሳቦች ናቸው? ወይስ እነዚህ ትንቢቶች በአምላክ መንፈስ መሪነት መጻፋቸውን የሚጠቁሙ ነገሮች አሉ? እስቲ ማስረጃዎቹን አብረን እንመርምር።
ከዛሬ 2,000 ዓመታት ገደማ በፊት ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ ሳለ በጠላቶቹ እጅ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚገደል ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ስለዚህ ሁኔታ እንዴት ሊያውቅ ቻለ? “ብሉይ ኪዳን” ተብለው በሚጠሩት በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ስለ እሱ የተነገሩትን ትንቢቶች ጠንቅቆ ያውቅ ስለነበር ነው። ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል ብዙዎቹ የተጻፉት ኢየሱስ ከመወለዱ ከ700 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት ነው። ኢሳይያስ እነዚህን ሐሳቦች ቀደም ብሎ እንደጻፋቸው እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
በ1947፣ በዌስት ባንክ ከቤድዊን ጎሳ የሆነ አንድ እረኛ በሙት ባሕር ሰሜን ምዕራብ ዳርቻ ባለው የኩምራን ዋሻ ውስጥ ተደብቀው የቆዩ ጥቅልሎችን አገኘ። እነዚህና በዚያ አካባቢ ባሉ ሌሎች ዋሻዎች ውስጥ የተገኙት ጥቅልሎች የሙት ባሕር ጥቅልሎች ተብለው ይጠራሉ። ከእነዚህ መካከል ሙሉውን የኢሳይያስን መጽሐፍ የያዘው ቅጂ ይገኝበታል። * ይህ ቅጂ ኢየሱስ ከመወለዱ ከሁለት መቶ ዓመታት ገደማ በፊት የተጻፈ ነው። እንግዲያው ኢሳይያስ የጻፈው የተከናወኑ ነገሮችን ሳይሆን ወደፊት የሚፈጸሙ ነገሮችን ነበር። ታዲያ ክርስቶስ ወይም መሲሕ ስለሚቀበለው መከራ ኢሳይያስ ምን ትንቢት ተናግሯል? * እስቲ ኢሳይያስ የጻፋቸውን ሁለት ትንቢቶች እንመልከት።
ክርስቶስ መከራ እንደሚቀበል ትንቢት ተነግሯል
ትንቢት 1፦ “ለሚገርፉኝ ጀርባዬን . . . ሰጠሁ።” —ኢሳይያስ 50:6 *
ፍጻሜ፦ በ33 ዓ.ም. የኢየሱስ ጠላቶች የሆኑት አይሁዳውያን ኢየሱስን በሮማዊው ገዥ በጳንጥዮስ ጲላጦስ ፊት ለፍርድ አቀረቡት። አገረ ገዥው ኢየሱስ ንጹሕ ሰው መሆኑን በማወቁ ሊፈታው ሞከረ። ይሁን እንጂ ጲላጦስ፣ አይሁዳውያኑ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ኢየሱስን እንዲገድለው ስለወተወቱት ‘የጠየቁት እንዲፈጸም ፈረደላቸው’፤ ከዚያም ኢየሱስን እንዲሠቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው። (ሉቃስ 23:13-24) ከዚያ በፊት ግን ጲላጦስ “ኢየሱስን ወስዶ ገረፈው።” (ዮሐንስ 19:1) ኢሳይያስ አስቀድሞ እንደተናገረው ኢየሱስ ‘ለሚገርፉት ጀርባውን ሰጠ’ እንጂ ለመከላከል አልሞከረም።
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
● ሮማውያን የሞት ፍርድ የተበየነባቸውን ሰዎች ከመግደላቸው በፊት የመግረፍ ልማድ እንደነበራቸው የታሪክ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደገለጸው “ግርፋቱ የሚፈጸመው ቁርጥራጭ ወይም ሹል ብረቶች በተሰኩበት የጠፍር ጅራፍ ነበር። ግለሰቡ ከወገቡ በላይ ራቁቱን ሆኖ . . . ሥጋው እስኪተለተል ድረስ . . . ይገረፋል። አንዳንድ ጊዜ በግርፋቱ ብቻ ግለሰቡ ሊሞት ይችላል።” ኢየሱስ ግን የመከራው የመጀመሪያ ክፍል ከሆነው ከዚህ ከባድ ግርፋት በሕይወት ተርፏል።
