ንድፍ አውጪ አለው?
አስደናቂ የሆነው የእንጭርሪት የመስማት ችሎታ
በደቡብ አሜሪካ የምትገኘው የዛፍ ዋዝንቢት (Bush katydid) ጆሮ፣ ከአንድ ሚሊ ሜትር ያነሰ ሲሆን የሚሠራው ግን የሰው ልጆች ጆሮ ከሚሠራበት መንገድ ጋር በሚመሳሰል መልኩ ነው። ይህች ነፍሳት (ኮፒፎራ ጎርጎኔንሲስ) የተለያዩ ዓይነት የድምፅ ሞገዶችን ከረጅም ርቀት መለየት ትችላለች። ዋዝንቢቶችና የሌሊት ወፎች፣ የሰው ልጆች ሊሰሙት የማይችሉ ድምፅ ያወጣሉ፤ ይህች ዋዝንቢት ግን በእነዚህ ድምፆች መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ስለምትችል ሌላ ዋዝንቢት የሚያሰማውን ድምፅ፣ አዳኝ የሆነ የሌሊት ወፍ ከሚያሰማው ድምፅ ለመለየት አትቸገርም።
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ የዋዝንቢት ጆሮ የሚገኘው በሁለት የፊት እግሮቿ ላይ ነው። የዚህች ነፍሳት ጆሮ ልክ እንደ ሰው ጆሮ የድምፅ ሞገዶችን ይቀበላል፤ ይቀይራል እንዲሁም የድምፅ ሞገዶችን ዓይነት ይለያል። የሳይንስ ሊቃውንት፣ በዚህች ነፍሳት ጆሮ ውስጥ ሞላላ ፊኛ የመሰለና በታመቀ ፈሳሽ የተሞላ አንድ ልዩ ነገር አግኝተዋል። አኩስቲክ ቬሲክል የሚል መጠሪያ የሰጡት ይህ ነገር የሚሠራው፣ በአጥቢ እንስሳት ውስጥ ከሚገኘው ኮክልያ (በጆሮ ውስጠኛ ክፍል የሚገኝ አካል) ጋር በሚመሳሰል መንገድ ነው፤ መጠኑ ግን ከኮክልያ በጣም ያንሳል። ዋዝንቢት አስደናቂ የሆነ የመስማት ችሎታ ሊኖራት የቻለው በአኩስቲክ ቬሲክል ምክንያት ነው።
በዩናይትድ ኪንግደም፣ የብሪስቶል የሥነ ሕይወት ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዳንኤል ሮበርት፣ ይህ ግኝት “በተፈጥሮ ንድፍ ላይ የተመሠረቱ፣ መጠናቸው ከአሁኖቹ የማዳመጫ መሣሪያዎች ያነሱና እስካሁን ከነበሩት ሁሉ የተሻሉ የማዳመጫ መሣሪያዎችን ለመሥራት” መሐንዲሶችን እንደሚረዳቸው ገልጸዋል። በተጨማሪም ግኝቱ፣ ሆስፒታሎች ለምርመራ የሚጠቀሙባቸውን መሣሪያዎች ጨምሮ በአልትራሶኒክ የምሕንድስና ዘርፍ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለመድረስ እገዛ እንደሚያደርግ ተመራማሪዎች ያምናሉ።
ምን ይመስልሃል? አስደናቂ የሆነው የዋዝንቢት የመስማት ችሎታ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?