በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

አምላክ በዛሬው ጊዜ ሰዎችን ለመቅጣት በተፈጥሮ አደጋዎች ይጠቀማል?

አምላክ በዛሬው ጊዜ ሰዎችን ለመቅጣት በተፈጥሮ አደጋዎች ይጠቀማል?

አንዳንድ ሰዎች አምላክ ሰዎችን ለመቅጣት የተፈጥሮ አደጋዎችን እንደሚጠቀም ያምናሉ። ሌሎች ደግሞ ይህን ሐሳብ ይቃወማሉ። በዚህ ረገድ ምን አቋም መያዝ እንዳለባቸው ግራ የተጋቡ ሰዎችም አሉ። አንድ የሃይማኖታዊ ጥናቶች ፕሮፌሰር እንዲህ ብለዋል፦ “አብዛኞቹ ሃይማኖቶች የተፈጥሮ አደጋዎች የሚደርሱት በአምላክ ፈቃድ ስለመሆኑ በእርግጠኝነት መናገር የሚችል ማንም እንደሌለ ያስተምራሉ።”

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ አጥጋቢ መልስ ይሰጣል። አምላክ በዛሬው ጊዜ የተፈጥሮ አደጋዎችን ተጠቅሞ ሰዎችን እንደሚቀጣ ለሚሰማቸው ሰዎች ጥሩ ግንዛቤ የሚያሰፋ ሐሳብ ይዟል። በተጨማሪም በብዙ ሰዎች ላይ ከሚደርሰው መከራ በስተ ጀርባ ያለው ነገር ምን እንደሆነ እንድንገነዘብ ያስችለናል።

አምላክ ነገሮችን የሚያከናውንበት መንገድ

መጽሐፍ ቅዱስ ስሙ ይሖዋ ስለሆነው አምላክ ሁለት መሠረታዊ እውነቶችን ይገልጻል። አንደኛ፣ ይሖዋ ፈጣሪ ስለሆነ የምድርን የተፈጥሮ ኃይሎች መቆጣጠር ይችላል፤ እንዲሁም በእነሱ ላይ ሥልጣን አለው። (ራእይ 4:11) ሁለተኛ፣ ይሖዋ የሚያደርጋቸው ነገሮች ሁልጊዜ ከማንነቱ፣ ከባሕርይውና ካወጣቸው መሥፈርቶች ጋር የሚስማሙ ናቸው። በ⁠ሚልክያስ 3:6 ላይ “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም” በማለት ተናግሯል። እነዚህን ነጥቦች በአእምሯችን በመያዝ በቀድሞ ዘመን ስለተፈጸሙ ሁለት ክስተቶች ማለትም ስለ ጥፋት ውኃና ስለ ድርቅ የሚገልጹ ታሪኮችን እንመልከት። አምላክ ፍርዱን ለማስፈጸም የተፈጥሮ ኃይሎችን በተጠቀመ ጊዜ ሁሉ (1) ማስጠንቀቂያ እንደሰጠ፣ (2) ያመጣበትን ምክንያት እንደገለጸ እና (3) ለታዛዥ አምላኪዎቹ ጥበቃ እንዳደረገላቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች እንመለከታለን።

በኖኅ ዘመን የደረሰው የጥፋት ውኃ

ማስጠንቀቂያ።

የጥፋት ውኃ ከመምጣቱ ከአሥርተ ዓመታት በፊት ይሖዋ ለኖኅ “ከሰማይ በታች የሕይወት እስትንፋስ ያለባቸውን ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ለማጥፋት እነሆ፤ በምድር ላይ የጥፋት ውሃ አወርዳለሁ” በማለት ነግሮታል። (ዘፍጥረት 6:17) “የጽድቅ ሰባኪ” የነበረው ኖኅ ሕዝቡን ቢያስጠነቅቅም እነሱ ግን “ምንም አላስተዋሉም።”—2 ጴጥሮስ 2:5፤ ማቴዎስ 24:39

ምክንያት።

“ሰውን ሁሉ ላጠፋ ነው፤ ምድር በሰው ዐመፅ ስለ ተሞላች” በማለት ይሖዋ ጥፋት የሚያመጣበትን ምክንያት ተናግሯል።—ዘፍጥረት 6:13