ክርስቶስ እንደሚገደል ትንቢት ተነግሯል
ትንቢት 2፦ “እስከ ሞት ድረስ ሕይወቱን አሳልፎ [ይሰጣል]።” (ኢሳይያስ 53:12) * ከዚህ ጋር በተያያዘ መዝሙር 22:16 እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዟል፦ “የክፉዎች ሸንጎ በዙሪያዬ ተሰልፎአል፤ እጆቼንና እግሮቼንም ቸነከሩኝ።”
ፍጻሜ፦ ማርቆስ 15:15 ጲላጦስ ‘ኢየሱስን ከገረፈው በኋላ እንዲሰቀል አሳልፎ ሰጠው’ ይላል። በኢየሱስ ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ የሞት ቅጣት እጆቹንና እግሮቹን በእንጨት ላይ መቸንከርን ይጨምር ነበር። (ዮሐንስ 20:25) የተወሰኑ ሰዓታት እንዳለፉ “ኢየሱስ በታላቅ ድምፅ ከጮኸ በኋላ እስትንፋሱ ቆመ።”—ማርቆስ 15:37
ታሪክ ምን ያረጋግጣል?
● ዓለማዊ የታሪክ ጸሐፊዎች ስለ ኢየሱስ አሟሟት ብዙም ባይጽፉም በ55 ዓ.ም. የተወለደው ታሲተስ የተባለ እውቅ የታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ብሏል፦ “ክርስቲያን ለሚለው ስም መገኛ የሆነው ክርስቱስ [ክርስቶስ] በጢባርዮስ የንግሥና ዘመን ከአስተዳዳሪዎቻችን አንዱ በነበረው በጳንጥዮስ ጲላጦስ እጅ ከፍተኛ የሆነ ቅጣት ተቀብሏል።” * ታሲተስ የተናገረው ይህ ሐሳብ ጢባርዮስ ቄሳርን፣ ጳንጥዮስ ጲላጦስንና ሌሎች ባለሥልጣናትን በስም ከሚጠቅሱት የወንጌል ዘገባዎች ጋር ሙሉ በሙሉ ይስማማል።—ሉቃስ 3:1፤ 23:1-33፤ ዮሐንስ 19:1-24
በተጨማሪም ሮማውያን፣ ባሪያዎችንና በሕዝብ ዘንድ የሚጠሉ ወንጀለኞችን በስቅላት ይቀጡ እንደነበረ ታሪክ ያረጋግጣል። ይህን ለማስፈጸም አንዳንድ ጊዜ ወንጀለኞቹን የቆመ እንጨት ላይ ያስሯቸዋል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ምስማር ይጠቀማሉ። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንዲህ ይላል፦ “በወንጀለኛው እጆችና እግሮች ላይ ምስማር ይመታ ነበር፤ እንዲሁም ግለሰቡ በውኃ ጥም እንዲቃጠልና ይህ ነው በማይባል ሕመም እንዲሠቃይ እዚያው በተሰቀለበት እንዲቆይ ይደረግ ነበር።”
ቀደም ሲል እንደተገለጸው፣ ኢየሱስ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚገደል አስቀድሞ ያውቅ ነበር። በመሆኑም የሚሞትበት ጊዜ እየተቃረበ ሲመጣ ለታማኝ ተከታዮቹ በድፍረት እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዝን ነው፤ የሰው ልጅ ለካህናት አለቆችና ለጸሐፍት አልፎ ይሰጣል፤ እነሱም ሞት ይፈርዱበታል፤ እንዲሁም እንዲያፌዙበት፣ እንዲገርፉትና እንዲሰቅሉት ለአሕዛብ አሳልፈው ይሰጡታል።” (ማቴዎስ ) ይሁን እንጂ አንዳንዶች ‘ኢየሱስ መሞት ያስፈለገው ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ያነሳሉ። የዚህ ጥያቄ መልስ ሁላችንንም የሚመለከት ከመሆኑም በላይ እስከ ዛሬ ከሰማናቸው ሁሉ የላቀ ምሥራች ይዟል። 20:18, 19
