በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የፍትሕ መጓደል የሌለበት ቦታ አልነበረም

የፍትሕ መጓደል የሌለበት ቦታ አልነበረም

የተወለድኩት በ1965 በሰሜን አየርላንድ ሲሆን ቤተሰቦቼ ድሃ ነበሩ። ያደግሁት በካውንቲ ዴሪ ነው። በወቅቱ በፕሮቴስታንቶችና በካቶሊኮች መካከል ግጭት ነበር፤ “ትራብልስ” ተብሎ የሚታወቀው ይህ አሰቃቂ ግጭት ለ30 ዓመታት ዘልቋል። አነስተኛ የሆኑት ካቶሊኮች ከፍተኛ ቁጥር በነበራቸው ፕሮቴስታንቶች መድልዎ እንደሚፈጸምባቸው ይሰማቸው ነበር፤ ካቶሊኮቹ ከምርጫ፣ ከፖሊስ ቁጥጥር፣ ከሥራ እና ከመኖሪያ ቤት ጋር በተያያዘ ፍትሐዊ ያልሆነ አሠራር እንዳለ ቅሬታቸውን ያሰሙ ነበር።

የፍትሕ መጓደልና መድልዎ የማይፈጸምበት ቦታ አልነበረም ማለት ይቻላል። በተደጋጋሚ ጊዜያት ተደብድቤያለሁ። እንዲሁም በርካታ ጊዜያት ከመኪና ጎትተው በማውጣት በሽጉጥ አስፈራርተውኝ ያውቃሉ፤ በፖሊሶች ወይም በወታደሮች የተፈተሽኩበትና ምርመራ የተደረገብኝ ጊዜም አለ። ግፍ እና ጭቆና እየደረሰብኝ እንዳለ ስለተሰማኝ ‘ያለኝ አማራጭ ወይ በደሉን ችሎ መኖር አሊያም መቃወም ነው!’ ብዬ አሰብኩ።

የብሪታንያ ወታደሮች በ1972 የገደሏቸውን 14 ሰዎች ለማሰብ ተብለው በሚዘጋጁትና ብለዲ ሰንዴይ ተብለው በሚጠሩት ሰልፎች እካፈል ነበር፤ እንዲሁም በ1981 የረሃብ አድማ አድርገው የሞቱትን ሪፑብሊካን እስረኞች ለማሰብ በሚደረጉት ሰልፎች ተካፍያለሁ። ባገኘሁበት ቦታ ሁሉ የታገዱ ባንዲራዎችን እሰቅል እንዲሁም የብሪታንያን መንግሥት የሚቃወም  ጽሑፍ እጽፍ ነበር። ተቃውሞ እንድናሰማ የሚያነሳሳን ነገር ጠፍቶ አያውቅም፤ ለምሳሌ፣ ካቶሊኮች መገደላቸው ወይም በእነሱ ላይ ግፍ መፈጸሙ ለተቃውሞ እንድንወጣ ያደርገን ነበር። መጀመሪያ ላይ ሰላማዊ የሚመስለው ሰልፍ አብዛኛውን ጊዜ ተፋፍሞ ትልቅ ረብሻ ይነሳል።

ዩኒቨርሲቲ ሳለሁ የአካባቢ ደኅንነትን በተመለከተ በሚደረጉ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መካፈል ጀመርኩ። ወደ ለንደን ከተዛወርኩ በኋላ ደግሞ ድሆችን እየበደሉ ሀብታሞችን የሚጠቅሙ የመንግሥት ፖሊሲዎችን ለመቃወም በሚደረጉ የሶሻሊስት ሰልፎች ተካፍያለሁ። የሠራተኛ ማኅበራት የደመወዝ መቀነስን በመቃወም በሚያደርጓቸው አድማዎች እንዲሁም ገቢን ያላገናዘበ የግብር ሕግን በመቃወም በ1990 በተካሄደውና በትራፋልጋር አደባባይ ላይ ከፍተኛ ውድመት ባስከተለው ሰልፍም ተሳትፌያለሁ።

ውሎ ሲያድር ግን ተስፋ መቁረጥ ጀመርኩ። ተቃውሟችንን ማሰማታችን የተነሳንባቸውን ዓላማዎች ከማሳካት ይልቅ ጥላቻ እንዲቀጣጠል እንዳደረገ ተሰማኝ።

የሰው ልጆች ዓላማቸው ጥሩ ቢሆንም እንኳ ፍትሕንና እኩልነትን ፈጽሞ ሊያሰፍኑ አይችሉም

አንድ ወዳጄ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያስተዋወቀኝ በዚህ ጊዜ አካባቢ ነበር። እነሱም አምላክ የሚደርስብን መከራ እንደሚያሳዝነውና የሰው ልጆች ያደረሱትን ጉዳት በሙሉ እንደሚያስተካክለው ከመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሩኝ። (ኢሳይያስ 65:17፤ ራእይ 21:3, 4) የሰው ልጆች ዓላማቸው ጥሩ ቢሆንም እንኳ ፍትሕንና እኩልነትን ፈጽሞ ሊያሰፍኑ አይችሉም። ሰዎች የአምላክ አመራር ያስፈልጋቸዋል፤ ከዚህም ሌላ በዓለም ላይ ላሉት ችግሮች ተጠያቂ የሆኑትን አጋንንት ማስወገድ የሚችለው አምላክ ብቻ ነው።—ኤርምያስ 10:23፤ ኤፌሶን 6:12

አሁን ሳስበው የፍትሕ መጓደልን ለማስወገድ አደርግ የነበረው ጥረት፣ እየሰጠመ ባለ መርከብ ላይ የሚገኙ ወንበሮችን ለመጠገን እንደ መሞከር ነበር። በዓለማችን ላይ የፍትሕ መጓደል የማይኖርበትና ሁሉም ሰው እኩል የሚሆንበት ጊዜ እንደሚመጣ ማወቄ ይህ ነው የማይባል እፎይታ አስገኝቶልኛል።

መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ አምላክ ‘ፍትሕን እንደሚወድ’ ያስተምራል። (መዝሙር 37:28) አምላክ፣ ሰብዓዊ መንግሥታት ሊያመጡት ያልቻሉትን ፍትሕ እንደሚያሰፍን እንድንተማመን የሚያደርገን አንዱ ምክንያት ይህ ነው። (ዳንኤል 2:44) ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከፈለግህ በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች ማናገር አሊያም www.mr1310.com/am የተባለውን ድረ ገጻችንን መመልከት ትችላለህ።