ለቤተሰብ | የወላጅ ሚና
ልጆች እልኸኛ ሲሆኑ ምን ማድረግ ይቻላል?
ተፈታታኙ ነገር
የሁለት ዓመት ልጃችሁ በሚበሳጭበት ጊዜ ይጮኻል፣ ይራገጣል እንዲሁም ይንፈራገጣል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ ‘ልጄ እንዲህ የሚሆነው በደህናው ነው? የዚህን ያህል እልኸኛ እንዲሆን ያደረገው ያጠፋሁት ነገር ይኖር ይሆን? ይህ ፀባዩ ሲያድግ ይተወው ይሆን?’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል።
ጥሩነቱ፣ የሁለት ዓመት ልጃችሁ ባሕርዩን እንዲያስተካክል ልትረዱት ትችላላችሁ። በመጀመሪያ ግን እንዲህ ዓይነት ፀባይ እንዲያሳይ አስተዋጽኦ የሚያደርጉት ነገሮች ምን እንደሆኑ እንመልከት። *
ምክንያቱ ምንድን ነው?
ትናንሽ ልጆች ስሜታቸውን በመቆጣጠር ረገድ ብዙ ልምድ የላቸውም። ይህ በራሱ አንዳንድ ጊዜ እልኸኞች እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ።
አንድ ሕፃን ሁለት ዓመት ገደማ ሲሆነው ምን ዓይነት ለውጦች እንደሚያጋጥሙት አስቡ። ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ ወላጆቹ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ያሟሉለት ነበር። ለምሳሌ፣ በሚያለቅስበት ጊዜ ወዲያው ይደርሱለታል። ‘ታሞ ይሆን? ርቦት ይሆን? ያልተመቸው ነገር ይኖር ይሆን? ወይስ የሽንት ጨርቅ እንዲቀየርለት ፈልጎ?’ ብለው ያስባሉ። ወላጆች ልጁ እንዲመቸው የሚያስፈልገውን ሁሉ ያደርጉለት ነበር። ደግሞም ሕፃኑ በዚህ ወቅት ሙሉ በሙሉ የወላጆቹ እንክብካቤ ስለሚያስፈልገው እንዲህ ማድረጋቸው ተገቢ ነው።
ይሁን እንጂ ሕፃኑ ሁለት ዓመት ገደማ ሲሆነው ወላጆቹ የቀድሞውን ያህል ትኩረት እንደማይሰጡት መገንዘብ ይጀምራል። እንዲያውም እሱ የፈለገውን ሁሉ ከማድረግ ይልቅ ከእሱ የሚጠብቁት ነገር ይኖራል። ሁኔታው ድንገት ይለወጥበታል፤ አንድ የሁለት ዓመት ሕፃን ይህ ለውጥ ስለማያስደስተው ተቃውሞውን ለመግለጽ የእልኸኝነት ባሕርይ ሊያሳይ ይችላል።
ውሎ አድሮ ግን ልጁ፣ የወላጆቹ ሥራ እሱን መንከባከብ ብቻ ሳይሆን ለእሱ መመሪያ መስጠትንም እንደሚጨምር መቀበል ይጀምራል። በተጨማሪም እሱም ‘ለወላጆቹ መታዘዝ’ እንደሚጠበቅበት መገንዘብ ሊጀምር ይችላል። (ቆላስይስ 3:20) ይህ እስከሚሆንበት ጊዜ ግን ልጁ እልኸኛ በመሆን የወላጆቹን ትዕግሥት መፈታተኑ አይቀርም።
ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
ችግሩን ተረዱለት። ልጃችሁ ገና ሕፃን መሆኑን አትርሱ። ስሜቱን በመቆጣጠር ረገድ በቂ ልምድ ስለሌለው በሚናደድበት ጊዜ ብስጭቱን የሚገልጽበት መንገድ ከመጠን ያለፈ ሊሆን ይችላል። ሁኔታውን በእሱ ቦታ ሆናችሁ ለማየት ሞክሩ።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ 1 ቆሮንቶስ 13:11
ረጋ በሉ። ልጃችሁ እልኸኛ በሚሆንበት ጊዜ እናንተም መቆጣታችሁ የሚያስገኘው ጥቅም የለም። በተቻለ መጠን ምንም እንዳልተፈጠረ በመቁጠር ረብሻውን ችላ በሉት። ልጃችሁ እልኸኛ የሚሆንበትን ምክንያት ማስታወሳችሁ ሁኔታውን በእርጋታ ለመያዝ ይረዳችኋል።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ምሳሌ 19:11
በአቋማችሁ ጽኑ። ልጃችሁ እልኸኛ በሚሆንበት ጊዜ አቋማችሁን አላልታችሁ የሚፈልገውን ካደረጋችሁለት ሌላ ጊዜም የፈለገውን ነገር በዚህ መንገድ ማግኘት እንደሚችል ሊያስብ ይችላል። ቃላችሁን እንደማትለውጡ ለልጃችሁ በእርጋታ አሳዩት።—የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት፦ ማቴዎስ 5:37
ልጃችሁ እልኸኛ የሚሆንበትን ምክንያት ማስታወሳችሁ ሁኔታውን በእርጋታ ለመያዝ ይረዳችኋል
ትዕግሥተኛ ሁኑ። ልጃችሁ በአንድ ጊዜ ይህን ባሕርዩን ይተዋል ብላችሁ አታስቡ፤ በተለይ ደግሞ እልኸኛ በሆነ ቁጥር ፍላጎቱን ትፈጽሙለት ከነበረ ቶሎ ላይስተካከል ይችላል። በተገቢው መንገድ ምላሽ ከሰጣችሁና በአቋማችሁ ከጸናችሁ ግን ባሕርዩ እየተስተካከለ ይሄዳል። ቀስ በቀስም እልኸኝነቱ ሙሉ በሙሉ ይተወዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “ፍቅር ታጋሽ” እንደሆነ ይናገራል።—1 ቆሮንቶስ 13:4
በተጨማሪም የሚከተሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ለማድረግ ሞክሩ፦
ልጃችሁ በእልኽ መንፈራገጥ በሚጀምርበት ጊዜ ከቻላችሁ እቀፉት፤ ከዚያም በእጃችሁ ያዝ በማድረግ እንዳይወራጭ ለማድረግ ሞክሩ፤ እርግጥ ነው፣ በጣም አጥብቃችሁ እንዳትይዙት ወይም እንዳትጎዱት መጠንቀቅ ያስፈልጋችኋል። ልጁ ላይ አትጩኹበት። ንዴቱ እስኪበርድለት በትዕግሥት ጠብቁ። ልጁ እልኽ መጋባቱ የትም እንደማያደርሰው መረዳቱ አይቀርም።
ልጃችሁ በእልኽ በሚረብሽበት ጊዜ አንድ ቦታ እንዲቀመጥ አድርጉት። ከዚያ ቦታ መንቀሳቀስ የሚችለው እልኹ ሲወጣለት እንደሆነ ንገሩትና ትታችሁት ሂዱ።
ልጃችሁ እንዲህ ያለ ባሕርይ ያሳየው ብዙ ሰው ባለበት ቦታ ከሆነ ሌሎች ሊያዩት ወደማይችሉበት ቦታ ውሰዱት። የሌሎችን ትኩረት የሚስብ ነገር ስላደረገ ብቻ አትሸነፉለት። አለዚያ ልጁ፣ እልኸኛ መሆኑ የፈለገውን ለማግኘት እንደሚያስችለው ሊያስብ ይችላል።
^ አን.5 በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ ልጆች ስንናገር በወንድ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።