“ስለ በደላችንም ደቀቀ”
ፍጽምና የጎደለን ሰዎች በመሆናችን ብዙ ጊዜ ስህተት እንሠራለን። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነቱን ስህተት ኃጢአት ብሎ ይጠራዋል። ኃጢአት በአንድ ሞተር ውስጥ ከገቡ ጠጠሮች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ጠጠሩ ውሎ ሲያድር ሞተሩን በመብላት ጉልበቱን እያዳከመው ይመጣል፤ በመጨረሻም መሥራት እንዲያቆም ያደርገዋል። በተመሳሳይም ኃጢአት እንድናረጅ፣ እንድንታመምና እንድንሞት ያደርገናል። ሮም 6:23 “ኃጢአት የሚከፍለው ደሞዝ ሞት ነው” ይላል። ይሁን እንጂ የክርስቶስ ሞት ከዚህ አሳዛኝ ሁኔታ ነፃ መውጣት እንድንችል ያደርገናል። እንዴት? ኢሳይያስ በአንድ ሌላ ትንቢት ላይ ክርስቶስ “ስለመተላለፋችን” እንደሚሞት ወይም “ስለ በደላችን” እንደሚደቅቅ እንዲሁም ‘በእሱ ቁስል እኛ እንደምንፈወስ’ ጽፏል። *—ኢሳይያስ 53:5
የኢሳይያስ ትንቢት ኢየሱስ በዮሐንስ 3:16 ላይ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ ያስታውሰናል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”
በኢየሱስ ላይ እምነት ልታዳብር የምትችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምትችለው ስለ እሱ በመማር ነው። ኢየሱስ ሲጸልይ እንዲህ ብሏል፦ “የዘላለም ሕይወት ማግኘት እንዲችሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ስለሆንከው ስለ አንተና ስለላክኸው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እውቀት መቅሰማቸውን መቀጠል አለባቸው።” (ዮሐንስ 17:3) ይህ ውድ የሆነ እውቀት የሚገኘው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
ኢየሱስ፣ ብዙ ሰዎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ እንደሚፈልግ ምንም ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ ይህን ታላቅ ትንቢት ተናግሯል፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል።” (ማቴዎስ 24:14) እዚህ ላይ ኢየሱስ የተናገረው አምላክ ስላቋቋመው መስተዳድር ሲሆን ይህ መስተዳድር፣ የሰው ልጆች የክርስቶስ መሥዋዕት የሚያመጣቸውን በረከቶች እንዲያገኙ ያደርጋል። በሚቀጥሉት የዚህ ዓምድ ሁለት ተከታታይ ክፍሎች ላይ ይህ ትንቢትም በትክክል እንደተፈጸመ የሚያሳዩ ማስረጃዎችን እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.5 በዚህ ቦታ ከተገኙት ጥቅልሎች ውስጥ ሙሉ ጥቅል የተገኘው የኢሳይያስ መጽሐፍ ብቻ ነው። ሌሎቹ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑ መጻሕፍት ቁርጥራጮች ናቸው።
^ አን.5 የመሲሑን ማንነት ለማወቅ የሚያስችሉ ተጨማሪ ትንቢቶችን ለማግኘት የሐምሌ 2012 ንቁ! መጽሔትን ተመልከት።