ለታዛዥ አምላኪዎቹ ጥበቃ ያደርጋል።

ይሖዋ፣ ኖኅ ስለሚገነባው መርከብ ዝርዝር መመሪያዎችን በመስጠት ከጥፋት ውኃው መትረፍ የሚቻልበትን ዝግጅት አድርጎ ነበር። በመሆኑም “ኖኅና ከእርሱ ጋር በመርከቧ ውስጥ የነበሩት ብቻ ተረፉ።”—ዘፍጥረት 7:23

በእስራኤል የደረሰው ድርቅ

ማስጠንቀቂያ።

ይሖዋ በእስራኤል ላይ ከባድ ድርቅ ከማምጣቱ በፊት፣ የእሱ ነቢይ የነበረው ኤልያስ “[በአምላክ] ቃል ካልሆነ በቀር፣ በሚቀጥሉት ዓመታት ዝናብ ወይም ጠል አይኖርም” በማለት አስታውቋል።—1 ነገሥት 17:1

ምክንያት።

ይሖዋ ይህን እርምጃ የወሰደው እስራኤላውያን የሐሰት አምላክ የሆነውን በዓልን በማምለካቸው ነበር። ኤልያስ ይህን ሁኔታ ለእስራኤላውያን ሲነግራቸው “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ተዋችሁ፣ እነ በኣልንም ተከተላችሁ” ብሏል።—1 ነገሥት 18:18

ለታዛዥ አምላኪዎች ጥበቃ ያደርጋል።

ይሖዋ ታዛዥ አምላኪዎቹ በድርቁ ዘመን እንዳይራቡ አድርጓል።—1 ነገሥት 17:6, 14፤ 18:4፤ 19:18

ከዚህ ምን እንማራለን?

በዛሬው ጊዜ የሚደርሱት የተፈጥሮ አደጋዎች፣ አምላክ ሰዎችን ለመቅጣት የሚጠቀምባቸው መሣሪያዎች እንደሆኑ የምናስብበት ምንም ምክንያት የለም። ይሖዋ የፍትሕ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ‘ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር አጥፍቶ’ አያውቅም። (ዘፍጥረት 18:23, 25) ለእሱ ታዛዥ የሆኑ ሰዎች እርዳታ የሚያገኙበትን መንገድ ያዘጋጃል። በዛሬው ጊዜ የተፈጥሮ አደጋዎች ማንንም ሳይለዩ ወንዶችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን ያጠቃሉ።

አምላክ በሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ ተጠያቂ አይደለም

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው በዛሬው ጊዜ የሚከሰቱትን የተፈጥሮ አደጋዎች፣ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ተመዝግበው ከሚገኙትና አምላክ ከወሰዳቸው የቅጣት እርምጃዎች ጋር የሚያመሳስላቸው ምንም ነገር የለም። ከዚህም በላይ እነዚህ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚደርሱ አደጋዎች አምላክ ያመጣቸው እንደሆኑ መናገር ከፈጣሪ ባሕርያት ጋር የማይጣጣም ነው። ያዕቆብ 1:13 አምላክ ሰዎችን በክፉ ነገር እንደማይፈትን የሚናገር ሲሆን 1 ዮሐንስ 4:8 ደግሞ “አምላክ ፍቅር ነው” በማለት የእሱን ባሕርይ ጠቅለል አድርጎ ይገልጻል። በመሆኑም አምላክ በተለያዩ አካባቢዎች በሚደርሱ ማዕበሎች፣ ርዕደ መሬቶችና ሌሎች ተመሳሳይ አደጋዎች ምክንያት በንጹሐን ሰዎች ላይ ለሚደርሰው መከራ ፈጽሞ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። ታዲያ እነዚህ የተፈጥሮ አደጋዎች ማብቂያ ይኖራቸው ይሆን?

መከራና ሥቃይ ያበቃል

ይሖዋ አምላክ፣ የሰው ዘር በተፈጥሮ አደጋዎች እንዲሠቃይ ፈጽሞ ዓላማው አልነበረም። የእሱ ፈቃድ ሰዎች ሰላማዊ በሆኑ ሁኔታዎች ሥር በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። በመሆኑም በኖኅ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ክፋትን ለማስወገድ በቅርቡ በምድር ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ ይገባል። ይሖዋ አምላክ እንደቀድሞው ሁሉ አሁንም በመላው ዓለም የማስጠንቀቂያ መልእክት እንዲታወጅ አድርጓል፤ ይህም ሰዎች ከጥፋቱ ለመትረፍ እንዲዘጋጁ ያስችላቸዋል።—መዝሙር 37:9, 11, 29፤ ማቴዎስ 24:14