በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወጣቶች ጥያቄ

ወንድነት የሚለካው በምንድን ነው?

ወንድነት የሚለካው በምንድን ነው?

“አባቴ የሞተው የሦስት ዓመት ልጅ ሳለሁ ነበር። አባታቸው ያሳደጋቸውን ልጆች ሳይ አንዳንድ ጊዜ እቀናለሁ። ከእኔ የተሻለ በራስ የመተማመን ስሜት እንዳላቸው ይሰማኛል።”—አሌክስ *

“ከአባቴ ጋር ብዙ አንቀራረብም። በመሆኑም ወንድ መሆን ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ያወቅኩት በራሴ ጥረት ነው።”—ጆናታን

ከላይ እንደተጠቀሱት ወጣቶች ተሰምቶህ ያውቃል? ወንድነት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ማወቅ አለመቻል ያሳስብሃል? ከሆነ ሐሳብ አይግባህ!

ሁለት የተለመዱ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን እንዴት ማሸነፍ እንደምትችል እስቲ እንመልከት።

ተፈታታኝ ሁኔታ 1፦ ብዙዎች ያላቸው የተሳሳተ አመለካከት

አንዳንዶች ምን ይላሉ?

  • ወንድ ልጅ ጠንካራ መሆን አለበት፤ ፈጽሞ ማልቀስ የለበትም።

  • ወንድ ልጅ ማንም እንዲህ አድርግ እንዲለው መፍቀድ የለበትም።

  • ወንዶች ከሴቶች ይበልጣሉ።

ጉዳዩ ከሌላ አቅጣጫ ሲታይ፦ አንድ ወንድ፣ ሙሉ ሰው ሲሆን ልጅ ከነበረበት ጊዜ የተሻለ ብስለት ይኖረዋል፤ ይህ ሲባል ግን ከሴቶች የሚበልጥ ይሆናል ማለት አይደለም። የወንድነት ባሕርይ አለህ የሚባለው የልጅነት ባሕርይህን ስትተው ነው። ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ጽፏል፦ “ሕፃን በነበርኩበት ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር፣ እንደ ሕፃን አስብ እንዲሁም እንደ ሕፃን አመዛዝን ነበር፤ አሁን ሙሉ ሰው ከሆንኩ በኋላ ግን የሕፃንነትን ጠባይ ትቻለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 13:11) በሌላ አነጋገር የልጅነት አስተሳሰብ፣ አነጋገርና ምግባር ትተህ ብስለት የሚንጸባረቅበት አስተሳሰብ፣ አነጋገርና ምግባር እያዳበርክ ስትሄድ ሙሉ ሰው ወይም ወንድ መባል ትችላለህ። *

እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ ቀጥሎ ለቀረቡት ጥያቄዎች የምትሰጠውን መልስ በወረቀት ላይ አስፍር፦

  1. “የሕፃንነትን ጠባይ” በመተው ረገድ በየትኞቹ ነገሮች ተሳክቶልኛል?

  2. የትኞቹን ነገሮችስ ማሻሻል ይገባኛል?

በተጨማሪም ሉቃስ 7:36-50⁠ን አንብብ። ኢየሱስ (1) ትክክል ለሆነው ነገር አቋም በመውሰድ እንዲሁም (2) ሴቶችን ጨምሮ ሌሎችን በአክብሮት በመያዝ ትክክለኛ የወንድነት ባሕርይ ያሳየው እንዴት እንደሆነ ልብ በል።

“ጓደኛዬን ኬንን አደንቀዋለሁ። አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ጥንካሬ አለው፤ እንዲሁም ደግ ሰው ነው። የእሱ ምሳሌነት ትክክለኛ የወንድነት ባሕርይ ያለው ሰው ራሱን ከፍ ለማድረግ ሲል ሌሎችን ዝቅ እንደማያደርግ እንድገነዘብ ረድቶኛል።”—ጆናታን

ተፈታታኝ ሁኔታ 2፦ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አባት አለማግኘት

አንዳንዶች ምን ይላሉ?

  • ከአባትህ ጋር የማትኖር ከሆነ ወንድነት ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ፈጽሞ ማወቅ አትችልም።

  • አባትህ መጥፎ ምሳሌ ከሆነ አንተም እሱ የሚሠራቸውን ስህተቶች መድገምህ አይቀርም።

ጉዳዩ ከሌላ አቅጣጫ ሲታይ፦ አስተዳደግህ ያን ያህል ጥሩ ባይሆንም እንኳ ትክክለኛ የወንድነት ባሕርያትን ማዳበር አትችልም ማለት አይደለም! ያለህበትን ሁኔታ መቀየር ትችላለህ። (2 ቆሮንቶስ 10:4) ንጉሥ ዳዊት ለልጁ ለሰለሞን የሰጠውን “በርታ፤ ቆራጥ ወንድ ሁን” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ትችላለህ።—1 ነገሥት 2:2 NW

እርግጥ ነው፣ ለልጁ እምብዛም ትኩረት ከማይሰጥ አባት ጋር መኖር ወይም እስከ ጭራሹ ያለ አባት ማደግ ከባድ ነው። በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው አሌክስ “አባትን አለማወቅ በጣም ይጎዳል” ብሏል። “አሁን 25 ዓመቴ ሲሆን በአሥራዎቹ ዕድሜ እያለሁ መማር የነበረብኝን ነገሮች ገና እያወቅሁ እንዳለሁ ይሰማኛል።” አንተም እንደ አሌክስ የሚሰማህ ከሆነ ምን ማድረግ ትችላለህ?

እንዲህ ለማድረግ ሞክር፦ እንደ አባት መካሪ ሊሆንልህ የሚችል ጥሩ አርዓያ የሚሆን ሰው ፈልግ። * አንድ ወንድ ሊያዳብራቸው የሚገቡ ትክክለኛ ባሕርያት የትኞቹ እንደሆኑ ጠይቀው። ከዚያም አንተ እነዚህን ባሕርያት ማዳበር የምትችለው እንዴት እንደሆነ ጠይቀው።—ምሳሌ 1:5

በተጨማሪም ምሳሌ መጽሐፍ ከምዕራፍ 1 እስከ 9 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ አንብብ። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ የሚገኘውን አንድ ልጅ ጥበበኛና መንፈሳዊ መሆን እንዲችል የሚረዳ አባታዊ ምክር ልብ በል።

ትክክለኛ የወንድ ባሕርያትን እያዳበርኩ በመሆኑ ደስተኛ ነኝ። በእርግጥ እንዲህ ያለ እድገት ሳደርግ አባቴ ቢረዳኝ ደስ ይለኝ ነበር፤ ያም ባይሆን ግን ወደፊት የተሻለ ሰው መሆን እንደምችል ይሰማኛል። ትክክለኛ የወንድነት ባሕርያትን ማዳበር እንደምችል እርግጠኛ ነኝ!”—ጆናታን

 

^ አን.3 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.12  “ልጅና ሙሉ ሰው ሲነጻጸር” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

^ አን.24 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች ጥሩ መካሪ ሊሆኑ ይችላሉ።

ወላጆችህን ለምን አትጠይቃቸውም?

የወንድነት መገለጫው ምን ይመስላችኋል? ብስለት በማሳየት ረገድ እኔ እንዴት ነኝ?