^ አን.7 የዚህ ዓረፍተ ነገር ባለቤት ክርስቶስ እንደሆነ በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንችላለን። ለምሳሌ ቁጥር 8 ላይ “ንጹሕ መሆኔን የሚያረጋግጥልኝ በአጠገቤ አለ” ይላል። እዚህ ላይ “ንጹሕ” የተባለው ኢየሱስ ሲሆን “በአጠገቤ አለ” የተባለው ደግሞ አምላክ ነው። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ከእሱ በቀር በአምላክ ፊት ንጹሕ ወይም ጻድቅ የሆነና ኃጢአት የሌለበት አንድም ሰው አልነበረም።—ሮም 3:23፤ 1 ጴጥሮስ 2:21, 22
^ አን.12 ከኢሳይያስ 52:13 እስከ 53:12 ላይ የሚገኘው ሐሳብ መሲሑን አስመልክቶ በዝርዝር የተነገሩ በርካታ ትንቢቶችን ይዟል። ለምሳሌ ኢሳይያስ 53:7 “እንደ ጠቦት ለዕርድ ተነዳ። . . . አፉን አልከፈተም” ይላል። ቁጥር 10 ደግሞ “ነፍሱን የኀጢአት መሥዋዕት” አድርጎ እንደሚያቀርብ ይናገራል።
^ አን.15 በጥንት ጊዜ የነበሩ ሌሎች የታሪክ ጸሐፊዎችም ክርስቶስን ጠቅሰዋል። ከእነዚህም መካከል ስዊቶኒየስ የተባለ እውቅ ሮማዊ የታሪክ ምሁር (በአንደኛው መቶ ዘመን)፣ የቢቲኒያ አገረ ገዥ የነበረው ትንሹ ፕሊኒ (በሁለተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ) እንዲሁም አይሁዳዊው የታሪክ ምሁር ጆሴፈስ (በአንደኛው መቶ ዘመን) የሚገኙበት ሲሆን ጆሴፈስ “ያዕቆብ፣ ክርስቶስ ተብሎ የሚጠራው የኢየሱስ ወንድም” እንደሆነ ጽፏል።
^ አን.19 ኢየሱስ “ምንም ኃጢአት” ስላልሠራ መሞት አልነበረበትም። (1 ጴጥሮስ 2:22) ሆኖም የኃጢአታችንን ዋጋ ለመክፈል ሲል ሕይወቱን ለእኛ በመስጠት ከሞት መዳፍ ፈልቅቆ አውጥቶናል። በመሆኑም የኢየሱስ ሞት “ቤዛዊ” መሥዋዕት ተብሎ ይጠራል። (ማቴዎስ 20:28) በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ተመልከት፤ ይህን መጽሐፍ www.mr1310.com በተባለው ድረ ገጽም ላይ ማግኘት ይቻላል።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ለክርስቶስ መሥዋዕታዊ ሞት ጥላ የሆኑ ነገሮች
ለእስራኤል ብሔር የተሰጠው የአምላክ ሕግ መሲሑ ወደፊት ለሚያደርጋቸው ነገሮች ጥላ ወይም ናሙና ሆነው የሚያገለግሉ ደንቦችም ነበሩት። ለምሳሌ አንድ እስራኤላዊ ኃጢአት ከሠራ ወይም የአምላክን ትእዛዝ ከጣሰ እንከን የሌለበት እንስሳ መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ነበረበት። (ዘሌዋውያን 17:11፤ 22:21) ታዲያ የእንስሳት መሥዋዕት ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ሊያስተሰርይ ይችላል? በፍጹም። (ዕብራውያን 10:4) ይሁን እንጂ ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ለሚሸፍነው መሥዋዕት ይኸውም ‘የዓለምን ኃጢአት ለሚያስወግደው የአምላክ በግ’ ጥላ ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም ጥላ ሆኗል። (ዮሐንስ 1:29፤ ዕብራውያን 10:1, 5-10) በበግ በተመሰለው በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ሁሉ ውድ የሆነው የዘላለም ሕይወት ተስፋ አላቸው።—ዮሐንስ 6:40